1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«እዉር አሞራ ቀላቢ» የኢትዮጵያዊዉ ስደተኛ እዉነተኛ ታሪክ

«እዉር አሞራ ቀላቢ »በእዉነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ዘጋቢ ፊልም ነዉ። ዘካሪያስ ጥበቡ መስፍን የተባለ ካናዳ የሚኖር ኢትዮጵያዊ  ደግሞ እዉነተኛዉ ባለታሪክ ነዉ። ፊልሙ በአሳዛኙ የስደት ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን በኒዉዮርክ ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ የፊልም ፌስቲቫልና በዳላስ ቴክሳስ ዓለም ዓቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:21

«ያሳለፍኩት አሰቃቂ የስደት ህይወት አሁንም ድረስ በሀሳቤ እየመጣ ይረብሸኛል»

 የሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት አግኝቷል። በመጪዉ ሳምንት ጥቅምት 6/ 2010ዓ,ም በኢትዮጵያ ተመርቆ ለዕይታ ይበቃል። የዛሬዉ የባህል መድረክ ዝግጅታችን ይህንን ዘጋቢ ፊልም ይቃኛል። ለዝግጅቱ ፀሐይ ጫኔ።

« ዘካሪያስ ጥበቡ መስፍን እባላለሁ። በ1998 ዓ/ም ከሀገሬ ተሰድጀ ወደ እስራኤል ለመግባት ሰዉነቴን የሚያስረሳ መከራን አሳልፌያለሁ።» 

 «ዕዉር አሞራ ቀላቢ » ከተሰኘዉ ፊልም በጥቂቱ የተቀነጨበ ነበር። በእዉነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራዉ ይህ ፊልም የ1 ስዓት ከ25 ደቂቃ ርዝመት ያለዉ ሲሆን  በሳቢሳና ሲራራ የፊልም ፕሮዳክሽኖች የተሰራ ነዉ። የፊልሙ ባለታሪክ ዘካሪያስ ጥበቡ መስፍን በአሁኑ ጊዜ ነዋሪነቱ ካናዳ ቢሆንም ያለፈበት የስደት ህይወት በርካታ ስቃይና መከራ እንዲያይ አድርጎታል። የልጅነት ህይወቱም ቢሆን ዉጣዉረድ የበዛበትና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደነበር ያስታዉሳል። በተለይ ወላጅ እናቱን በሞት ከተነጠቀ በኋላ ሁሉም ነገር የተመሰቃቀለ ነበር ይላል።

በልጅነት ዕድሜዉ ወላጅና አይዞህ ባይ ያጣዉ ዘካሪያስ ትምህርቱን አቋርጦ ኑሮን ለማሸነፍ ፀጉር ማስተካከልን ጨምሮ  የልጅነት አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ መስራት ጀምሮ  ነበር። በጎንደር ከተማ ይሰራበት የነበረዉን ፀጉር ቤት ግን በተለዬ መልኩ ሁሌም  ያስታዉሰዋል። በፀጉር ቤቱ የሚታደሙትን ከዉጭ ሀገር የሚመጡ ደንበኞቹንም እንዲሁ። 
እናም በ14 ዓመት ዕድሜዉ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ጉዞ ጀመረ። ይሁን እንጅ የጓጓለት የስደት ህይወት እንዳሰበዉ ቀላል ሆኖ አላገኘዉም። የቋመጠለትን የድሎት ህይወትም በቀላሉ ሊጨብጠዉ እንደማይችል የገባዉ ያኔ ነበር። ስደት ለዘካሪያስ የተሻለ ህይወት ከማምጣት ይልቅ «አሁንም ድረስ በአእምሮዬ እየተመላለሰ ይረብሸኛል » የሚለዉን በርካታ ስቃይና መከራ እንዲያይ አድርጎታል።


 በተለይ ደግሞ ከሱዳን ወደ ግብፅ ያደረገዉን አስቸጋሪ የበረሃ ጉዞ ጨርሶ ወደ እስራኤል ለመሻገር ሲሞክር ሲና በረሃ ዉስጥ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪወችን ለመያዝ በተደረገ የቦንብ ጥቃት  ብዙ ስደተኞች መኪና ዉስጥ እንዳሉ መጋየታቸዉን  ያስታዉሳል።
ዘካሪያስ ከዚህ የቦንብ ጥቃት በተዓምር ቢተርፍም ከእስራኤል የድንበር ጠባቂ ፓሊሶች ግን ማምለጥ አልቻለም። እናም የጓጓለትን የእስራኤል ድንበር ሳይሻገር በድንበር ጠባቂ ፓሊሶች ተይዞ ወደ ግብፅ እንዲመለስ ተደረገና  አስዋን በተባለ ቦታ ወደ እስር ቤት ተወረወረ።   የ 2 ዓመት እስር ቆይታዉም ሌላ ስቃይ ሌላ መከራ ይዞበት መጣ።

የግብፅ ከፍተኛ ወንጀለኞች በሚታሰሩበት በዚህ እስር ቤት ፤«የብዙ ሰወች አይን ጠፍቷል፣ብዙወች አእምሮአቸዉ ተነክቷል ሴቶ እስረኞች ከወታደሮች ወልደዋል»ይላል ዘካሪያስ

ዘካሪያስ ይህንን ታሪኩን ባስታወሰ ቁጥር ያለቅሳል። በሰሃራና በሲና በረሃ ስለሞቱት፣ የአካል ጉዳት ስለደረስባቸዉ ፣ የአእምሮ በሽተኛ ስለሆኑት እና ስለተደፈሩት ወገኖቹ  ሲናገር አሁንም እምባ ይተናነቀዋል። ይህንን እዉነተኛ ታሪኩን «እዉር አሞራ ቀላቢ» በሚል በፊልም ሲያስቀርጸዉም «ከኔ ህይወት ሊሎች ይማሩበታል» በሚል እንደሆነ ይናጋራል።
 ዘጋቢ ፊልሙን ለማዘጋጀት የጅቡቲንና የሱዳን ድንበሮችን ጨምሮ በ 9 የኢትዮጵያ ከተሞች ወደ 8,800 ኪሎ ሜትሮች ተጉዘዉ ፊልሙን መቅረፃቸዉን የፊልሙ አዘጋጅና ዳይሬክተር ሰዉመሆን ይስማዉ ይገልጻል ። ሰዉ መሆን እንደሚለዉ ባለ ታሪኩ የተጓዘበት አስቸጋሪ ታሪክና መንገድ ለቀረፃም ቀላል አልነበረም።

ባለ ታሪኩ እንደሚለዉ ምንም እንኳ የትወና ሙያ ባይኖረዉም ያለፈበትን ህይወት ማስቀረፅ  አልከበደዉም። በቀረጻ ወቅት የሀዘን ስሜቱን መቆጣጠር ግን ሌላ ፈተና ሆኖበት ነበር። በተለይ የእናቱን መቃብር ለመጀመሪያ ጊዜ በማየቱ ስሜቱ ተጎድቶ እንደነበር ይናገራል። ለመሆኑ« እዉር አሞራ ቀላቢ» የፊልሙ  ርዕስ ሆኖ ለምን ተመረጠ?

«ያዉ ዕዉር አሞራ ማለት የሚያደርገዉን አያዉቅም ወደየት እንደሚሄድ አያዉቅም ስለ ምሳና እራቱ አያስብም ግን ፈጣሪ ራሱ ያኖረዋል። እኔንም ራሴን የመሰልኩት በዚያ ነዉ። እኔም ምንም ሰዉ ሳይኖረኝ በቂ ትምህርት ሳይኖረኝ ከዚህ ሁሉ መዓትና መከራ ያወጣኸኝ አንተ ነህና እዉነትም ዕዉር አሞራን ታኖራለህ እንኳን በአምሳልህ የፈጠርከዉን ሰዉ ብዬነዉ የሰየምኩት።»
በዘጋቢ ፊልሙ በህይወት የሌሉ ሰዎች ብቻ ገጸ-ባህሪ የተሳለላቸዉ ሲሆን አብዛኛዉ ታሪክ በዋናዎቹ ባለታሪኮች የተሠራ ነዉ። ያ የፊልሙን ቀረጻ አስቸጋሪ ቢያደርገዉም እንዲህ አይነት ፊልሞች መሰራታቸዉ ግን  ጠቀሜታቸዉ  ከፍተኛ መሆኑን ሰዉመሆን ይናገራል።


የፊልም ባለሙያዉና አዘጋጁ ሰዉመሆን ከዶክመንተሪ ድራማ ዘዉግ ይመደባል የሚለዉን ይህንን ፊልም የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን የሰጡት ሲሆን በአሜሪካ ኒዉ ዮርክ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል እና በዳላስ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች የሰርተፍኬትና የዋንጫ ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። ለፊልሙ በተቸረዉ በዚህ ጥሩ ምላሽም በገንዘብ የማይተመን የመፈስ እርካታ እንዳገኘበት ባለታሪኩ ይገልፃል።

ዘካሪያስ አሁን በ30ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነዉ። ከበርካታ የስደትና የስቃይ ዓመታት በኋላ ካናዳ ዉስጥ ትዳር መስርቶ የሁለት ልጆች አባት ሆኗል። ያም ሆኖ ግን ሰዎች «ተሳክቶለታል » ብለዉ ሊያስቡ አይገባም ነዉ የሚለዉ። አብረዉት ከተጓዙት 1,200 ስደተኞች 42 ብቻ በህይወት መትረፋቸዉን የሚናገረዉ ዘካሪያስ ፤ ስደትን «አላሸነፍኩትም» ይላል።
ከዓመታት በፊት ዘካሪያስ የተጓዘባቸዉ የስደት መንገዶች አሁንም ብዙዎች  ይጎርፉበታል። በሰሃራና በሲና በረሃዎች አሁንም ድረስ የተሻለ ህይወት ፍለጋ መንገድ ጀምረዉ የሚጠሙ፣ የሚራቡ፣ የሚሞቱ ብዙዎች መሆናቸዉ እየታየ ነዉ። የዘካሪያስ ጥበቡ መስፍን እዉነተኛ የስደት ታሪክም «እዉር አሞራ ቀላቢ» እያለ ይጣራል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ መዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic