አይቮሪ ኮስትና የኮኮ ምርት | ኤኮኖሚ | DW | 28.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አይቮሪ ኮስትና የኮኮ ምርት

አይቮሪ ኮስት ኮኮ ምርትን ለውጭ ገበዮች በመላክ በዓለም ላይ ታላቋ አገር መሆኗ ይታወቃል። ምዕራብ አፍሪቃይቱ አገር በዓለምአቀፍ ንጽጽር የምርቱን ከሲሶ የሚበልጥ ድርሻ ትይዛለች።

አይቮሪ ኮስት ኮኮ ምርትን ለውጭ ገበዮች በመላክ በዓለም ላይ ታላቋ አገር መሆኗ ይታወቃል። ምዕራብ አፍሪቃይቱ አገር በዓለምአቀፍ ንጽጽር የምርቱን ከሲሶ የሚበልጥ ድርሻ ትይዛለች። ይሁን እንጂ አይቮሪ ኮስት ከአንድ አሠርተ-ዓመት የፖለቲካ ቀውስ በኋላ ዛሬ የቀድሞ የገበያ ድርሻዋን አጥታ ነው የምትገኘው። አገሪቱን እስከቅርብ ያናጋው የፖለቲካ ነውጽ በኮኮው መስክም ከባድ መዋቅራዊ ችግሮችን ነው ማስከተሉ አልቀረም። በዚህም የተነሣ በዓለም ገበያ የኮኮ ንግዷ ድርሻ ከአርባ ወደ 35 ከመቶ ነው ያቆለቆለው።

በኮኮ ምርት ተፎካካሪዎቿ የሆኑት የጋና ወይም የላቲን አሜሪካ ሃገራት የገበያ ድርሻ በአንጻሩ ጨምሯል። በአይቮሪ ኮስት የኮኮው ምርት ዘርፍ የተዳከመው ገበሬው በሚገባ የሠለጠነ ባለመሆኑ፣ የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ ተክሎችን ማምረቱን እየመረጠ መሄዱ፣ በዓለም ገበያ ላይ በጣሙን የሚጨምረው ዋጋና ምርቱን የሚገዙት የመሃል ነጋዴዎች ዘይቤ አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጠው ባለመሆኑ ነው። የጀርመን የኮኮ ንግድ ማሕበር ባልደረባ ለሁኔታው መሻሻል ጉድለቱን በሚገባ ማውጣጣት ግድ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

«በመጀመሪያ ደረጃ ጉድለቱን ፈልጎ ማግኘቱ አስፈላጊ ነው። የገበሬዎቹና የኮኮው እርሻ ሕልውና በሌሎች ካውቹክን በመሳሰሉ ተክሎች አደጋ ላይ ወድቋል። በብቃት አይተከልም። ገበሬው በመሠረቱ ባለፈው ጊዜ ዋጋ የተወሰነ ባለመሆኑ ጥቂት ድርሻ ኖሮት ነው የኖረው። አዲሱ የአይቮሪ ኮስት መንግሥት አንድ የገበያ ለውጥ ሲያደርግ ይህም ካለፈው ጥር ወዲህ እየተሰራበት ነው። ለውጡ ሁለት ግቦች ሲኖሩት አንዱም የውስጡን ገበያ ማረጋጋት ነው»

በነገራችን ላይ የአይቮሪኮስት ገበሬ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በኪሎግራም ኮኮ 15 ኤውሮ እንዲያገኝ ሕግ ተፈጥሮለታል። ይህም ትልቅ መሻሻል ነው። ከአቢጃን በስተደቡብ የሚገኝ የጋራ የኮኮ እርሻ ሃላፊ የሆነው ጆርጅ ታኖህ እንደሚለው በቀውሱ ዓመታት የኮኮ አተካከልን የተመለከተ ብዙ ዕውቀት ነው የጠፋው። ብዙ ገበሬዎች በውዝግቡ የተነሣ የእርሻ መሬታቸውን እየተዉ መሸሽ ነበረባቸው። አሁን በዚያ ቦታ ያሉት ስለ ኮኮ አንዳች ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ናቸው።

