ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞችና ህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች | ኢትዮጵያ | DW | 23.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞችና ህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች

የአውሮጳ አገራት ከሊቢያ ወደ አውሮጳ የሚደረገውን የስደተኞች ጉዞ ለማስቀረት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመምከር ላይ ናቸው። አውሮጳውያኑ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪቃ ካለው ጭቆና፤ ድህነት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ይልቅ በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ትኩረት አድርገዋል።

የሙዓመር ጋዳፊ ውድቀት ለሊቢያ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ስርዓት፣የፍትሃዊ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል ቀዳሚ ምዕራፍ ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮቿ በአገሪቱ የተነሳውን አብዮት ሲደግፉ የሰውየውን ተቃዋሚዎች ሲያስታጥቁም «ዋንኛ አላማችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሊቢያ እንዲኖር ማገዝ ነው» ብለው ነበር። ሊቢያ ግን ዛሬ የተባለችዉ አይደለችም። ታጣቂዎች እርስ በርስ የሚፋጁባት፤ በየአካባቢዉ የነገሱባት፤ ከአፍሪቃና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በመነሳት ወደ አውሮጳ ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች መሸጋገሪያ፤ መገደያም ሐገር ሆናለች።እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የሊቢያ መንግስታዊ መዋቅር በመፈራረሱ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ወይም ደላሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያጋብሱባት ምድር ናት። ከልካይ ህግም ይሁን ህግ አስከባሪ የለምና።

አሁን በትሪፖሊ ከተማ ለስደተኞች በተዘጋጀ መጋዘን ውስጥ የሚገኘው ልዑል ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ከዛ ወደ ሊቢያ የተጓዘው በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ነበር። በመጋዘኑ ውስጥ ቢኒያምን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከልዑል ጋር ይገኛሉ።«ሱዳን የጉዞ ፈቃድ (ቪዛ) ስለከለከለች በህገ-ወጥ መንገድ ነበር መውጣት የነበረብን። ካርቱም ለመድረስ አስራ አምስት ቀን ነው የፈጀብን።» የሚለው ቢኒያም የሰሐራ በርሃን በማቋረጥ ሊቢያ ሲደርስ ሌሎች 81 ሰዎች አብረውት እንደነበር ያስታውሳል።

ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሊቢያ ከልካይ የለባቸውም። ስራቸውን በግልጽ ይከውናሉ። አንዳንዶቹ ራሳቸውን ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ጭምር ያስተዋውቃሉ።እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ መሆናቸውንና በሊቢያ ግዛቶችን ከሚቆጣጠሩ ታጣቂዎች ጋርም ግንኙነት እንዳላቸው አሶሼትድ ፕሬስ ይፋ ያደረገው ጽሁፍ ያትታል። ሙዓመር ጋዳፊ ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረገውን የስደተኞች ፍልሰት ለመቆጣጠር ከአውሮጳ ህብረት ጋር ውል ነበራቸው። አውሮጳን በዘመነ ጋዳፊ ያሳሰበው የስደተኞች ብዛት ከእሳቸው ውድቀት በኋላ እጅጉን አሻቅቧል። በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2010 ዓ.ም. ከሊቢያ ወደ አውሮጳ የተሻገሩ ስደተኞች ቁጥር 4,500 የነበረ ሲሆን፤ በ2014 ወደ 170,000 አድጓል። ሁኔታው ያሳሰባቸው የአውሮጳ አገራት በሊቢያ በሚገኙት ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ብሎም ለስደተኞቹ በሜድትራኒያን ባህር ዳርቻ መጠለያ ለማበጀት የሚያስችል እቅድ እንዳላቸው የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ሮቤርታ ፒዮንቲ ተናግረዋል። ፕሮ አዙል የተሰኘዉ የጀርመን የስደተኞች ተቆርቋሪ ድርጅት የበላይ ካርል ኮፕ ግን ይህም ቢሆን ለስደተኞቹ ተብሎ የታሰበ አይደለም በማለት ይተቻሉ።

«ይሕ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንዳይቀርቡ ለማድረግ ያለመ ነዉ።ከሶሪያ የሚሰደዱ ብዙ አሉ።አንድ ስደተኛ ከሶሪያ አዉሮጳ መድረስ የሚችለዉ እንዴት ነዉ።ፕሮ አዙል የሚፈልገዉ ስደተኞች በግልፅ አዉሮጳ የሚገቡበት መንገድና ሥልት እንዲኖር ነዉ።የሚደረገዉ ግን በተቃራኒዉ ነዉ።ወደ መጡበት ይመለሳሉ።ስደተኞች በሕጋዊ መንገድ እንዲገቡ ሳይፈቀድ ሰዎችን የሚያሽግሩት ወገኖችን እንቆጣጠር ማለት ስደተኞቹ ባሕር ላይ ሳይሆን፤አዉሮጳ ድንበር አጠገብ ይሙቱ እንደማለት ነዉ።»

ልዑልና ቢኒያምን መሰል ስደተኞችን ከአገር አገር በህገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩት እና ከተሳካላቸዉ ከአነስተኛ ጀልባ ጀምሮ እስከ መርከብ በመጠቀም ከወደ አውሮጳ የሚያሻግሩት፤ ደላሎች አዘዋዋሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ኪሳቸው እየደለበ መጥቷል። የሜድትራኒያንን ባህር ለማቋረጥ የሚከፈለው እንደ ጀልባው አይነት ከ1000- እስከ 2000 ዶላር ይደርሳል። ክፍያው ሁል ጊዜም በቅድሚያ የሚከፈል ሲሆን ስደተኞቹ ክፍያውን ለመፈጸም በሊቢያ ህጋዊም ይሁን ህገ-ወጥ ስራዎችን ይሰራሉ። በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ስራው ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት ቢኒያም ተናግሯል።

ልዑል እና ቢኒያም አሁን በትሪፖሊ ከተማ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ የአውሮጳ ጉዟቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩት በሽፍን መኪና በመሆኑ የት እንዳለ አያውቁም። ስልክ መደወል እና ከቀሪው አለም ጋር ግንኙነት ለማድረግ የህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹን ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic