አዜያንና የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ራዕዩ | ኤኮኖሚ | DW | 24.08.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አዜያንና የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ራዕዩ

በአሕጽሮት አዜያን በመባል የሚታወቀው የደቡብ ምሥራቅ እሢያ መንግሥታት ማሕበር ዓባል ሃገራት በአውሮፓ ሕብረት አርአያ ውስጣዊ የጋራ ገበያ ለመክፈት ይፈልጋሉ። አዜያን የጋራ የኤኮኖሚ አካባቢ ከመፍጠርና የንግድ መሰናክሎችን ከማስወገድ ባሻገር ከአሜሪካ ጋር የንግድ ውል ለማስፈን ያለው ፍላጎትም እጅግ እየጠነከረ ሄዷል።

የአዜያን ጉባዔ በኩዋላ ሉምፑር

የአዜያን ጉባዔ በኩዋላ ሉምፑር

የአዜያን መንግሥታት ማሕበር የገንዘብ ሚኒስትሮች በወቅቱ ማሌይዚያ ርዕሰ-ከተማ ኩዋላ ሉምፑር ላይ ተሰብስበው በአካባቢው ዘላቂ የምጣኔ ሐብት ትስስር ጉዳይ እየመከሩ ነው። ሚኒስትሮቹ እስከ ነገ በሚዘልቀው ጉባዔ ላይ እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በአውሮፓ ሕብረት መልክ የተዋቀረ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ለማቋቋም ተስማምተዋል። ጉዳዩ በፊታችን ታሕሣስ ወር ፊሊፒን ውስጥ ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ቀርቦ ከጸደቀ ከዚህ ቀደም ከታሰበው የጊዜ ገደብ በአምሥት ዓመታት የፈጠነ ነው የሚሆነው።

ለጉዳዩ መፋጠን ምክንያት የሆነው የማሌይዚያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ባዳዊ እንዳሉት በዓለምአቀፉ የምጣኔ ሐብት ዕርምጃ አካባቢው ወደ ኋላ እንዳይቀር የተፈጠረው ስጋት ነው። “አዜያን በጋራ መቋቋም ያለበት ታላቅ ፈተና ተደቅኖበታል። የምጣኔ ሐብት ይዞታችን ይበልጥ ከዓለም ኤኮኖሚ እየተሳሰረ እንደመሆኑ መጠን በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ዕድገት በቅርብ መከታተል ይኖርብናል። በአጠቃላይ የውጩ ዕርምጃ በትስስር ጥረታችን ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ግንዛቤ መኖሩ አስፈላጊ ነው”

በደቡብ ምሥራቅ እሢያ የጋራ የሆነ ውስጣዊ ገበያ በመፍጠሩ በኩል በተለይ ትልቁ ችግር በአዜያን መንግሥታት መካከል ያለው የኤኮኖሚና የፖለቲካ ልዩነት ነው። ከማሕበሩ አሥር ዓባል መንግሥታት መካከል ሢንጋፑርን የመሳሰሉ ዘመናዊና ያደጉ መንግሥታት ሲገኙ ላኦስንና በርማን የመሳሰሉ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ የሚገኙ አገሮችም አሉ። የበርማ አምባገነን ወታደራዊ አገዛዝ ለደቡብ ምሥራቅ እሢያው መንግሥታት ዕድገትም ሆነ የዴሞክራሲ ዕርምጃ ከባድ ችግር ወይም መሰናክል እየሆነ ነው የመጣው። ከዋሺንተን ጋር የሚታሰበውን የንግድ ውል የአሜሪካው ብሄራዊ ሸንጎ በዚሁ በበርማ አምገነን አገዛዝ የተነሣ እንዳይቃወመውም ያሰጋል።

በሌላ በኩል የፊሊፒን የንግድ መድረክ ባልደረባ ማይክል ካላንሢይ እንደሚያምኑት አዜያን መንግሥታት በመካከላቸው ያለውን የንግድ መሰናክል አስወግደው የውስጡን የጋራ ገበያ ዕውን ማድረጉ የሚገዳቸው አይሆንም። “በአዜያን ስብስብ ውስጥ በራሱ ሊቆም የሚችል 500 ሚሊዮን ሕዝብን የጠቀለለ የፍጆት ገበያ አለን። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የሚያወራው ስለ ቻይና ነው። ግን አዜያንም ከአምሥት እስከ ሰባት በመቶ ዓመታዊ የኤኮኖሚ ዕድገት በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ችላ ይባል እንጂ የሚናቅ ዕርምጃ አይደለም”

የደቡብ ምሥራቅ እሢያው መንግሥታት ማሕበር አዜያን የተቋቋመው ባንግኮክ ላይ ከ 39 ዓመታት በፊት ነበር። መሥራቾቹ ታይላንድ፣ ኢንዶኔዚያ፣ ፊሊፒንና ሢንጋፑር ሲሆኑ ማሕበሩ ዛሬ አሥር ዓባላትን የሚጠቀልል ነው።