በዚሁ የተነሣም አዲሱ የኡዋታራ መንግሥት የኮኮን ገበያ ስርዓት በመጠገንና ቋሚ ዋጋን በማስፈን የአነስተኛውን ገበሬ የወደፊት ተሥፋና ዋስትና ለማጠናከር፤ እንዲያም ሲል ለዘለቄታው በኮኮ ተክል ተግባር ተሰማርቶ እንዲቀጥል ለማበረታታት እየጣረ ነው። መንግሥት ባካሄደው ለውጥ የኮኮ ዋጋ መረጋገጥ መላውን የምርት ዓመት በተሻለ ሁኔታ ማቀድ እንደሚያስችል ነው የሚናገረው። በአንድሬያስ ክሪስቲያንዘን አገላለጽ በዚሁ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ገበያውን እንዳሻቸው የሚጠቀሙበት ጊዜም አልፏል።

«ይህ የአይቮሪ ኮስት መንግሥት ሁኔታውን በማጤን የወሰደው የመጀመሪያ ዕርምጃ ነው። አሁን ከለውጡ በኋላ ሁሉም የእርሻው ዘርፍ ተሳታፊዎች መዋዕለ ነዋይ ማድረግ እንዲችሉ ጥርጊያ ተከፍቷል። ጥንት ነገሩ እንዲህ አልነበረም። በአገሪቱ የሰፈሩ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ነበሩ ገበያውን የሚቆጣጠሩት። የሚከፍሉትም ታዲያ እነርሱ የፈለጉትን ያህል ነበር»

አሁን እንግዲህ ለጀርመን ኩባንያዎችም ሁኔታው ተለውጧል።

«ቀድሞ ከነጋዴዎችና ከአስገቢዎች ይገዛ የነበረ አንድ የጀርመን ኩባንያ ዛሬ በቀጥታ ከአገሬው አምራች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አሣሪ የአቅርቦት ውል ሊዋዋል ይችላል። ሌላ ወገን መጥቶ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ይነጥቀኛል የሚል ስጋት አያድርበትም። ሁሉም አንድ ዓይነት ዋጋ መክፈል ስላለበት ችግሩ ተወግዷል ማለት ነው»

የኮኮ ዋጋ በቶን 2450 ዶላር ገደማ ያወጣል። ምዕራብ አፍሪቃይቱ አገር ውስጥ «ቡናማው ፍሬ» ኮኮ የሕልውና ዋስትና የሆነ ታላቅ የፖለቲካ ክብደት ያለው ምርት ነው።

የኮኮ ገቢ ከአይቮሪ ኮስት አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር 20 በመቶ መሆኑና ከቡና ጋር የአገሪቱን የውጭ ንግድ 40 በመቶ ድርሻም መያዙ ሁኔታውን ግልጽ ያደርገዋል። አይቮሪ ኮስት ውስጥ ባለፈው ሣምንት የመጀመሪያው ዓለምአቀፍ የኮኮ ምርት ጉባዔ ሲካሄድ ይህም የአገሪቱ ንግድ መልሶ በመጠናከር ላይ ለመሆኑ ምልክት መሆኑ አልቀረም። በጉባዔው ላይ ተገኝተው የነበሩት የጀርመን ኮኮ አስመጭ ኩባንያዎች ማሕበር ባልደረባ አንድሬያስ ክሪስቲያንዝንም ምርታማነት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ነው የሚናገሩት።

ብዙዎቹ አነስተኛ ገበሬዎች የማደግ አቅም እንዳላቸው ያምናሉ። ዛሬ አንድ የአይቮሪ ኮስት ገበሬ በሄክታር 500 ኪሎ ኮኮ ያመርታል። ግን አጥብቆ ሊያመርት ቢጥር አምሥት ዕጁ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ክሪስቲያንዘን ያስረዳሉ።

