አንድም ሁለትም፥ብዙም ናቸዉ። | ዓለም | DW | 31.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አንድም ሁለትም፥ብዙም ናቸዉ።

ደወሉ በርግጥ ከቱኒዝ በፊት ካይሮ ላይ ነበር ያቃጨለዉ።2006።የሰማዩ ብልጥ አበረሪ-ጀግና ተዋጊ ፥ የምድሩ ድንቅ ገዢ የሐይለኞች ጥሩ ታዛዥ ባፍታ ፀጥ አደረጉት

default

31 01 11

እርገጠኛ መሆን በርግጥ ያሳስታል።ቤን ዓሊን ተከታይ ተረኛዉ ሆስኒ ሙባረክ አይደሉም ማለት ደግሞ ጅልነት ነዉ።የቱኒዚያዉ ሕዝባዊ አመፅ የሐገሪቱን የሃያ-ሰወስት ዘመናት መሪ አሸቅንጥሮ በጣለ ማግሥት እኛም እንደ ብዙዎች ላነሳነዉ ጥያቄ ከወደ ካይሮ መልስ የሚገኝ መስለል። ካይሮን የሚገለባብጠዉ፣ አልጀርስ፣አማንን የሚያስደልቀዉ ሕዝባዊ ቁጣ ሰነዓንም እያስጓራት ነዉ።የግብፅ መሰንበቻ መነሻችን፤ የሐያሉ አለም አቋም ማጣቀሻ፣ የቱኒዝ-ካይሮ ቀዳሚ-ተከታዮች ሁለትም አንድምነት፣ የአሰላሹ-ተቀራራቢነት ግምት፣ ማጣቃሻ፣ አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ደገኛዉ ኢትዮጵያዉ እንደ ነባር ልምድ-ባሕሉ ወቃዉን ሰብል-ምርት መጠን የሚለካ-የሚያሠላበት ሰርግ የሚደግስበት ወር ባተ ጥር-ሁለት ሺሕ ሰወስት። ክርስቱያኑ ጥምቀት ሊል ነዉ።ቱኒዝ በወይራ ፍሬ አበባ ሥም በየሰየመችዉ ሕዝባዊ አመፅ እንደታመሰች ነበር።የጃሲሚን አብዮት ጎመራ።

ዘይን አል-አቢዲን ቤን ዓሊ ግን የሕዝባዊዉን ማዕበል ግፊት ሐያልነት፥ የደወሉን ድምፅ ሰቅጣጭነት አልሰሙትም።ወይም ሃያ-ሰወስት ዘመን የኖሩበት ብልጣብጥነት፥ ጉልበት፥ ሥልጣን መስሚያቸዉን ደፍኖት ነበር።(አሁንና ካሁን በሕዋላ እንደ ጎሮጎሮሳዉ እንቁጠር) ጥር አስራ አንድ ቱኒዚያን ያጥለቀለቀዉን ሕዝባዊ አመፅ ልክ ሃያ ሰወስት-ዘመን እንደለመዱት ሁሉ የወንጀለኞች ሴራ-ሻጥር አሉት።
ካይሮ ባለፈዉ ሳምንት።ሆስኒ ሙባረክ ባለፈዉ ባለፈዉ አርብ።

Ägypten Kairo Proteste Hosni Mubarak

ሙባረክ«ዛሬና ባለፉት ቀናት የተፈፀመዉ ድርጊት አብዛኛዉን የግብፅ ሕዝብ እያሰጋ ነዉ።ሥር ዓተ-አልበኝነት፥ አመፅ ጥፋቱ በጣም አሳሳቢ ነዉ።የሐገሪቱን እና የሕዝቡን ፀጥታና ደሕንነት ለማስከበር የመጀመሪያዉን ሐላፊነት የምወስደዉ እኔ ነኝ።ሕዝቡ በስጋትና ፍርሐት እንዲኖር አልፈቅድም። በፍፁም አልፈቅም።»

አልፈቀዱም።በትንሽ ግምት ዘጠና አምስት ሰዉ ተገደለ።የቱኒዝ-ግብፅ ሕዝብ ጥያቄ ፍላጎት በርግጥ ከሁለትነት ይልቅ አንድነቱ የጎላ ነበር።የጭቆናዉ ሰንሰለት-ይበጠስ፥ የሙስናዉ ክምር ይናድ፥ ችግር-ሥራ አጥነት ይወገድ ከሁሉም በላይ ገዢዎቹን በቃችሁን አይነት ጥያቄ።


ደወሉ በርግጥ ከቱኒዝ በፊት ካይሮ ላይ ነበር ያቃጨለዉ።2006።የሰማዩ ብልጥ አበረሪ-ጀግና ተዋጊ ፥ የምድሩ ድንቅ ገዢ የሐይለኞች ጥሩ ታዛዥ ባፍታ ፀጥ አደረጉት።ሁለት ሺሕ ስምንት ተደገመ። የፈርዖኖቹ ዉርስ አልተቻሉም።መሐመድ ሆስኒ ሰይድ ሙባረክ።የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የፖለቲካ እስረኛዉን ብዛት ይቆጥራሉ።ያኔ አስራ-ሰባት ሺሕ ነበር።

እስረኞችና የእስረኞች ቤተሰቦች የእስር ቤቱን ስቃይ ሰቆቃ ያወራሉ።ከንቱ ጩኸት።ሙባረክ እንደነበሩበት ከምዕራቦች በሚንቆረቆርላቸዉ የገንዘብ፥ የፖለቲካ ድጋፍ ያሸቸዉን እንዳደረጉ ቀጠሉ።እንደ ሁለት ሺሕ ስድስቱ ሁሉ የሁለት ሽሕ ስምንቱን የተቃዉሞ ሠልፍ መሩ አደራጁ ያሏቸዉን የእስላማዊ ወንድማማች ማሕበር መሪዎችን በአሸባሪነት ሥም አስቀፈድደዉ ድጋሚ አመከኑት።

የመብት ተሟጋቾች አልቦዘኑም።ግን ያዉ ቁጥር ነዉ-የሚያሰሉት።የእስረኛ ቁጥር ሰላሳ ሺሕ ደረሰ ብለዉ ነበር-ያኔ።ልክ እንደ ግብፅ ሕዝብ ጥያቄ-ጩኸት ሁሉ የሰማቸዉ የለም።እንዲያዉም ሕዳር ሁለት ሺሕ አስር በተደረገዉ የይስሙላ ምርጫ እንደ እዉነተኛ ባለድል ብቅ አሉ ሰዉዬዉ።

Flash-Galerie Ägypten Kairo Proteste

«የምርጫ ኮሚሽኑና የግብፅ ሲቢክ ማሕበረሰብ አባላት የተከታተሉት ምርጫ ነፃ እና ትክክለኛ በመሆኑ ደስተኞች ነን።መምረጥ ከሚችለዉ ሕዝብ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ በምርጫዉ መሳተፉ ተረጋግጧል።»

ለሰላሳኛ አመት ሊገዙ አሸነፉኩ-ወይም ፓርቲዬ አሸነፈ አሉ።ጥሪ-ማስጠንቀቂያዉን መስሚያ ጆሮ አልነበረባቸዉምና።

ጥር አስራ አንድ ቱኒዚያ-እና ፓሪስ

ቱኒዝ፥ ቤን ዓሊ ደወሉን ሰሙ።በትክክል ያደመጡት ግን አልመሰሉም።እራሱን እያቃጠለ፥ እየተገደለ፥ እየተደበደበ የቱኒዚያ አደባባይን ያጥለቀለቀዉን ሕዝብ ጥያቄ ለማድበስበስ ሞከሩ።ጥርም አስራ ሁለት ዓለ።

በሰወስተኛዉ ቀን ግን እብስ አሉ።አርብ ጥር አስራት።ለቱኒዚያዉያን በርግጥ ፌስታ።

አመፅ ቁጣዉን ቀድሞ የጀመረዉ የግብፅ ሕዝብ በቱኒዞች ተቀደመ።ዓለም ማነሕ ባለተራ እያለ ሲጠይቅ ግብፃዊዉ እዚያ የሆነዉ-እዚሕ የማደገምበት ምን ምክንያት አለ-ይል ገባ።

ሰዉዬዉ ግን እንቢኝ እንዳሉ ነዉ።ቤን ዓሊ በመጨረሻዉ ሰአት መጀመሪያ የወጣቶች አከታትለዉ የፀጥታ ሚንስትሮቻቸዉን እየሻሩ-እየሾሙ ማስፈራሪያ፥ ጥይት-ዱላ አፈሳ ያልበገረዉን ሕዝባዊ አመፅ ለማዳፈን እንደሞከሩ ሁሉ ሙባረክም ካቢኔያቸዉን ይጠጋግኑ ገቡ።

«መንግሥት (ካቢኔዉ) ሥልጣን እንዲለቅ አዝዣለሁ።የወቅቱን ሁኔታ በተመለከተ ቅድሚያ ሰጥቶ መፍትሔ የሚፈልግ አዲስ መንግሥት እመሰርታለሁ።»

መሠረቱ።ቤን ዓሊ ሙባረክ ሁለትም አንድምነታቸዉን ዳግም አስመከሩ።ድሮም እንዲያ ነበሩ።

ግብፃዊዉ ቆፍጣና ፓይለት፣በ1973ቱ የአረብ-እስራኤሎች ጦርነት የሐገራቸዉን አየር ሐይል በጀግንነት ለማዋጋታቸዉ ዉለታ ለአየር ሐይሉ ጠቅላይ ማርሻልነት ሲሾሙ፣የጦርነቱን ሚስጥር እያነፈነፈ ለቱኒዚያ ጦር ሲያጮልግ የነበረዉ የሐገሪቱ ወታደራዊ ደሕንነት ሐላፊ ለሙያ ብቃት ቅልጥፍናቸዉ-ሽልማት በሞስኮ የቱኒዚያ ወታደራዊ አታሼነትን ተሾሙ።

ግብፃዊዉ ፓይለት የሐያል፣ ሥልታዊ፣ ታሪካዊ፣ ትልቅ አረባዊ-አፍሪቃዊቱን ሐገር ሁለተኛ ትልቅ ሥልጣን በያዙ ሰሞን በግብፅ የዩናይትድ ስቴትሱ አምባሳደር ኸርማን ኢልትስ እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ በሌላ ቀጠሮ አሳበዉ ዘና-ቀላል እንዳሉ ከግብፁ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከኢስማኢል ፋሒሚ ቢሮ ገቡ።እያዋዙ ጠየቁ።«እኝሕ ሰዉ እንዴት ናቸዉ።»

ፋሒሚ አላመነቱም «እንደ ዋዛ እንዳታየዉ በሳዳት የተመረጡ የሳዳት ሰዉ ነዉ» መለሱ።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሜሪካኖች፥ እስራኤሎችም እንደ ዋዛ አላዩዋቸዉም። ሙባራከም ለአሜሪካኖች ታዛዥ ለእስራኤሎች ታማኝ ሸሪክ እንደሆኑ ሰላሳ-ዘመን አስቆጠሩ።አሜሪካኖች አሁንም በሙባረክ ላይ አልጨከኑባቸዉም።ከሙባረክ ሟች ስርዓት ጋር ዘላቂ ጥቅማቸዉ እንዲሞት ግን ዋሽንግተኞች አይፈቅዱም።

Proteste in Ägypten gegen Mubarak Regime gehen weiter Tahrir Square Platz Kairo«ይሕንን የግብፅን ችግር ለማስወገድ የሐይል እርምጃ መልስ አይደለም።ሥለዚሕ መንግሥት የሐይል እርምጃ ከመዉሰድ መታቀብ አለበት።አደባባይ የወጣዉ ሕዝብም ከአመፅ መጠንቀቅ አለበት። እንደሚመስለኝ ሕዝቡ ተገቢ ቅሬታዉን የሚገልፅበት መንገድ መኖር አለበት»

ድሮ፥-ሙባረክ የምክትል ፕሬዝዳንነቱን ሥልጣን በጨበጡ በሁለተኛዉ አመት የስምንት አመት ታናሻቸዉ ቱኒዚያዊዉ ብልጣብልጥ ሠላይ መኮንን የትንሺቱን ዉብ ታሪካዊ አረብ-አፍሪቃዊት ሐገር የብሔራዊ ደሕነንነት ዳይሬክተር ሆኑ።1977።
የአዉሮፕላን አብራሪ፥ የምድር ጦር አስተማሪነትን ግብፅና ሶቬት ሕብረት የተማሩት ሙባረክ ትልቁን ወንበር የሚጠቀልሉበትን ጊዜ-ሥልት ሲያዉጠነጥኑ፥ የወታደራዊ ደሕንነትን ሙያ ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስ የተማሩት ቤን ዓሊ በፖላንድ የቱኒዚያ አምባዳር ሆነዉ-ከቱኒዝ ራቁ።

ከወደ ደቡብ አረቢያ ግን ሰወስተኛ አምሳያቸዉ ድንገት ብቅ አሉ።አሊ አብደላ ሳላሕ።የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸዉን ያላጠናቀቁት የሰሜን የመኑ አስር ዓለቃ በጠንካራ ጎሳቸዉ ድጋፍ ወደ ሰነዓ ቤተ-መንግሥት ማንጋጠጥ የጀመሩ።

ሰኔ-1977 የሰሜን የመኑ ፕሬዝዳት አሕመድ ዓል ጋሺሚ ተገደሉ።አስር አለቃ ዓሊ አብደላ ሳላሕ የካይሮ፥ ቱኒዝ ታላላቆቻቸዉን ቀድሞዉ የመሪነቱን ሥልጣን ጠቀለሉ።ሐምሌ-1977።
በአራተኛዉ አመት ፕሬዝዳት አንዋር አሳዳት ተገደሉ።ሙባረክ በቅርብ የተመኙትን ቤተ-መንግሥት ተቆጣጠሩት።1981።
ፈረንሳዮች-ፈረንሳይ የተማሩ፥እንደ ፈረንሳዮች የሚያስቡትን ወጣት መኮንን የቱኒዚያን ቤተ-መንግሥት እንዲጠቀልሉ መፈለጋቸዉ አልቀረም። ግን ፈረንሳዮችን የተዋጉ፥ ሐገራቸዉን ከፈረንሳዮችን ነፃ በማዉጣታቸዉ የሚወደዱትን ፕሬዝዳት ቡርጊባን ለማስወገድ ፓሪሶች በቀጥታ ጣልቃ መግባቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ አላማ ፍላጎታቸዉን በአልጀርስ እና በሮም ወዳጆቻቸዉ በኩል ሊያስፈፅሙ አንድ ሁለት ይሉ ገቡ።

የቀድሞዉ የኢጣሊያ የወታደራዊ ደሕንነት ሐላፊ ፉልቪዮ ማርቲኒ በ1999 ሲነጋሩ «ቡርጊባ በቤን ዓሊ እንዲተኩ ከ1985 እስከ 1987 ድረስ መለስተኛ መፈንቅለ መንግሥት ብጤ አደራጅተን ነበር» አሉ።ዓሊ አብደላ ሳላሕ-የሰነዓን ቤተ-መንግሥት በተቆጣጠሩ በአስረኛዉ አመት፥ ሙባረክ የካይሮን በጠቀለሉ በስድስተኛዉ አመት ቤን አሊ ቱኒዚያ-እና ቱኒዞችን ጨምድደዉ ያዙ።1987።

የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ቤን ዓሊ ከሃያ ሰወስት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ሲያሸቀነጥራቸዉ ወደ ፈረንሳይ ወዳጆቻቸዉ ነበር የኮበለሉት።ፓሪሶች-ከሞተ ጋር ጥቅማቸዉን መግደል አልፈለጉም።ልክ እንደ ቱኒዚያ ሕዝብ ሁሉ «ዞር በል አሏቸዉ»።ሙባረክስ? ዓሊ አብደላሕስ ቡተፈሊቃ እና ሌሎችስ? ሌላ ጊዜ ለመታዘብ ያብቃን።ለዛሬዉ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