አነጋጋሪዉ ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ባለተራ | የጋዜጦች አምድ | DW | 17.01.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

አነጋጋሪዉ ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ባለተራ

ሱዳን ለአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ብቁ አይደለችም ሲሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትናንት ገለፁ። እነዚህ ቡድኖችና ሌሎች አጋር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ እንደገለፁት የሱዳን ፕሬዝደንት ዖማር አልበሽር የህብረቱ ሊቀመንበር ሆነዉ ከተለረጡ የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የሚታዩትን ዉዝግቦች ይፈታል የሚለዉን ተዓማኒነት አጣ ማለት ነዉ።

በዳርፉር ከተፈናቀሉ ሰዎች በከፊል

በዳርፉር ከተፈናቀሉ ሰዎች በከፊል

በፊታችን ሳምንት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በሱዳን ርዕሰ ከተማ ካርቱም በሚያካሂዱት ጉባኤ ነዉ የናይጀሪያዉን ፕሬዝደንት ዖሊሴንጎን ዖባሳንጆን የሚተካ የህብረቱን ሊቀመንበር ይመርጣል ተብሎ የሚጠበቀዉ።
የአፍሪካ ዲፕሎማቶችና የፖለቲካ ተንታኞች እንደጠቆሙት በሚቀጥለዉ ሳምንት በግዛቷ የሚካሄደዉን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የመመረጫዋ አጋጣሚ ለማድረግ ሱዳን አድፍጣለች።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ዲፕሎማቲክ የዜና ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበዉ የሱዳኑ ባሺር የሊቀመንበሩነቱን ቦታ ለመያዝ በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ካዉንስል ቁልፍ ሚና ያላቸዉን የደቡብ አፍሪካዉን ፕሬዝደንት የታቦ ምቤኪን ድጋፍ በአስተማማኝ መልኩ ይዘዋል።
ሆኖም ደቡብ አፍሪካ ለባሽር ያላትን ድጋፍ የሚያረጋግጥም ሆነ የሚያስተባብል መረጃ ከመስጠት ራሷን ቆጥባለች።
ዖባሳንጆና ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች እንዲሁም 50 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ለምቤኪ በፃፉት ደብዳቤ በሺር በራሳቸዉ ግዛት በዳርፉር ሰላምን የማስፈን ሃላፊነታቸዉን ያልተወጡ እምነት የማይጣልባቸዉ ናቸዉ ሲሉ ከሰዋል።
በደብዳቤያቸዉም ከያዝነዉ የፈረንጆቹ ዓመት እስከ መጪዉ ዓመት የሚዘልቀዉን የአፍሪካ ህብረትን የሊቀመንበርነት ስልጣን ለሱዳን በተለይም ለፕሬዝደንት ኦማር አልበሺር አሳልፎ የመስጠቱ አዝማሚያ በጥልቅ እንዳሳሰባቸ ገልፀዋል።
አያይዘዉም እንዲህ ያለዉ እርምጃና ዉሳኔ አፍሪካ ህብረት ያለዉን ተዓማኒነት የሚሸረሽርና ዝቅ የሚያደርገዉ ከመሆኑም በላይ በተቋሙ ዉስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ኃላፊነቶች የሚፈታተን መጥፎ አጋጣሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህን ሃሳብ እነዚህ ወገኖች በደብዳቤ አስፍረዉ ለምቤኪ ለመላክ የወሰኑት ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ በኬንያ ርዕሰ ከተማ ናይሮቢ ካካሄዱት ስብሰባ በኋላ ነዉ።
ተንታኞች እንደሚሉት በመሠረቱ ሱዳን የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት ለመምራት ሊፈቀድላት አይገባም።
ሆኖም አፍሪካ ህብረት ስልጣኑንን ለመያዝ የሚያስችል ግልፅ የሆነ መመሪያ ስለሌለዉ በተለይ ሱዳንን ለማገድ አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም።
ለምሳሌ ሱዳን ሊቀመንበርነቱን ብትይዝ ኦባሳንጆ በሊቀመንበርነታቸዉ ዘመን የጀመሩትን የአይቮሪኮስት የሰላም ሁኔታና የዳርፉርን ግጭት የመፍታቱ ጥረት ሁሉ ትርጉም አልባ ታደርገዋለች እንደፖለቲካ ተንታኞች እምነት።
በዚያ ላይ የአፍሪካ ህብረት የቅኝት ተግባር እንዲያከናዉን ያሰማራዉ 7,000 ሰላም አስከባሪ ቡድን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በቋፍ በሆነበት ዳርፉር ይገኛል።
ሱዳን የዚህን የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ስልጣን ብትጨብጥ የታሰበዉ ሁሉ ከዚህ አንጻር ለሱዳን መንግስት እንቆቅልሽ ይሆናል።
በአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መካከል የተለመደ አንዱ በአንዱ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ማለትም ያለመገፋፈጥ አካሄድ ይታያል።
ከዚህ በመነሳትም ለአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ሱዳን ሊቀመንበርነቱን መያዝ የለባትም የሚለዉን ደፍረዉ ለመናገር ሊያዳግታቸዉ ይችላል።
መሪዎቹ እንዲህ ያለዉን ጉዳይ በለመዱት የዲፕሎማሲ ዘዴ ነዉ የሚይዙት ስለሆነም በሱዳን ያለዉን የሰብዓዊ መብቶች ችግር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግር በግልፅ ለማንሳት አይሞክሩትም ብዙዎቹ ከዚህ ችግር የጸዱ አይደሉምና።
ለሱዳን ተቃዋሚ ኃይላት መጠለያ በመስጠቷ ሳቢያ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዲቤን ለመገልበጥ ሱዳን ሙከራ ያደረገችባት ጎረቤቷ ቻድ ብቻ ናት የሱዳንን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት በይፋ መቃወሟን ያሰማችዉ።
መንግስታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች የፃፉት ደብዳቤ በሱዳን ዳርፉር የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ለሰዉ ልጅ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች አቅርቦት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በአካባቢዉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈትና ለሁለት ሚሊዮን ህዝቦች ከመኖሪያ ቀያቸዉ መፈናቀል ችግር የባሽር መንግስት በከፊል ተጠያቂ ነዉም ብለዋል። የሱዳን መንግስት ግን በተደጋጋሚ ክሱን ሲያስተባብል ቆይቷል።
ይህን መሰሉ ችግርና ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚፈፀምባት ሱዳን መንግስቷ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሆን አይገባዉም ባይ ናቸዉ።
በዘልማድ በ53ቱ አባል ሀገራት መካከል የሚሽከረከረዉ የሊቀመንበርነት ስልጣን በተራ ከሆነ አሁን ተራዉ የሱዳን ነዉ ስጋትና ተቃዉሞ ግን አጅቦታል።