«ኤች አይ ቪ» እና የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ችግር | ጤና እና አካባቢ | DW | 28.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

«ኤች አይ ቪ» እና የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ችግር

ኢትዮጵያ ዉስጥ ላለፉት አስር ዓመታት ከHIV ተሐዋሲ ጋ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ «አካል ጉዳተኛ ሴቶች እኩል እድል እንዲኖራቸዉ» ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የማኅበሩ መሥራችና ሊቀመንበር ወ/ሪት ወይንሸት ሙሉሰዉ ይናገራሉ። ማኅበሩ ከተቋቋመ አስር ዓመቱን የደፈነዉ ባለፈዉ ዓመት ሐምሌ ማለቂያ ላይ ነበር።

የምሥረታዉን አስረኛ ዓመት አስመልክቶ ሊካሄድ የታሰበዉ ዝግጅት በተለይ ችግር ላይ የሚገኙ ለHIV የተጋለጡ አካል ጉዳተኛ ሴቶችና ሕፃናትን ለመርዳት በቂ ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል ቀኑን አሳልፎ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ዕለቱን ቢያስብም፤ የታሰበዉን ያህል ግን ብዙዎችን ለመርዳት የሚያስችል ገንዘብ አለመገኘቱን ያስረዳሉ ወ/ሪት ወይንሸት።

እንደየዓለም የጤና ድርጅት መረጃ በመላዉ ዓለም እስከጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር 2013 መጨረሻ ድረስ ከ33 እስከ 37 ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ሕዝብ የHIV ተኀዋሲ በደሙ ዉስጥ መኖሩ ተመዝግቧል። ከእነዚህ መካከልም በተለይ መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት 11,7ሚሊዮን የሚሆነዉ ሕዝብ የፀረ HIV መድኃኒት ተጠቃሚ መሆን ችሏል። ይህ ተላላፊ በሽታም እስካሁን የ39 ሚሊዮን ሰዎችን ነፍስ አጥፍቷል። ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ልዩ ትኩረት መደረግ እንደሚገባ የሚያሳስቡት ወ/ሪት ወይንሸት እነዚህ ወገኖች በተለይ ለHIV የተጋለጡ ናቸዉ የሚሉበትን ምክንያት ይዘረዝራሉ።

ሰባት በሚሆኑ ሴት የአካል ጉዳተኛና HIV ተኃዋሲ በደማቸዉ ዉስጥ በሚገኝ ዜጎች የተቋቋመዉ ማኅበር ሀገር ዓቀፍ ሲሆን ወደ473 የሚደርሱ አባላት አሉት። መሥራችና ሊቀመንበሯ እንደገለፁልንም በአዲስ አበባ ብቻ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ የሚበልጡ የማኅበሩ ርዳታና ድጋፍ ተጠቃሚዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከልም በጣም በከፋ ችግር ዉስጥ የሚገኙት ሁለት መቶ ሃምሳ ይሆናሉ። መድኃኒቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ በነፃ እንደሚሰጥም ሳይገልፁ አላለፉም ወ/ሪት ወይንሸት። መድኃኒቱን ማግኘቱ ግን ለአካል ጉዳተኞቹ ቀላል አለመሆኑንንም በአፅንኦት አመልክተዋል። መድኃኒቱ ቢኖርም እንኳ ለሰዉ ልጅ ሕይወት መሠረታዊ ነገሮች ለአብዛኞቹ ያልተሟሉ ናቸዉም ይላሉ። ማኅበሩ የፊታችን ሐምሌ መጨረሻ ገደማ 11ኛ ዓመቱን ይይዛል። ባለፉት ዓመታትም የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ችግሩ ግን ሊቀመንበሯ እንደገለፁት ቢያንስ አልጋ የያዙትን ህመምተኞች ለመደገፍ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ማጣት ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic