1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ወደ ኢትዮጵያ ከሚላከው ገንዘብ አብዛኛው በኢ-መደበኛ መንገድ ነው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2009

ኢትዮጵያ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ አንድ አራተኛው በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች የሚልኩት ነው። ይኸው ገንዘብ ከአገሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን ወደ 7% ድርሻ አለው። ኢትዮጵያውያኑ ገንዘባቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ግን ሁሌም መደበኛውን/ሕጋዊውን መንገድ አይከተሉም። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ያጣል። 

https://p.dw.com/p/2j73a
Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

ኢትዮጵያ የሚገባዉ ገንዘብ

የውጭ ምንዛሪ እጥረት አዘውትሮ የሚንጣት ኢትዮጵያ በተለምዶ "ስውር ገበያ" አንዳንዴም "እጅ በእጅ" እየተባለ የሚጠራው የጎንዮሽ የምንዛሪ ግብይት ይጫናት ይዟል። በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን ወደ አገር ለመላክ አሊያም ወዳጅ ዘመድ ለመደጎም የጎንዮሹን መንገድ ይመርጣሉ። ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት በያዝንው ወር ይፋ ያደረጉት ጥናት ከአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 78 ከመቶ ገንዘብ በኢ-መደበኛ መንገድ እንደሚላክ ይጠቁማል። ጥናቱን ያዘጋጁት የገንዘብ ዝውውር ጥናት ባለሙያው ሌዎን አይዛክስ ናቸው።
"ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ወደ 3.7 ቢሊዮን ዶላር {በአመት} አቅራቢያ እንደሆነ እንገምታለን። ከዚህ ውስጥ ወደ 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው በመደበኛው መንገድ፤ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይላካል። መደበኛ ባልሆነው መንገድ የሚላከው 78 ከመቶ ገንዘብ በተወሰኑ መተላለፊያዎች ነው። በሁሉም አይደለም። ከአውሮጳ እና ከአሜሪካ ይልቅ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶችን ከመሳሰሉ አገራት  ብዙ ገንዘብ መደበኛ ባልሆነው መንገድ ይላካል። ከአውሮጳ እና ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚላከው ገንዘብ ሐምሳ ሐምሳ አካባቢ ነው።"ሌዎን አይዛክስ ዴቬሎፒንግ ማርኬትስ አሶሼትስ የተባለው ኩባንያ ሥራ አስፃሚ ናቸው። በትምህርታቸው ኤኮኖሚን አጥንተዋል፤የዓለም ገንዘብ አዘዋዋሪዎች ጥምረትንም በበላይነት መርተው ያውቃሉ። ባለሙያው ከደቡብ አፍሪቃ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት፤ከአውሮጳ እስከ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን የገንዘብ መጠን ተንትነዋል። ገንዘቡ የሚላክበትን መንገድ፤ላኪዎቹ መደበኛውን አሊያም የጎንዮሹን ለመምረጥ የሚስገድዷቸውን ሁኔታዎችም ፈትሸዋል። ኢትዮጵያ ከጎረቤቷ ኬንያ፣  ራቅ ቢልም፣  ከሕንድ አኳያ አብዛኛውን ገንዘብ ከውጭ ሀገራት የምትቀበለው መደበኛ ባልሆነው መንገድ እንደሆነ ሌዎን አይዛክስ ይናገራሉ። በእርሳቸው ትንታኔ መሰረት የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ አለመኖርን የመሳሰሉ ምክንያቶች ኢ-መደበኛውን የገንዘብ መላኪያ መንገድ ከሚያበረታቱ መካከል ይጠቀሳሉ።
"የኢትዮጵያን ዲያስፖራ ብንመለከት አሁን እየተቀየረ ቢሆንም አብዛኛው ገንዘብ ለመላክ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ በሚጠየቁባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና በደቡብ አፍሪቃ የሚኖር ነው። ስለዚህ በዚያ የሚኖሩት ኢ-መደበኛውን የመላኪያ መንገድ ከመጠቀም ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም። አውሮጳ እና ሰሜን አሜሪካን በመሳሰሉ አካባቢዎች ላኪዎች እንዲህ አይነት መሥፈርት አይጠየቁም። ማንነታቸውን የሚገልጥ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፤ሕጋዊ መሆን አለመሆናቸውን ግን አይጠየቁም። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ አንድ ሰው ወደ ስውር ገበያ ሔዶ በመደበኛው መንገድ ከሚያገኘው የተሻለ ምንዛሪ የሚያገኝበት የጎንዮሽ የውጭ ምንዛሪ ተመን አለ። ገንዘባቸውን ከመደበኛው ይልቅ በኢ-መደበኛው መንገድ በመላክ ከ5-15 ከመቶ ተጨማሪ ያገኛሉ።"
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሰረት ከሁለት አመት በፊት በውጭ የሚኖሩ ዜጎች 3.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት ልከዋል። የዓለም የገንዘብ ተቋም በበኩሉ በ2014/2015 ወደ ኢትዮጵያ የተላከውን ገንዘብ 3-3.5 ቢሊዮን ያደርሰዋል። የዓለም ባንክ ቁጥሮች ግን ከብሔራዊ ባንኩም ይሁን ከገንዘብ ተቋሙ እጅጉን ያነሱ ናቸው። ሶስቱም ተቋማት ግን ኢትዮጵያ የሚላክላት ገንዘብ በመጨመሩ ላይ ይስማማሉ። 
በዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት ይፋ የተደረገው እና ሌዎን አይዛክስ ያዘጋጁት ጥናታዊ ሰነድ የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበኛውን መንገድ የሚላከውን ገንዘብ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ያደንቃል። ይሁንና በላኪዎች ዘንድ አሁንም ኢ-መደበኛው መንገድ ተመራጭ መሆኑን አይሸሽግም። በሰነዱ አባባል ለላኪዎቹ ፤ ለቤተሰቦቻቸውና እና ገንዘቡን ፈሰስ ለሚያደርጉበት የስራ መስክ ፈተና ነው።

