አፍሪቃ፤ የተፈጥሮ ሃብቷ፣ ሙስናና ብዝበዛው | ኤኮኖሚ | DW | 04.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አፍሪቃ፤ የተፈጥሮ ሃብቷ፣ ሙስናና ብዝበዛው

አፍሪቃ ብዙዎች የሚፈልጉት የተፈጥሮ ሐብት፤ ነዳጅ ዘይት፣ ጋዝ፣ የተለያዩ ንጥረ-ነገሮች ወዘተ. ባለጸጋ ናት። ይሁንና ሕዝቧ የዚህ ሃብት ተጠቃሚ ሆኖ አይገኝም።

default

ለዚህም በተለይ ሙስና፣ የአስተዳደር ዝቤትና ብዝበዛ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው። ችግሩን ለመቋቋም የአፍሪቃ መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ሃላፊነቱን እንዴት መከፋፈል አለባቸው? ይህ በየጊዜውና በያጋጣሚው ሲነሣ የቆየ ጥያቄ ነው። ባለፈው ሣምንትም በዚህ በጀርመን በርሊን ከተማ ውስጥ በተካሄደ ውይይት ትኩረት ተደርጎበት ነበር። በጀርመኑ በጎ-አድራጎት ድርጅት በሃይንሪሽ-በል-ሽቲፍቱንግ አዘጋጅነት በተካሄደው ውይይት ፖለቲከኞች፣ የኤኮኖሚ ጠበብትና የኩባንያ ተጠሪዎች፤ እንዲሁም ከአፍሪቃና ከአውሮፓ የመጡ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ልዑካን ተሳትፈዋል። በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት የቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሢያና ብራዚል ተጠሪዎችም እንዲሁ የውይይቱ ተካፋዮች ነበሩ። ስብሰባው የተጠናቀቀው ማሕበራዊና ሃላፊነት የተመላበት የተፈጥሮ ሃብት ፖሊሲ ሰነድን በማጽደቅ ነው።

የተፈጥሮ ሃብትን በተመለከተ ጥያቄው የመኖር ያለመኖር፤ የድሀነት ወይም የሃብታምነት ጥያቄ ነው። በዓለም ላይ በተፈጥሮ ሃብት ታላቅ ከሚባሉት ሃገራት መካከል 12ቱ በከፋ ድህነት ላይ የሚገኙ ናቸው። ሰፊ የነዳጅ ዘይት ምንጭ ያላቸው 26 ሃገራት በሙስና ይተቻሉ። ከግማሽ በላዩ በተፈጥሮ ሃብት የታደሉ አገሮች ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የላቸውም። እንግዲህ ችግሩ ብዙ ለውጥን የሚጠይቅ ሆኖ ነው የሚገኘው። የኬንያ ብሄራዊ የነዳጅ ዘይት ድርጅት ባልደረባ ሱማያ አታማኒ በውይይቱ ላይ አገራቸው ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ሃብቱን ልትጠቀም እንደምትችል አመልክተዋል። “ምንም እንኳ ገና ለማምረት ባንበቃም ከሁለቱም ወገን የመማር የተለየ ዕድል አለን። በጥሬ ሃብታችው የሚያገኙትን ገቢ በጥሩ ሁኔታ ከሚጠቀሙትና ያላግባብ ከሚይዙት ወገኖችም እንዲሁ! በዚሁ አንድ ሁነኛ ዘዴ ልናዳብር፣ ስሕተቶችን ከወዲሁ ልናስወግድና ስኬት ልናገኝ እንደምንችል ተሥፋ አደርጋለሁ”

በነገራችን ላይ ኬንያ ብዙ ሃብት ለማስገባት ተሥፋ የምታቀነቅነው ገና አንዲት ጠብታ ነዳጅ ዘይት እንኳ ከከርሰ-ምድር አውጥታ ባላየችበት ወቅት ነው። በጥሬ ሐብቱ ዘርፍ ይበልጥ ግልጽ አሠራር እንዲኖርና ሃብቱን በመንከባከቡ ረገድም ለነገሩ ጥረቶች አልተጓደሉም። ለምሳሌ የአውሮፓ የኤኮኖሚና የትብብር ድርጅት፤ በአሕጽሮት OECD ለዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ያሰፈነው የተግባር መርህ አለው። ከዚህ በተጨማሪም “Publish What You Pay” “የምትከፍለውን ይፋ አድርግ” በሚል ዓለምአቀፍ ዘመቻ መንግሥታት ገቢያቸውን ይፋ እንዲያደርጉ፤ ኩባንያዎችም በፊናቸው የሚከፍሉትን እንዲናገሩ ጥረት ይካሄዳል።
አሁን በቅርቡ የተያዘው አዲስ ጥረት ደግሞ ኩባንያዎች፣ መንግሥታትና ሲቪሉ ሕብረተሰብ ይበልጥ Transparency ግልጽነት እንዲያሳዩ ይጠይቃል። ግን በሌላ በኩል ግዴታው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ብዙም ፍቱን መሆኑ ያጠያይቃል። በናይጄሪያ “የከፈልከውን ይፋ አድርግ” የሚለው ጥረት ባልደረባ ዴቪድ ኡጎሎር ስለዚሁ ሲያስረዱ፤ “አፍሪቃ ውስጥ በሰፈነው ሙስና ምዕራባውያን ኩባንያዎችም ተሳታፊ መሆናቸው ሲበዛ ግልጽ ነው። ስለዚህም የምዕራባውያኑ ሙስናን የመታገል ጥረቶች ፍቱንነት የላቸውም። ጉዳዩን አፍሪቃ በሙስና የተዋጠችና ተቋማቷም ደካሞች ናቸው ከሚል ዕምነት ብቻ ከተመለከቱት ሁኔታው የባሰ ነው የሚሆነው”

የካሜሩኑ የኤኮኖሚ ባለሙያና በዚያው ተቀማጭ የሆነው የአፍሪላንድ ባንክ ፕሬዚደንት ፖካምም እንዲሁ በተባለው ጥረት ላይ ተሥፋ ከመጣል ይልቅ ተጠራጣሪ ናቸው። “የምርት አውጪው ኢንዱስትሪ ጥረት ዋነኞቹን ወገኖች ሳያሳትፍ ነው የተነሣው። ቁልፍ የሆኑትን ኩባንያዎች ማለቴ ነው። በውይይቱ እንዲካተቱ አልተደረገም። በመሆኑም ይህን መሰሉ ዕቅድ እነዚህ ኩባንያዎች በድርድሩ ጥረጴዛ ላይ አብረው ሳይቀመጡ ስኬት ያገኛል ብዬ አላምንም። ምንም ውጤት አይታየኝም”

ከአፍሪቃ ተሳታፊዎች በኩል ሌላም ሃሣብ መሰንዘሩ አልቀረም። ሙስናንና የተዛባ የመንግሥት የኤኮኖሚ አያያዝን በሙስና የሚታሙ መንግሥታትንና ጸረ-ሙስና ጥረት የሚያካሂዱ ወገኖችን በማካተት ብቻ መታገል አይቻልም የኤኮኖሚው ባለሙያ እንደሚሉት። “የናይጄሪያ ሙስና በዚህ ጥረት ሳቢያ ለዝቧል ብለው ያምናሉ? እኔ በበኩሌ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን ናይጄሪያ በጥሬ ሃብት አያያዝ ግልጽነት የማስፈኑም ጥረት በፊርማ አጽድቃለች። ይህ ደግሞ መንግሥት መልሶ እንዲመረጥ ሰዎችን በጉቦ በሚገዛበትና ሕዝብ የተፈጥሮው ሃብት ተጠቃሚ ባልሆነበት አገር እንዴት ነው የሚቻለው። ለኔ ጥረቱ እንዳች ትርጉም የለውም”

ሃቁ ይህ በመሆኑም ብዙዎች በወቅቱ Trasparenz ወይም ግልጽነትን ዓቢይ የአጀንዳ ርዕስ አድርጎ ባስቀመጠው የጀርመን የ G-8 መንግሥታት ፕሬዚደንትነት ዘመን ላይ ብርቱ ተሥፋ ጥለዋል። ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ ውል እንዲኖር ነው የሚፈለገው። ለምሳሌ ያህል Global Witness የተሰኘው ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት መሥራችና አፈ-ቀላጤ ፓትሪክ አሌይ አሣሪና የሚያስከስሱ ደምቦች ዕውን ሊሆኑ ይገባል ይላሉ። “በዕውነት የሚያስፈልገን በጎ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ነው። ዛሬ ጥሬ ሃብትን፣ ውዝግቦችንና ሙስናን የመሳሰሉት ጉዳዮች ዓቢይ የፖለቲካ አጀንዳዎች ናቸው። ከአሥር ዓመታት በፊት እንዲህ አልነበረም። አሁን አንዳንድ ዘዴዎች አሉ። ሆኖም ግን ብዙም ከቃል የሚያልፉም አይደሉም። እና ሕጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው። እኔ አሣሪ ባልሆኑ ደምቦች አላምንም”

የሚፈለገው ይህ ከሆነ የሚከተለው ጥያቄ ማነው የሚቀጥለውን ዕርምጃ የመውሰድ ሃላፊነት ያለበት የሚለው ይሆናል። አፍሪቃ ወይስ ምዕራቡ ዓለም? እንደ ኬንያው ብሄራዊ የነዳጅ ዘይት ድርጅት ባልደረባ እንደ ሱማያ አትማኒ ከሆነ ችግሩ ሁሉንም የሚነካ ነው። “ችግሩ የአፍሪቃ ነወይ? እርግጥ የአፍሪቃ ነው! አፍሪቃውያን መንግሥታት ለክፍለ-ዓለሚቱ ችግሮች ሃላፊነት መውሰድ አለባቸው። ግን የተቀረውስ ዓለም? ምዕራቡ ዓለም ችግሩን አውቆ እስካልተቀበለ ድረስ ወደ ድንበሩ የሚፈሰው ስደተኛ መጨመርና በብልጽግናው ላይ የተደቀነው አደጋ አያከትምም። እርግጥ ችግሩ ያለው ምርቱ በሚገኝባቸው አገሮች ነው። ይህ ደግሞ ከመልክዓ-ምድር አቀማመጥ አንጻር ሩቅ ሊመስል ይችላል። ግን አሁን የቤታችውን ደጃፍ እያንኳኳ ነው”

ተዛማጅ ዘገባዎች