አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች | የጋዜጦች አምድ | DW | 13.11.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች

በዚህ ሣምንት ጀርመን ውስጥ በተለይ አበይቱና ሀገርአቀፍ ተነባቢነት ያላቸው እለታዊ ጋዜጦች ናቸው ለአፍሪቃው አህጉር ሰፊውን ትኩረት የሰጡት። ሰፊውን ጋዜጣዊ ሽፋን ያገኙት ዋንኞቹ ያፍሪቃ ጉዳዮች፥ አውሮጳ ለጎረቤቱ አህጉር እርጋታ የሚሰማትን ኃላፊነት፣ በቀውስ የተወጠረችው ዚምባብዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን ለመልቀቅ ስለመፈለጋቸው የሚነፍሰውን ጥቆማ፣ ተመላሾቹ የቡርኪና ፋሶ አእላፍ ስደተኞች የሚገኙበትን ጉስቁልና፣ በሰሜን ኡጋንዳ ሃይማኖትን መሣሪያ የሚያደርጉት ኣማጽያን የሚፈጽሙን ጭፍጨፋ፣ የጦር ወንጀል ክስ የሚቀርብባቸው የቀድሞው የላይቤሪያ አምባገነን ቻርልስ ቴይለር እንዲያዙ የሚደረውን ሙከራ፣ አፍሪቃውያን መሪዎች የኮትዲቯርን ፖለቲካ ቀውስ ለማውሳት በአክራ ያካሄዱትን ጉባኤ እና ታዋቂው ጀርመናዊ የሙዚያ ከያኒ ሐርበርት ግረነማየር “የጋራ ርምጃ ለአፍሪቃ” በተሰኘው መፈክር ፳፭ ግብረሠናይ ድርጅቶችን በማስተባበር የልማት መዋጮ ለማሰባሰብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የተመለከቱ ናቸው። አሁን ከእነዚሁ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን በትኩረት እንመልከት፥

የአፍሪቃ መንግሥታት አህጉሩን ለማረጋጋት አንድ የሰላም ጥበቃ ኃይል ለማቋቋም በሚያደርጉት ጥረት ረገድ የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን ለመርዳት አሁን ዝግጁ መሆኑን አረጋገጧል፣ ለዚሁም ዓላማ ከአውሮጳው የልማት መዋጮ ግምጃቤት ፪፻፶ ሚሊዮን ኦይሮ እንዲወሰድ የቀረበው ሐሳብ አሁን በኮሚሲዮኑ እና በአባላቱ ሀገሮች መካከል ክርክርን ፈጥሮአል። የግራው ለዘብተኛ ጋዜጣ ፍራንክፉርተር ሩንትሻው እንደዘገበው፣ የአፍሪቃው የሰላም ጥበቃ ኃይል ግንባታ በድህነት አንፃር የሚደረገውን ትግል ማድከም እንደሌለበት ጀርመናዊቱ የልማት ትብብር ሚኒስትሪት ሃይደማሪ ቪቾረክ-ትሶይል በጥብቅ ያስገነዝባሉ። የአውሮጳው ኅብረት ለጎረቤት አህጉር አፍሪቃ ተዓማኒነትንና የኃላፊነት ስሜትን ለማጠናከር የሚበቃው ለዚያው የሰላም ጥበቃ ኃይል ምሥረታ ተጨማሪ ገንዘብ ዝግጁ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን አበክረው ማስገንዘባቸው ተመልክቷል። እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ የፍፁም ድሆች አሃዝ በግማሽ እንዲቀነስ የተተለመው ግብ ከሁሉ የቀደመውን ትኩረት ማግኘት እንደሚገባው ነው፣ “ፍራንክፉርተር ሩንትሻው” እንደሚለው፣ ሚኒስትሪቱ የሚከራከሩት።

ለዚምባብዌ ሰፊ ትኩረት የሰጠው የደቡብ ጀርመን ጋዜጣ “ዚውትዶይቸ ትሳይቱንክ” ዓምባገነን ሮበርት ሙጋቤ ቦታ ከለቀቁ በኋላ ሥልጣን ለማካበት የሚሹት ቡችሎቻቸው አሁን አቆብቁበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን፣ ግን በዚህ አንፃር ሰፊው የሀገሪቱ ሕዝብ በየጊዜው ወደ መከራ ኑሮ እንደሚያሽቆለቁል ያመለክታል። በጋዜጣው ዘገባ መሠረት፣ የ፸፱ ዓመቱ ሙጋቤ ምናልባት የመንግሥታቸው ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ በመጭው ታህሣሥ በሚከፍተው ጉባኤ ላይ ሥልጣን’ እንደሚለቁ ያስታውቁ ይሆናል ነው የሚባለው። የዋጋው ግሽበት እስከ ፩ሺ በመቶ እንደደረሰ በሚገመትባት፣ ከሕዝቡ ፸ በመቶው ሥራአጥ በሆነባት እና የመከራ ማዕበል በተስፋፋባት ሀገር ውስጥ ሕዝቡ አሁን የሚናፍቀው ለዚሁ መከራ ያበቁት ዐምባገነን ከሥልጣኑ መድረክ የሚወገዱበትን ጊዜ ነው ይላል “ዚውትዶይቸ ትሳይቱንክ።

ለአሠርተ ዓመታት ኮትዲቯር ውስጥ የስደት ኑሮ ሲያሳልፉ የቆዩት አእላፉ የቡርኪና ፋሶ ስደተኞች አሁን ከጦርነትና ከክትትል ለመዳን ወደሀገራቸው ቢመለሱም፣ እዚያም የጠበቃቸው የባሰው የኑሮ ሥቃይ መሆኑን የዘገበው የበርሊኑ ግራዘመም ጋዜጣ “ታገስትሳይቱንክ”፣ የጀርመን ቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት “ጂቲዜድ” ይህንኑ መከራ ለማቃለልና በተለይ ሴቶችንና ሕፃናትን መልሶ ለማቋቋም ባለፈው ግንቦት በአንድ ሚሊዮን ኦይሮ አንድ ፕሮዤ እንደዘረጋ ያስረዳል። ይኸው ጋዜጣ ቀጥሎ የቡርኪና ፋሶ፣ የጋና፣ የቶጎ፣ እና የቤኒን ፕሬዚደንቶች በጎረቤት ኮትዲቯር ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔውን ለመፈለግ ከዚያችው ሀገር መሪ ግባግቦ ጋር በጋና ርእሰከተማ አክራ ውይይት ቢከፍቱም፣ ግባግቦ ከአማጽያኑ ጋር ለመነጋገር አለመፈለጋቸውን አመልክቷል።

ናይጀሪያ ውስጥ የተንደላቀቀ የስደተኛነት ኑሮ የሚመሩት የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር አካባቢውን ሲያበጣብጡ በኖሩበት እና የጦር ወንጀል በፈፀሙበት አድራጎታቸው አንፃር ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚፈለጉበትን ሁኔታ የሚያብራራው ጋዜጣ “ፍራንክፉርተር ሩንትሻው”፣ እኒሁኑ የጦር ወንጀለኛ ለመያዝ ያስቻለ ሰው ሁለት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጠው ዋሽንግተን ውስጥ መነገሩን ጠቅሶታል። በአሜሪካው በጀት ውስጥ ለሴራሊዎን በተቋቋመው ልዩ ፍርድቤት ፊት መቅረብ ላለበት ለአንድ በስም ያልተጠቀሰ የጦር ወንጀለኛ ማስያዣ ፪ ሚሊዮን ዶላር እንደተመደ መገለፁንና ያው የተባለው ጦርወንጀለኛ ቻርልስ ቴይለርን የሚመለከት መሆን እንዳለበት ጋዜጣው ተንትኖ አቅርቦታል። ግን፣ በፍራንክእፉርተር ሩንትሻው ዘገባ መሠረት፣ ይኸው የታሰበው ያሜሪካው ርምጃ ለቻርልስ ቴይለር የፖለቲካ ተገን የሰጠውን የናይጀሪያውን መንግሥት ያስቆጣና ወደፊትም የሚያስቆጣ ሆኖ ነው የሚታየው።