ጥናታዊው ሰነድ ኢ-መደበኛው የገንዘብ ዝውውር ኢትዮጵያን መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሳጣውም አትቷል። በሰነዱ መሰረት ጥስው ገበያም የሚያጣቅሰው እና በተለይ በደቡብ አፍሪቃ እና ሳዑዲ አረቢያን በመሳሰሉ የመካከለኛው ምሥራቅ በሚኖሩ ዜጎች የሚመረጠው የገንዘብ መላኪያ መንገድ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት እንቅፋት እንደሚሆን ያትታል። 
በኢትዮጵያ መደበኛ ገበያ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተለይ ነጋዴዎች ወደ ኢ-መደበኛው መንገድ እንደሚገፋቸው ጭምር ሌዎን አይዛክስ ይናገራሉ።  
"በምንዛሪ ተመኑ ረገድ ሁለት ፈተናዎች እንዳሉ አስባለሁ። አንደኛው ከአውሮጳ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ዩሮ ወደ ዶላር መቀየር አለበት። የተላከው ገንዘብ መጠን የሚታወቀው የአሜሪካው ዶላር ከኢትዮጵያ ባንክ ደርሶ  ተከፋዩ ሊቀበል ሲሔድ ነው። ችግሩ ዛሬ 500 ዩሮ ቢላክ ተቀባዩ ባንክ እስኪሔድ ድረስ መጠኑ አይታወቅም። በኢ-መደበኛው መንገድ ሲላክ ግን ወዲያውኑ ለተቀባይ የሚደርሰው የገንዘብ መጠን ወዲያውኑ ይታወቃል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ገንዘቡን የሚከፍለው ግለሰብ ምንም ይሁን ምን የውጭ ምንዛሪውን ስለሚፈልገው ሊሆን ይችላል። አዘዋዋሪዎቹ ገንዘቡ በባንክ ቢላክ ከሚመነዘረው በላይ ለመክፈል ፈቃደኛ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ በዩሮ እንዲገዛላቸው የሚፈልጉት ነገር ስለሚኖር እና በኢትዮጵያ ባለው የምንዛሪ ቁጥጥር ምክንያት ዩሮ ለመግዛት በመቸገራቸው ነው።"  
ሌዎን ኢሳክስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት መሻሻሎች ማድረጉን ይናገራሉ። ይሁን እና በተለይ አሁንም ሳዑዲ አረቢያ እና ደቡብ አፍሪቃን በመሳሰሉ አገሮች ያለ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ የሚኖሩ ዜጎች በመደበኛው መንገድ ገንዘብ መላክ መቸገራቸው እንደሚቀጥል ባለሙያው ያስረዳሉ። 
"ሁለት ጎላ ያሉ ፈተናዎች አሉ ብዬ አስባለሁ። አንደኛው አብዛኛው ኢ-መደበኛ የገንዘብ ዝውውር የሚፈጸመው ምርጫ በሌላቸው ሰዎች ነው። ምክንያቱም ከመደበኛው ኤኮኖሚ ውጪ ገንዘብ በሚያገኙበት አገር ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚኖሩ ናቸው። ከዚያ አገር በመደበኛው መንገድ ገንዘብ ለመላክ አይፈቀድላቸውም። ሳዑዲ አረቢያ እና ደቡብ አፍሪቃ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ይኸ የሚቀየርበት ብቸኛው መንገድ ሁለቱም አገሮች ህጎቻቸውን ቢቀይሩ ነው። በተጨባጭ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሲባል ሊቀይሩ አይችሉም። ሕግጋቶቻቸውን እንዲቀይሩ ከብዙ አገራት ተጨባጭ ጫና በተባበረ መንገድ ያሻል።"
ሌዎን እንደሚሉት በኢ-መደበኛ መንገድ የሚላከውን ገንዘብ ወደ መደበኛው መንገድ መመለስ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርንም ለመግታት ይረዳል። የመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ደቡብ አፍሪቃን የመሰሉ አገራት ኢ-መደበኛውን መንገድ የሚመርጡ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ እንዲልኩ የሚያስችል ማሻሻያ እንዲያደርጉ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ጫና ብቻውን በቂ አይደለም። የተሻለ የምንዛሪ ተመን ፈልገው ኢ-መደበኛውን መንገድ የሚመርጡ ዜጎችን ወደ ሕጋዊው ለመመለስ የጎንዮሹን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ማስቆም ሌላው አማራጭ ነው። ሌዎን አይዛክስ እንደሚሉት ይኸ ግን ወደ ሌሎች የኤኮኖሚው ዘርፎች ተሻግሮ የከፋ ዳፋ ያስከትላል። 
"የጎንዮሹን ገበያ ለማስወገድ ከፈለጉ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኤኮኖሚያዊም ጣጣ ያመጣል። የጎንዮሹን ገበያ ካስወገዱ በብር የምንዛሪ ተመን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ይኸ ደግሞ በውጪ እና ገቢ ንግድ ተወዳዳሪነት ላይ ጫና ይኖረዋል። ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከውጭ በሚላከው ገንዘብ ላይ ካለው የሰፋ ተፅዕኖ አለው። መንግሥት ሊወስዳቸው የሚችላቸው እርምጃዎች አሉ። በተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) የሚደረግ ክፍያን ማበረታታት አንዱ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወጪያቸው ከተለመደው የገንዘብ ዝውውር በግማሽ ይቀንሳል። ከባንኮች ውጪ ያሉ ተቋማት እንዲህ አይነት የገንዘብ ክፍያ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ማበረታታትም ሌላው እርምጃ ነው። ሰዎች ርቀው በመጓዝ ወጪ ከሚያወጡ ይልቅ ከቤታቸው አቅራቢያ ገንዘባቸውን እንዲቀበሉ የሚያግዝ መሰረተ-ልማት በገጠራማ አካባቢዎችማስፋፋት በራሳቸው ሊያደርጉት የሚችሉት ነው።"
የጎንዮሹን የውጭ ምንዛሪ ግብይት አሊያም ጥቁሩን ገበያ የመቆጣጠሩ ነገር የፈታኝነቱን ያክል ጠቀሜታውም ላቅ ያለ ነው። ሌዎን አይዛክስ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ አብዛኛው ወደ መደበኛው ሥርዓት ቢገባ ከግለሰብ እስከ መንግሥት ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚያገኙይናገራሉ።
"ይመስለኛል ለረጅም ጊዜ የነበረ በመሆኑ ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት አድርሷል። ጥሩው ነገር አሁን ከምንገኝበት በመነሳት ልናሻሽለው እንችላለን። ትልቁ ችግር የኢትዮጵያ መንግሥት ኢ-መደበኛው የገንዘብ መላኪያ መንገድ ትልቅ ገበያ እንደሆነ ይረዳል። ምን ያክል ትልቅ እንደሆነ ግን ጠንቅቆ አያውቅም። ምን ያክል ወደ አገሪቱ እንደሚመጣ ሁሉ ትክክለኛ መረጃ ቢኖረው የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ጫና ባሳደረ ነበር። ሁለተኛው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ ይቀይረዋል። በመደበኛው መንገድ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ከመጣ ለሚፈልጉት አስመጪዎች ይሸጣል። ለመንግሥት በርካታ እቅዶችም ግልጋሎት ላይ ይውላል። ሶስተኛው በቤተሰብ ደረጃ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በተለይ በርካታ ሰዎች ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ እንዲገቡ ያግዛል። ሰዎች የባንክ ደብተር ይኖራቸዋል። በጀርመን አሊያም በፈረንሳይ ያለው የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙም ያደርጋቸዋል።"

Destination Europe – Kapitel-Nr. 7
ምስል LAIF
Banknote in Briefkasten
ምስል fotolia
Logo Internationale Organisation für Migration IOM
ምስል IOM/Alemayehu Seifeselassie


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