አውሮፓና የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ የንግድ ግንኙነት | ኤኮኖሚ | DW | 14.03.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አውሮፓና የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ የንግድ ግንኙነት

አውሮፓውያን መንግሥታት ከቀድሞዎቹ ቅኝ ግዛቶች፤ የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ አገሮች ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት ፍትሃዊነት ለብዙ ዓመታት ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው።

እርግጥ የአውሮፓ ሕብረት በሎሜ ውል መሠረት ለነዚሁ አገራት የተለየ የንግድ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል። ይሁንና የዓለም ንግድ ድርጅት የግንኙነቱ መልክ እንዲለወጥ ከወሰነ ወዲህ ሕብረቱ አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን ግፊት እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ገበዮቻቸውን መክፈት የሚገደዱትን ብዙዎቹን ታዳጊ አገሮች ከጥቅም እጦት ስጋት ላይ መጣሉ አልቀረም። የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት የልማት ሚኒስትሮች ትናንትና ከትናንት በስቲያ 78 ሃገራትን ከጠቀለለው የታዳጊው ዓለም ቡድን ተጠሪዎች ጋር በዚህ በቦን ተገናኝተው ተነጋግረው ነበር።

27 ዓባል መንግሥታትን ያቀፈው የአውሮፓ ሕብረት ከአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሲፊክ ሃገራት ስብስብ ጋር አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል እንዲያሰፍን በዓለም ንግድ ድርጅት የተጣለው የጊዜ ገደብ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ያከትማል። ሁለቱ ወገን እስካሁን በጉዳዩ ያካሄዱት ንግግር የገበያን ድርሻ፣ በጎ አስተዳደርንና የዕርዳታ መጠንን በመሳሰሉ ጉዳዮች ለወራት መሰናክል ገጥሞት ነው የቆየው። በጠቅላላው 78 ሃገራትን ያቀፈው የአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሲፊክ መንግሥታት ስብስብ ለሶሥት አሠርተ ዓመታት ጥገኛ ሆኖ ከቆየበት ወደ አውሮፓው ሕብረት ገበዮች የሚያዘልቅ ልዩ የንግድ አስተያየት በቀላሉ ለመሰናበት ፈቃደኛ አይደለም።

የሁለቱ ወገን ትብብር የተጀመረው እ.ጎ.አ. በ 1975 ማለት ከ 32 ዓመታት በፊት በተደረገ የሎሜ ውል ነበር። ከዚያም የንግድ ግንኙነታችውን የሚያለዝብ ተከታይ ውል በሰኔ ወር 2000 ዓ.ም. ኮቶኑ ላይ ይፈራረማሉ። እንግዲህ አሁን አዲስ የኤኮኖሚ ትብብር ውል ለማስፈን የተያዘው ጥረት ከዚሁ የተከተለ መሆኑ ነው። ጥያቄው ከታቀደው ነጻ ንግድ ማን ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል የሚለው ሆኖ ይቀጥላል።

ብዙዎቹ የቀድሞዎቹ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ በሚያደርገው አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ከጠቃሚነት ይልቅ ተጎጂ እንደሚሆኑ ነው የሚያምኑት። ስለዚህም የድርድሩ ጊዜ እንዲራዘም ይፈልጋሉ፤ ገበዮችን ለመክፈት የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ለማካሄድም ተጨማሪ የገንዘብ ዕርዳታ ያስፈልገናል ባዮች ናችው። ንግግሩን አክብዶት የቆየው ዋና ነጥብም ይሄው ነው። ሆኖም የአውሮፓ ሕብረት የልማት ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል ከትናንት በስቲያ እንዳሉት ሕብረቱ አዲሱን ውል ለማስፈን ቁርጠኛ ግፊት ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም። ሚሼል የሁለቱ ወገን የልማት ሚኒስትሮች ጉባዔ እዚህ ቦን ውስጥ ሲከፈት እንዳስገነዘቡት በአሕጽሮት ACP በመባል በሚታወቀው የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ ስብስብ የተጠቃለሉት ሃገራት ከአውሮፓው ሕብረት ለሚገቡ ምርቶች ገበዮቻቸውን መክፈቱን ጨርሶ መፍራት የለባቸውም።

በአንጻሩ ከዓለምአቀፉ ንግድ ጋር ራሳቸውን ከማስተሳሰር ማንገራገራቸው ስህተት ነው ሲሉ አንዳንዶቹ ሃገራትና ከመንግሥታት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች በአውሮፓ ሕብረት የለውጥ ዕቅድ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ እንደማይቀበሉ ነው የገለጹት። በቦኑ የሁለት ቀናት ጉባዔ ላይ የተሳተፉት የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስም ቢሆን ታዳጊዎቹ አገሮች እስከ ዓመቱ መጨረሻ መስፈን በሚኖርበት በአዲሱ ውል እንዲሁ ስጋት ሊያድርባችው አይገባም ባይ ናችው። ከአውሮፓ ሕብረት በኩል የሚንጸባረቀው አስተያየት የታቀደው ውል የታዳጊዎቹን ሃገራት ንግድና ልማት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለማስተሳሰር ጥሩ ዕድል ይሰጣል የሚል ነው።

ይህንኑ ሃሣብ ከሚያራምዱት አንዷ የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል የታዳጊዎቹን አጋር ሃገራት ስጋት ለማለዘብ ውሉ መበጀት-አለመበጀቱት ለማየት የሚረዳ የጊዜ ገደብ አንቀጽ በውሉ ውስጥ መካተቱን እንደ አንድ አስታራቂ ሃሣብ ሊቀበሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል። እንደርሳቸው ሁሉ ይህን መሰሉ አንቀጽ የ ACP አገሮች ውሉን ተቀብለው እንዲፈርሙ ሁኔታውን የሚያቃልል ነው የሚሉ አንዳንድ የአውሮፓው ሕብረት ዲፕሎማቶችም አልታጡም። ጥያቄው ይህ በሕብረቱ ውስጥ የብዙሃኑ ተቀባይነት አለው ወይ ነው።

የዓለም ንግድ ድርጅት የግንኙነቱ መልክ እንዲለወጥ የጊዜ ገደብ የጣለው የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሲፊክ ስብስብ ሃገራት ወደገበዮቹ ምርት እንዲያስገቡ ከሰላሣ ዓመታት በላይ ሲሰጥ የቆየውን ልዩ አስተያየት በሌሎች አገሮች ላይ አድልዎ እንደሆነ በማመልከት ለውጥ ወደማስፈለጉ ውሣኔ ከደረሰ በኋላ ነው። የግፊቱ መነሻ ይህ ሲሆን በአሕጽሮት EPA-2007 እየተባለ በሚጠራ ሕብረት የተሳሰሩ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ተቆርቋሪ ድርጅቶች የአውሮፓ ሕብረት ያቀረበውን የውል ሃሣብ በታዳጊ አገሮች ልማት ላይ ጎጂ ተጽዕኖ የሚኖረው ነው ብለውታል።

የጀርመን የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስትር በበኩላቸው የታቀደውን የንግድ ውል ለዕድገት እንዲበጅ አድርጎ ስልታዊ ከሆነ የረጅም ጊዜ ልማት ጋር ማስተሳሰሩ ጠቃሚ ነው ይላሉ። የአውሮፓ ሕብረትም ውሉን የሚፈልገው የ ACP ሃገራት የበለጠ ዕድገትና የፉክክር ብቃት እንዲያገኙ በሚያደርግ ሁኔታ የአካባቢ ገበዮቻቸውን ለመደገፍ ነው። ውሉ የሚፈረም ከሆነ በአውሮፓው ሕብረት ፍላጎት የታዳጊዎቹ ሃገራት ስብስብ ገበዮቹን ለውጭ ምርቶች ጨርሶ ለመክፈት የ 12 ዓመት መሸጋገሪያ ጊዜ ይኖረዋል። በዕቅዱ መሠረት ለነጻው ንግድ ጥርጊያው እስኪከፈት ስድሥት የአካባቢ ገበዮች ይፈጠራሉ፣ የየሃገራቱ ውስጣዊ ኤኮኖሚም ብዙ-ወጥ ሆኖ እንዲቀናጅ ይደረጋል ነው የሚባለው።

ለማንኛውም የአውሮፓ የንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሶን ትናንት እዚህ ቦን ውስጥ ከተሰበሰቡት የሕብረቱ የልማት ሚኒስትሮችና ሰላሣ ከሚሆኑ የ ACP ተጠሪዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ውሉ በተጣለለት የጊዜ ገደብ እንዲሰፍን የሚያደርጉትን የድርድር ግፊት ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። ማንደልሶን የአውሮፓ ሕብረት ታዳጊዎቹ ሃገራት አሁን በሚገኙበት የልማት እጦት ሁኔታ እንዳይቀጥሉ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበትም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ይሁንና በገበያው መከፈት፤ ያለው ለዚያውም ኋላ ቀር የሆነ የኤኮኖሚ መዋቅራችው እንዳይዳከም የሚሰጉትን ሃገራት ተጠሪዎች ማሳመን መቻላችው የሚያጠያይቅ ነው።
የአውሮፓ ሕብረት በተለይ በአፍሪቃ ቻይናን ከመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ተፎካካሪዎች በገጠመው ግፊት ውሉን በዚህም-በዚያም ለማፋጠን መነሣቱ አልቀረም። ይሁን እንጂ አጠቃላዩ ችግር ተገቢውን ማሰሪያ ሊያገኝ የሚችለው መሰናክል ገጥሞት በቆየው የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር የታዳጊ አገሮችን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ፍትሃዊ ስምምነት ዕውን ለመሆን ሲችል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በወቅቱ በቀላሉ የሚገኝ አይመስልም።

በነገራችን ላይ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ በርሊን ላይ ተካሂዶ የነበረ የአፍሪቃና የአውሮፓ መድረክ ስብሰባ በኤነርጂ መስክም በሁለቱ ክፍለ-ዓለማት መካከል ትብብሩ መጠናከሩ የሃይል አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አስገንዝቧል። ጉባዔው የአካባቢ አየር ጥበቃንና የድህነት ቅነሣንም አስፈላጊነት ያመለከተ ነበር። በሌላ በኩል በወቅቱ በልማት ትብብሩ በኩል የሚቀርበው የገንዘብ ዕርዳታ የአፍሪቃን የኤነርጂ ፍላጎት ለማሟላት የሚበቃ ሆኖ አይገኝም። የሆነው ሆኖ ክፍለ-ዓለሚቱ በተለይ በአየር ለውጥ ይበልጥ የተጎዳችው እንደመሆኗ መጠን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የተፈጥሮ አደጋን፣ የውሃ እጥረትንና እየተስፋፋ የሚሄደውን በሽታ በመቋቋሙ ረገድ እንዲረዱ ጥሪ ተደርጎላችዋል።