አንጎላ “ከሉዋንዳዉ የሰላም ዉል“ በኋላ | አፍሪቃ | DW | 09.04.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አንጎላ “ከሉዋንዳዉ የሰላም ዉል“ በኋላ

በአፍሪቃ ከተካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች መካከል አንዱ የነበረዉ የአንጎላ የእርስ በርስ ጦርነት የሉዋንዳ ስምምነት የተሰኝዉ ዉል ካበቃ 10 ኛ አመቱን ደፈነ። እአአ1978 ዓም አንጎላ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ በቀድሞዎቹ የነጻነት ታጋይ እንቅስቃሴዎች ማለትም በኤምፒኤልኤ በዩኒታ እና በ ኤፍኤንኤልኤ መካከል የእርስ በእርሱ ጦርነት ተጀመረ።

default

ሉዋንዳ

በአፍሪቃ ከተካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች መካከል አንዱ የነበረዉ የአንጎላ የእርስ በርስ ጦርነት የሉዋንዳ ስምምነት የተሰኝዉ ዉል ካበቃ ባለፈዉ ረቡዕ ሚያዝያ 4 ቀን 10 ኛ አመቱን ደፈነ። እ,አ 1978 ዓ,ም አንጎላ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ በቀድሞዎቹ የነጻነት ታጋይ እንቅስቃሴዎች ማለትም በኤምፒኤልኤ በዩኒታ እና በ ኤፍኤንኤልኤ መካከል የእርስ በእርሱ ጦርነት ተጀመረ። ይህ ጦርነት የልዋንዳ የሰላም ዉል እስከ ተፈረመበት እ,አ2002 ዓ,ም ድረስ መካሄዱ የሚዘነጋ አይደለም። በዚሁ የእርስ በርስ ጦርነት የኩባ እና የደቡብ አፍሪቃ ወታደሮችም ጣልቃ የገቡ ሲሆን የእርስ በርሱ ጦርነት በቀዝቃዛዉ ጦርነት በተቃናቃኝነት ይተያዩ ለነበሩት ለምዕራቡ እና ለምስራቁ ጉድኝትም የዉክልና ጦርነት ማራመጃ አላማ በመሆን አገልግሎአል። የሉዋንዳ የሰላም ስምምነትበተቀናቃኞቹ እንቅስቃሴዎች መካከል ከተፈረመ ወዲህ፣ በነዳጅ ዘይት ሀብትና  በሌሎች የተፈጥሮ ማዕድናት የታደለችዉ አንጎላ አስገራሚ የኢኮነሚ እድገት አስገኝታለች። ከዚሁ የአስር አመት ሰላም እና የኢኮነሚ እድገት የአንጎላ ህዝብ ተጠቃሚ ሆንዋል አልሆነም የሚለዉ ጥያቄ ብዙዎችን እያነጋገረ ሲሆን አንጎላዉያን እራሳቸዉ ይህንኑ ሂደት እንዴት ይመለከቱታል?

Rapper MCK aus Angola

የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ MCK


የአንጎላ ዜጎች ያለፉት አስር አመታት በሀገሪቱ የሰፈነዉ ሰላም ያስገኘላቸዉ ዉጤት ስለመኖር አለመኖሩ ጥያቄ በሚቀርብላቸዉ ግዜ የማይጠበቅ ቀላል መልስ እንደሚሰጡ የምጣኔ ሃብቱ ፕሮፊሰር እና የዲሞክራቲክ ቡድን በተሰኝዉ የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሪዚደንት ጁስቲኖ ፒንቶ ደአንድራዳ አስታዉቀዋል።
 
«ዛሬ ካለአንዳች ችግር በመላይቱ አገር መንቀሳቀስ እንችላለን። አንዳንድ መንገዶች እንደገና ታድሰዋል። ሌሎች አዳዲስ መንገዶችም ተሰርተዋል። የአንጎላ ዜጎች በመንገዶቻቸዉ ሊጠቀሙ ችለዋል። ይህ ቀድሞ የማይታሰብ ነበር።»  

ጁስቲኖ ፒንቶ ደአንድራዳ አክለዉ እንዳስረዱት በአሁኑ ግዜ የአንጎላ መንገዶች በጠቅላላ ያህሉ ለማለት ይቻላል በእርስ በርሱ ጦርነት ግዜ ከተቀበሩ ፈንጅዎች ነፃ ሆነዋል። የተለያዩ የፍሊክ ንቅናቄዎች በመንግስቱ አንፃር ለካቢንዳ ነፃነት ከሚታገሉበት ከካቢንዳ ግዛት በስተቀር በአሁኑ ግዜ ማንም የአንጎላ ዜጋ የተፋላሚ ሃይላት በሚያካሂዱት ዉግያ አደጋ ላይ የመዉደቅ ስጋት የለዉም። ይሁንና ከቀድሞዎቹ የነጻነት ንቅናቄዎች መካከል አንዱ የነበረዉ የዩኒታዉ ዋና ጸሃፊ አቢሉ ካማላታ ኑማ ባለፉት አስር አመታት በአገሪቱ ከሰፈነዉ ሰላም የጠበቁትን ዉጤት እንዳላገኙ ነዉ የሚናገሩት።

Angola Staatspräsident Jose Eduardo dos Santos

ፕሪዚደንት ሆዜ ኤድዋርዶ ዶሽሳንቶሽ


«ድምጽን ማሰማት የማትችልበት  ሰላም ለእኔ አይደለም። በሀገሪቱ ፍርሃት ሰፍኖአል። በህገ-መንግስታችን የተቀመጡት፣ አስተያየትን በነፃ የመሰንዘር እና የመናገር ነጻነት በተግባር ሊተረጎሙ አልቻሉም። ምክንያቱም ይህን የማይቀበል መሪ ነዉ ያለን። በዚህ ረገድ ፕሪዚደንቱ ሀገሪቱን ወደ ኋላ መልሰዋታል።»
ይህን አይነቱን ትችት የሰነዘሩት አቢሎ ካማላታ ኑማ ብቻ ሳይይሆኑ በደቡብ አንጎላ በሚገኘዉ ከቤንጉላ ግዛት የሚወለዱት ኦሙንጋ የተሰኘዉን የሲቪል ማህበረሰብ የሚመሩት ሆዜ ፓትሮቺኖም ችምር ባለፉት አስር አመታት ሂደት ደስተኛ እንዳልሆኑ ነዉ የገለጹት።    
«በፖለቲካዉ መስክ ያለመቻቻሉን ሂደት ቀጥለንበታል። ጥላቻን በልባችን ይዘናል። ዕርቀ ሰላም የማዉረዱና ከጦርነት ወደ ሰላማዊ አሰራር የሚወስደዉ የሽግግር ሂደት አልነበረም።»  
ብዙ አንጎላዉያን ከሰላሳ ሁለት አመታት በላይ ወዲህ አገሪቱን በመምራት ላይ በሚገኙት በፕሪዚደንት ሆዜ ኤድዋርዶ ዶሽሳንቶሽ አንጻር ተቃዉሞ ለማሰማት ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ አደባባይ ወተዋል። በተለይ ወጣቱ ትዉልድ እኒሁ በህዝብ ያልተመረጡት ፕሪዚደነት ሆዜ ኤድዋርዶ ዶሽሳንቶሽ ስልጣናቸዉን እንዲለቁ ጠይቆአል። እንደሚታወቀዉ በአንጎላ ፕሪዚደንቱ በህዝብ አይመረጥም። በምክርቤታዊ ምርቻ አብላቻዉን ድምጽ የሚያገኘዉ ፓርቲ ነዉ ፕሪዚደንቱን የሚሰይመዉ። ይሁንና የወጣቶቹ ጥያቄ መልስ በማግኘት ፈንታ የአገሪቱ የፀጥታ ሃይላት ተቃዉሞ ሰልፎቹን በሃይል ሲበትኑ ነዉ የታዩት።  ተቃዉሞ ሰልፎቹን ካደራጁት መካከል አንዱ የሆነዉ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኤምሲኬ የአገሪቱ መንግስት ከ2005 እስከ 2007 ዓ,ም ባሉት ግዝያት ከ 20 ከመቶ በበለጠ ኢኮነሚዊ   እድገት በማስገኘት በአለም ከፍተኛ ቦታ የያዘችዉ የአንጎላ መንግስት ህዝቡን ከነዳጅ ዘይቱ ሀብት ገቢ ተጠቃሚ አለማድረጉን አጥብቆ ነቅፎአል። 
«በአገሪቱ ከታየዉ ፈጣን የኢኮነሚ ዕድገት እራሳቸዉን ያበለፀጉ ጥቂት ሰዎች አሉ። አንድ ንዑስ ቡድን በየግዜዉ ሲበለፅግ፣ ሰፊዉ የሀገሪቱ ሕዝብ ይበልጡን ደህይቶአል። በሀገሪቱ በርግጥ ዕድገት የታየበት ንዑስ ዘርፍ የመሰረተ ልማቱ ዘርፈ ብሎም የሕንፃ ግንባታዉ ዘርፈ ነዉ።»

Hauptsitz von Sonangol in Luanda

ሉዋንዳ


ሰፊዉ የአንጎላ ህዝብ በድህነት በመሰቃየት ባለበት በአሁኑ ግዜ የፕሪዚደንት  ኤድዋርዶ ዶሽሳንቶሽ ቤተሰብ እየበለጸገ ሄድዋል። በተለይ የቀድሞ የኮሚኒስት ፓርቲ ኤምፒኤልኤ አባላት ካልጠፋ አገር በቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ፖርቱጋል ዉስጥ በርካታ ተቋማትን መግዛታቸዉ ህዝቡን እጅግ አስቆጥቶአል። የፕሪዚደንቱ ሴት ልጅ ኢዛቤላ ዶሽሳንቶሽም በፖርቱጋል ባንኮች እና የመገናኛ ተቋማት ዉስጥ በመቶ ሚሊዩን ዶላር የሚቆጠር አክስየን ባለቤት ናት። ለፕሪዚደንቱና ለቤተሰባቸዉ ሃብት መሰረት የሆነዉ፣ ወደዉጭ የሚላከዉ የነዳጅ ዘይቱ ሃብት ገቢ ነዉ። በአፍሪቃ ከናይጄርያ ቀጥላ ሁለተኛዋ የነዳጅ ዘይት አምራች አና ላኪ አገር አንጎላ፣ ከዚሁ ሃብት የምታገኘዉ ገቢ የት እንደሚዉል ግልጽ አይደለም። አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተማጋች ድርጅት Human Rights Watch እንደሚለዉ ከነዳጅ ዘይቱ ሃብት ሽያች የተገኘ 32 ሚሊያርድ ዶላር የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ጠፍቶአል። ይህ አይነቱ አሰራር በአንጎላ ቦታ እንደሌለዉ ያመለከተዉ ነዋሪነቱ በፖርቱጋል የሆነዉ አንጎላዊዉ ጋዜጠኛ ኦርላንዶ ካስትሮ በአገሩ ግዙፍና አስቸካይ ኢንቬስትመንት አስፈላጊ መሆኑን አመልክቶአል። ኦርላንዶ ካስትሮ አክሎ እንዳስረዳዉ ከነዳጅ ዘይቱ ሽያጭ የሚገኘዉ ገቢ በአገሪቱ ምርትን ለማሳደግ ወይም ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንዲሁም ትምህርትና እና ሃኪም ቤቶችን ለማስፋፋቱ አይነት ተግባር አልዋለም። እና ዛሪ ከአስር አመታት በኋላም አገሪቱ በነዚሁ ዘርፎች አኳያ ኋላ ቀር እንደሆነች ትገኛለች። በአንጎላ ድህነት ምን ያህል እንደተስፋፋ የሚያመለክቱ አስተማማኝ መዘርዝሮች ጥቂት ናቸዉ። በአጠቃላይ ሲታይ ግን ከእርስ በእርሱ ጦርነት በኋላ ድህነት በጉልህ ቀንሶአል ሊባል ይችላል። ይህም ቢሆን ግን አሁንም በአንጎላ ከየስድስቱ ህጻን አንዱ አምስት አመት ሳይሞላዉ ህይወቱ ታልፋለች። በተለይ በገጠር የሚገኘዉ ብዙዉ የሀገሪቱ ህዝብ አሁንም በከፋዉ ድህነት ዉስጥ እንደሚገኝ ነዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚያወጣቸዉ መዘርዝሮች የጠ ቆሙት። ይህ ለምን እንደሆንነ የገዥዉ ፓርቲ የኢኮነሚ ጉዳዮች ጽፈት ቤት ዋና ጸሃፊ  ኖርቤርቶ ጋርስያ ሲያስረዱ እንዲህ ነበር ያሉት፣

Mutter mit krankem Kind


«ማንበብ እና መፃፍ የማይችለዉ ሰዉ ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ እስከ ቀጠለ ድረስ ፣ የሃብቱ ክፍፍል አዳጋች ይሆናል። የመሃይማን ቁጥር በወቅቱ 35% ይደርሳል። የሀብቱ ክፍፍል በስራ በተሳካ ሁኔታ ሊከናወን ይችላል። ሰዎች በመንግስት መስሪያ ቤት ወይም በግሉ ዘርፍ በሚሰሩበት ግዜ ደምወዛቸዉን ሊያገኙ ይችላሉ። ይህም ብዙዎቻችንን የሚያጋጥመንን ችግር ሊቀንስልን ይችላል።» 

ለነገሩ አንጎላ ባላት የነዳጅ ዘይት ሃብትዋና የአልማዝ ማዕድንዋ ሌላ ቦታ መድረስ በተገባት ነበር፣ ግን የተ,መ, የልማት መስርያ ቤት ዩኤንዲፒ 187 አገሮችን አወዳድሮ ባወጣዉ መዘርዝር ላይ ከማዳጋስካር እኩል የ 148ኛዉን ቦታ ነዉ የያዘችዉ፣ ምንም እንኳ በአንጎላ የነፍስ ወከፉ ገቢ በማዳጋስካር ካለዉ በአምስት እጥፍ ቢበልጥም። የምጣኔ ሃብቱ ፕሮፊሰር ጁስቲኖ ፒንቶ ደአንድራዳ ይህ ለምን እንደሆነ ሲያስረዱ፣
«በነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ የሆንበትን አሰራር መቀነስ አለብን። ይህን ማድረጉ እስካሁን አልተሳካልንም። አሁንም ገና በነዳጅ ዘይቱ ሀብት ላይ በጣም ጥገኛ ነን»   
እንደ ጁስቲኖ ፒንቶ ደአንድራዳ አስተያየት በአንጎላ የእርስ በርሱ ጦርነት ካበቃ ዛሬ ከ10 አመታት በኋላም አንጎላ፣ ሁልት ትልቅ ፈተናዎች ተደቅነዉባታል። ማለትም ኢኮኖሚዋን ዘርፈ ብዙ ማድረግና ነፃነት እና የዲሞክራሲያዊዉን ሂደት መትከል ይጠበቅባታል።  

ዮሀንስ ቤክ/አርያም ተክሌ
መስፍን መኮንን

 

Audios and videos on the topic