በአቢጃኑ ጉባዔ ላይ የኮኮው ኢንዱስትሪ ዋነኛ ተጠሪዎች ሲሰበሰቡ ዓላማቸውም እያደገ ከሚሄደው የገበያ ፍላጎትና በተክሉ አኳያ የሚያንዣብብ አደጋ አንጻር ጥረትን በጋራ ለማቀናበር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበር። በሌላ አነጋገር የኮኮን ኤኮኖሚ ዘላቂ አድርጎ ለማቆየት ጥልቅ የሆነ ለውጥ መካሄዱን ይጠይቃል። ለንደን ላይ ተቀማጭ በሆነው ዓለምአቀፍ የኮኮ ድርጅት ICCO እና በአይቮሪ ኮስት ትብብር በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ ከ 1,200 የሚበልጡ በርካታ ኢንዱስትሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ የአምራቾች ተጠሪዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በኮኮ ምርት ቾኮሌት፣ የኮኮ መጠጥና መሰል የገበያ ዕቃዎች የሚመረቱ ሲሆን እነዚህን ሰርተው የሚያወጡት ወገኖች በመጪው ዓመት የገበያውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት የሚበቁ አይሆኑም። እንግዲህ በሁለቱ ታላላቅ የኮኮ ገበዮች በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የቾኮሌት ፍጆት ከፍተኛ ሲሆን ብራዚልን፣ ሕንድንና ቻይናን በመሳሰሉት ግዙፍ በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ላይ ያሉ መጤ ሃገራትም ፍላጎቱ በጣሙን እየሰፋ ሄዷል።

በመሆኑም የኮኮን ምርት ዘላቂነት ለማረጋገጥ አስፈላጊው ዕርምጃ ከወዲሁ ክልተወሰደ የቾኮሌት ምርት ብርቅዬ እየሆነ እንዳይሄድና በኮኮው ዘርፍ ለብዙ ትውልድ የሚተርፍ ማቆልቆል እንዳይከተል አስጊ ነው። ይህ እንዳይሆን ገበሬዎች ካውቹክንና የተክል ዘይትን ወደመሳሰሉ ሌሎች ምርቶች እንዳያዘነብሉ ማድረግ፣ ጥራትንና ምርታማነትን ማዳበር ወዘተ የወደፊቱ የዘርፉ ቁልፍ ተግባራት ይሆናሉ።

መረጃዎችን ለመጠቃቀስ በአፍሪቃ ከአይቮሪ ኮስት ቀጥላ ሁለተኛዋ ታላቅ የኮኮ አምራጥ ጋና ስትሆን በዓለምአቀፍ ንጽጽር ድርሻዋ 21,7 ከመቶ የሚደርስ ነው። አይቮሪ ኮስት 35,6 ከመቶ፤ ላቲን አሜሪካ 15,4 ከመቶ፤ እሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ደግሞ 14,3 ከመቶ! ኢንዶኔዚያ በተናጠል 12,1 ከመቶውን ድርሻ ትያዛለች።

የሆነው ሆኖ በዓለም አቀፉ የኮኮ ድርጅት መረጃ መሠረት የኮኮ ምርት በከፊልም በሣሃራ በዓመቱ መጀመሪያ ጠንክሮ በተገኘ ደረቅ ነፋስ ሳቢያ ምርት ጥሩ ሆኖ ከተገኘበት 2010/11 ሲነጻጸር በ 8,1 ከመቶ አቆልቁሏል። ይህም አርባ ከመቶ የሚደርስ የዋጋ ንረትን ነበር ያስከተለው። በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 3,962,000 ቶን ምርት የሚጠበቅ ሲሆን ከዚሁ ቡናማ ፍሬ ከ 70 በመቶ የሚበልጠው ምርት ለዓለም ገበያ የሚቀርበውም ከአፍሪቃ ነው። አይቮሪ ኮስት ብቻ 1,410,000 ቶን ታቀርባለች። ሂደቱም መልሶ ዕድገት የሚታይበት ነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic