አለማቀፉ የአዝማሪ ጉባኤ በጀርመን | ባህል | DW | 12.01.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

አለማቀፉ የአዝማሪ ጉባኤ በጀርመን

በጀርመን ሂልደስ ሃይም ከተማ በተዘጋጀዉ የመጀመርያዉ የአዝማሪ ጉባኤ ላይ በርካታ የአለም የሙዚቃ የታሪክ ምሁራን እና አዝማሪዎች ተገኝተዋል። በኢትዮጽያ ባህላዊ ሙዚቃ መሳርያ እና ቅላጼ አኳያ ከኢትዮጽያዉያን ይልