1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

«እኛ የስራ ማቆም አድማ አልጠራንም»የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር

ማክሰኞ፣ ኅዳር 20 2015

«ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ኢንፎርማል ግሩፕ የኛን ሎጎ ተጠቅሞ ነው። እኛ ደግሞ ይህንን ጉዳይ ተከታትለን በህግ እንጠይቃለን እኛ የስራ ማቆሙ አድማ አልጠራንም። የጠየቅነውን 14 ጥያቄዎች ለመንግስት አስገብተናል ።እኛ በአሰራራችን መሰረት ለትምህርት ሚኒስቴር ነው ጥያቄያችንን ያስገባነው »

https://p.dw.com/p/4KFf9
Äthiopien Studierende Tigray Universität
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ትላንት ሰኞ አሁን ባለው አሰራር ለዩንቨርስቲ መምህራን ደሞዝ መጨመር እንደማይቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ 42 ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበር የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ጥሪ አለማቅረቡን ፕሬዝዳንቱ ዶክተር በፍቃዱ ዘለቀ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር በፍቃዱ እርሳቸው በሚመሩት ማኅበር ሥም ለኢትዮጵያ መንግሥት የቀረቡት አስራ አራት ጥያቄዎች በእርግጥም ዩኒቨርሲቲዎች መምራን እና ቴክኒካል ረዳቶች መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ ቢያረጋግጡም የሥራ ማቆም አድማ ግን እንዳልተጠራ ገልጸዋል።

 
«ይህን ጥያቄ ያቀረበው ኢንፎርማል ግሩፕ የኛን ሎጎ ተጠቅሞ ነው ጥሪውን ያቀረበው። እኛ  ደግሞ ይህንን ጉዳይ ተከታትለን በህግ እንጠይቃለን እኛ የስራ ማቆሙ አድማ አልጠራንም  የጠየቅነውን 14 ጥያቄዎችግን ለመንግስት አቅርበናል እነዚህን ጥያቄዎች በእኛ በአሰራር መሰረት ለትምህርት ሚኒስቴር ነው ያስገባነው »

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበር ስም እና አርማ በያዘ ደብዳቤ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ኅዳር 15 ቀን 2014 የተሰራጨው መግለጫ አስራ አራት ጥያቄዎችን የያዘ ነው። በማኅበሩ ስም ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ ዕድገት፣ የቤት አበልን የተመለከቱ ይገኙበታል። ደብዳቤው በተጨማሪ ስራዎች የሚገኝ ገቢ ላይ የግብር ቅነሳ፣ የሶስተኛ ዲግሪ የምርምር ገንዘብ መጠን፣ የመምህራን የዝውውር ጉዳዮችን ጭምር ያካተተ ነው። 

ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ ለትምህርት ሚኒስቴር እና መገናኛ ብዙኃን እንዲደርስ በተጻፈው ደብዳቤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እና የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የመምህራኑ ችግር "በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት" ጥረት ለማድረግ መሞከሩን ያትታል። መንግስት ጥያቄዎቹን "ሙሉ በሙሉ" እንዳልመለሰ የሚገልጸው ደብዳቤ ከኅዳር 26 ቀን ጀምሮ "ላልተወሰኑ ጊዜያት የሥራ ማቆም አድማ" እንደሚደረግም ይገልጻል። ደብዳቤው "ምንም ለውጥ" አላመጡም የሚላቸው የማኅበሩ አመራሮችም ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቋል። 
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር የቀረበውን ጥሪ መመልከታቸውን አረጋግጠዋል። ከዚህ በፊትም የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር የሚሉት መምህር የአሁኑ ጥሪ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ ባልደረቦቻቸው የቀረበ እንደሆነ ቬሌ ተናግረዋል። 

«የተለያዩ የዩንቨርስቲ መምህራን ናቸው ጥያቄውን ያቀረቡት። በዋናነት ንቅናቄው የተጀመረው በማህበራዊ ሚዲያ ነው። ስራ የማቆሙን አድማን የበላይ አመራሮች ላይቀበሉት ይችላሉ ሌሎቹን ነጥቦች ግን ይስማማሉ ብዬ ነው ማስበው ሁሉም አድማውን ይስማማል ብዬ አላምንም  አንዳንድ ለመንግስት ሀይል የሚያደሉ መምህራንም ይኖራሉ ። ከዚ በፊት አድማ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተደርገዋል  ባለፈው ክረምት እራሱ አስበን ነበር ተራዘመ ትክክለኛ ግዜ ስላልነበር አሁን ግን የህልውና ጥያቄ ነው»።   


ሌላው የዩንቨርስቲ መምህር የዩንቨርስቲ መምህራን የጠየቁት ጥያቄ የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ነው ሲሉ ለስራ ማቆሙ አድማ ዘግይተናል ይላሉ
«አብዛኛው የዩንቨርስቲ መምህር ዝቅተኛ ገቢ እና በጥቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኝ ነው ይህ ንግግር በ45 ዩንቨርስቲዎች የተደረገ ንግግር  ነው  በትዕግስት የቆየ ጥያቄ ነው ከታሰበግን ቆይቷል  ዘግይተናል»።


የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ትላንት ሰኞ አሁን ባለው አሰራር ለዩንቨርስቲ መምህራን ደሞዝ መጨመር እንደማይቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት ለኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች መምህራን መምህራንና ቴክኒክ ረዳቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር በፍቃዱ ዘለቀ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል። 
 «ፕሮፌሰር ብርሀኑ  ይህንን ስለማለታቸው መረጃ የለኝም አልሰማውም ቢሉም እኛ የምናቀርበው ጥያቄ ነው ከደሞዝ ጥያቄ  ውጪ ብዙ ጥያቄ ነው ያለን። እኛ ምላሽ እየጠበቅን ያለነው ከከፍተኛ የመንግስት አካል እና ከትምህርት ሚኒስቴርም ጋር ቁጭ ብለን ለመነጋገር ነው ያሰብነው» ብለዋል ።

ማኅሌት ፋሲል 

እሸቴ በቀለ