አፍሪቃዉያን ስደተኞች በሰሜናዊ ጀርመን | አፍሪቃ | DW | 04.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አፍሪቃዉያን ስደተኞች በሰሜናዊ ጀርመን

ወደ ጀርመን በገቡት አፍሪቃዉያን ስደተኞች ምክንያት፤ የጀርመን እና የጣልያን ወዳጅነት እየተቃወሰ ነዉ። ከጥቂት ወራቶች ወዲህ በርካታ ወጣት ወንድ አፍሪቃዉያን ስደተኞች በሊቢያ የሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ድርጅት ጦር «የ ኔቶ» ጥቃትን በመሸሽ ወደ ደቡባዊ አዉሮጳ ጣልያን ከገቡት መካከል በርካቶች ጀርመን ገብተዋል።

በጣልያን በኩል አድርገዉ የመጡት ወደ 300 የሚጠጉት አፍሪቃዉያን ስደተኞች በሰሜናዊ ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ ያለ መጠለያ የጎዳና ተዳዳሪ በመሆናቸዉ እና ስለ ስደተኞቹ ማንም ሃላፊነትን ባለመዉሰዱ ከተማዋ መፍትሄን ለማግኘት ጥሪ አቅርባለች። ዝርዝሩን አዜብ ታደሰ ታቀርበዋለች። በሃምቡርግ ከተማ ማዕከላዊ የባቡር ጣብያ አካባቢ አፍሪቃዉያኑ ስደተኞች በሚያድሩበት አነስተኛ ድንኳን አጠገብ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ የከተማዉ ነዋሪ ጥያቂያቸዉን እንዲያይላቸዉ በትልቁ በጽሁፍ ለጥፈዉ ይታያል። ከጥያቄዎቻቸዉ መካከል «በሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ድርጅት፤ «ኔቶ» ጦርነት እንድንሰደድ ግድ ሆኖብናል» «መብታችን እንጠይቃለን» ይላል። ስደተኞቹ በጉዳና ላይ በሰሩት የመኖርያ ድንኳን ዉስጥ ከሚኖሩት መካከል የ 31 ዓመቱ ናይጄርያዊ ፍሪዲ ይገኛበታል። ፍሪዲ በጣልያን የሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ ከተዘጋ በኋላ፤ ወደ ሰሚናዊ ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ ከገባ አንድ ወር ግድም ሊሆነዉ ነዉ። ፍሪዲ በጣልያን የሸንጌን ቪዛን እና 500 ይሮን ተቀብሎአል።

«ከጣልያን መንግስት ያገኘሁት ስጦታ ነበር። ከነሱ በቀጣይ ምንም ዓይነት ገንዘብ እንደማናገኝ ነግረዉናል» ከአዉሮጳ ህብረት ለስደተኞች ጉዳይ የሚዉለዉ ገንዘብ ባለፈዉ የካቲት ወር በመጠናቀቁ ጣልያን ስደተኞችን መቀበሏን አቁማለች።

«በኢጣልያ ወረቀት ከሰጡን በኋላ ወደ ሌላ የአዉሮጳ ህብረት አባል አገር ሄዳችሁ አዲስ ህይወት መጀመር ትችላላችሁ ብለዉ ነገሩን» ፍሪዲ በጣልያን ሁለት ዓመት ኖሪያለሁ፤ በጣም የሚያበሳጭ ግዜን ነዉ ያሳለፍኩት ሲል በመማረር ይገልጻል። በርግጥ ለምን ሰሜናዊዋ ጀርመን ከተማ ሃንቡርግን እንደመረጠ እና ወደዝያ እንደመጣ ግን አይናገርም። እንደ ፍሪዲ ሁሉ ወደ ጀርመን ሰሜናዊ ከተማ ሃምቡርግ መጥተዉ በየመንገዱ የሚኖሩት ወደ 300 የሚጠጉ ስደተኞች ተይዘን ወደ ጣልያን እንመለሳለንል የሚል ስጋት ላይ ወድቀዋል።

«ወደ ጣልያን በግዴታ ከተመለስን፤ ወደ ገሃነብ ተመልሰን እንደገባን ነዉ የሚቆጠረዉ። እዝያ ምን ሊደርስብን እንደሚችል የምናዉቀዉ ነገር የለም። በጣልያን ያለዉ ሁኔታ እጅግ የተበላሸ ሆንዋል»ስደተኞቹ በሙሉ የመጡት ከሊቢያ ነዉ። «በሊቢያ ሳለን ጥሩ ስራና ኑሮ ነበረን» ሲል ሌላዉ ስደተኛ የቶጎዉ ተወላጅ ይናገራል። በሊቢያ ይኖሩ የነበሩት እነዚህ ስደተኞች የሞአመር ጋዳፊ ስርዓት ሲገረሰስ በሊቢያ ተወላጆች ጥቃት ይደርስባቸዉ ጀመር። በርካታ የሊቢያ ነዋሪዎች የሞአመር ጋዳፊ ደጋፊዎች አድርገዉ ያዩዋቸዉም ጀመር።

በጣልያን በኩል ወደ ሰሜናዊ ጀርመን፤ ሃንቡርግ ከተማ በገቡት ከሊቢያ በመጡት ስደተኞች ምክንያት በሃንቡርግ አስከፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳለ እየተነገረ ነዉ። የጀርመን የግራ ፓርቲ የዉስጥ ፖለቲካ ጉዳይ ቃል አቀባይ ክርስትያን ሽናይደር፤ በሃምቡርግ ምክር ቤት ላይ ታላቅ ወቀሳን አሰምተዋል፤ እሳቸዉ የሚያራምዱት የግራ ፓርቲ እና አረንጓዴዉ ፓርቲ በሃምቡርግ በየጎዳናዉ የሚገኙት የአፍሪቃን ስደተኞች ጉዳይ ችላ ተብሎአል ባይ ናቸዉ።

በሌላ በኩል በሃንቡርግ ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳይ ተጠሪ ዴትሊቭ ሺለ በጣልያን በኩል ወደ ወደ ጀርመን ሃንቡርግ ከተማ የገቡትና በየጎዳናዉ ላይ የሚታዩት ስደተኞች በሃምቡርግ ምንም አይነት ተስፋ እንደሌላቸዉ ይገልጻሉ።

« በቤተክርስትያን አካባቢ መጠለያ ከተገኘ፤ ወደ መጡበት ከመላካቸዉ በፊት እዝያ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንት ልናስቀምጣቸዉ እንችላለን» ስለስደተኞች ጉዳይ በጀርመን እና በጣልያን መካከል የተጀመረዉ ድርድር ሌላ አቅጣጫን የያዘ ይመስላል፤ ይኸዉም፤ ወጣት ስደተኞቹን ከአዉሮጳ ህብረት ሃገራት ዉጭ ወደ ትዉልድ ሀገራቸዉ መመለሱ ከሁሉ የተሻለ አማራጭ ነዉ ተብሎአል።

በጦርነት ምክንያት ከመኖርያቸዉ የተፈናቀሉት የሊቢያ ስደተኞች በበኩላቸዉ ጉዳዩን ሃላፊነት የጎደለዉ ነዉ ሲሉ በጥርጣሪ ያዩታል፤ ምክንያቱም ከሁለት ዓመት በፊት የሞአመር ጋዳፊን መንግስት ለመገርሰስ በተደረገዉ የቦንብ ጥቃት የአዉሮጳ ሀገራትም ተካፋይ ስለነበሩ ነዉ።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic