አስተማማኝ ያልሆነው የማሊ ፀጥታ | አፍሪቃ | DW | 13.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አስተማማኝ ያልሆነው የማሊ ፀጥታ

የጀርመን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ ትናንት ማሊን ጎብኝተዋል። ጋውክ በዚያ ከሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡባካር ኬይታ ጋር ባንድነት በመሆን አውሮጳውያን ወታደሮች የማሊ አቻዎቻቸው ለሚጠብቃቸው ከባድ የፀጥታ ተግባር ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኙባትን የኩሊኮሮ ከተማን ጎብኝተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:45

የማሊ ፀጥታ

ጋውክ የተመድ ፀጥታው አስተማማኝ ባልሆነው በሰሜናዊ ማሊ የጀመረውን አዳጋች የሰላም ማስጠበቅ ተግባርን ለማጠናከር ባለፈው ሳምንት ወደዚሁ አካባቢ ወዳለችው የጋው ከተማ የተላኩትን የመጀመሪያዎቹን የጀርመን ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ይጎበኛሉ ብለው ብዙዎች ጠብቀው እንደነበር ተገልጾዋል።

በዚሁ የአውሮጳ ህብረት የማሰልጠን ተልዕኮ ውስጥ በርግጥ ጀርመናውያኑ ወታደሮችም ይገኙበታል። የአውሮጳ ህብረት አሰልጣኞች በዚችው ሰው በማይኖርባት የኩሊኮሮ ከተማ የማሊ ወታደሮች እንዴት አሸባሪዎችን እንዴት በቁጥጥር ማዋል እንደሚችሉ ያለማምዳሉ። መሰረታዊ ስልጠና ብቻ መስጠት እንደሚችሉ እና የስልጠናው ውጤታማነት ብዙ ሊሻሻል እንደሚችል አንድ ጀርመናዊ የብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ሻምበል ቢገልጹም፣ የማሊ ወታደሮች የመሰልጠን ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

« የወታደሮቹ መሪዎች የተራቀቀ ስልጠና ሊያገኙ የሚችሉበትን እድል እዚህ እንደሚያገኙ ስለሚያውቁ፣ እኛ የምናስተምራቸውን ለመቀበል እና በተግባር ለመተርጎም በጣም ዝግጁ ናቸው። ወታደሮቻቸውን ስልጠና አብቅታችኋል ብለው ሲያሰናብቱ ምን ሊሰማቸው ይችል ይሆን ብለን ማጠያየቃችን አልቀረም፣ ምክንያቱም፣ በዚህ ያለን የስልጠና ጊዜ በመሰረቱ በቂ አይደለም ብለን ነው የምናስበው። በሌላ በኩል፣ ወታደሮቹ ሳይሰለጥኑ እንዲሰማሩ ቢደረግ ደግሞ ውጤቱ የባሰ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አላጣነውም። »

በኩሊኮሮ የሚገኙ የጀርመናውያኑ የብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች በዚህ ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታ ነው ተልዕኳቸውን በመወጣት ላይ ያሉት። የማሊ ወታደሮች ከዘጠኝ ሳምንታት ስልጠና በኋላ ጥቃት አዘውትሮ ወደሚጣልበት እና ቀውሱ ገና ወዳላበቃበት ሰሜናዊ ማሊ ይሰማራሉ። ባለፈው ማክሰኞ እጎአ የካቲት ዘጠኝ፣ 2016 ዓም በሰሜናዊው የሀገሪቱ አካባቢ ሲጓዝ የነበረ አንድ የጦር ኃይሉ ተሽከርካሪ በመንገድ የተቀበረ ፈንጂ በነጎደበት ጥቃት ሶስት ወታደሮች መገደላቸው፣ ፅንፈኛ ሙስሊሞች በዚሁ አካባቢ ትናንት በጣሉት ሌላ ጥቃትም አንድ ወታደር እና ሁለት ሲቭሎችን መግደላቸው ተዘግቦዋል። ባጠቃላይ አካባቢው ለሲብሉ ብቻ ሳይሆን ለጦር ኃይሉም አደገኛ ነው። በዚህም የተነሳ ይኸው የማሊ የፀጥታ ሁኔታን፣ በተለይም፣ ሽብረተኝነትን የተመለከተው ርዕስ ጀርመናዊው ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ እና የማሊው አቻቸው ኢብራሂም ቡባካር ኬታ ትኩrረት ሰጥተው የመከሩበት ጉዳይ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ርዕሳነ ብሔራት የማሊ መንግሥት ካካባቢው ዓማፅያን ቡድኖች ጋር ስለተፈራረመው የሰላም ስምምነት ሂደት ሲወያዩ፣ የአደገኛው ሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ ፀጥታ ከሰላሙ ስምምነት በኋላም ያን ያህል አስተማማኝ አለመሆኑነ የማሊ ፕሬዚደንት ኬይታ አስታውቀዋል።

« የማሊ ጦር ይህንኑ አካባቢ ገና ሙሉ ለሙሉ አልተቆጣጠረም። በሰላሙ ስምምነት የተጠቀሰውን ማስከበር አለብን። የማሊ ጦርም በሰሜኑ ደረጃ በደረጃ በመጠናከር ላይ ሲሆን፣ ሂደቱን በትዕግሥት መጠበቅ አለብን። ለዓማፅያኑ እንዳይመች ሂደቱን ሳንቸኩል በጥንቃቄ ልንከታተለው ይገባል፣ በዚህም የተነሳ፣ በሰላሙ ስምምነት የሰፈረው ሀሳብ ተግባራዊ መሆን እንደሚገባው እናምናለን። ይህ ጊዜ የሚወስድ ነው። እና ስምምነቱ ሊከበር ይገባል። »

የማሊ ተቃዋሚ ቡድኖች ይህን ዓይነቱ የፕሬዚደንቱን አነጋገር የማያረጋጋ ሲሉ አጣጥለውታል። ፕሬዚደንት ኬይታ ማሊን ለማረጋጋት አቅሙም ሆነ አስፈላጊው እቅድ የላቸውም፣ በዚህ ፈንታ የቅርቦቻቸውን እና ቤተሰባቸውን ጥቅም ለማስጠበቁ ተግባር ላይ ነው ያተኮሩት በሚል የተቃዋሚ ቡድኖች እና የሀገሪ ጋዜጦች ይወቅሱዋቸዋልው። እንደሚሰማው፣ የማሊ ኤኮኖሚ እድገት አይታይበትም፣ የግብርናው ዘርፍ ደካማ ሲሆን የስራ አጡ መጠን በጣም ከፍ ያለ ነው፣ በብዛት በውጭ ኩባንያዎች የተያዘው የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍም ለሀገሪቱ እንደሚፈለገው ጥቅም አለማስገኘቱ ፕሬዚደንት ኬይታ በሚመሩት መንግሥት ፖሊሲ አንፃር ቅሬታ ፈጥሮዋል። ይሁንና፣ የጀርመን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ በማሊባደረጉት አጭሩ ቆይታቸው ስለዚችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገርም ሆነ ስለ አቻቸው ቡባከር ኬይታ፣ ወይም ስለሚቀርብባቸው ወቀሳ የራሳቸው የሆነ አስተሳሰብ የመያዝ እድል ሳያገኙ ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።

የንስ ቦርኸርስ/ አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic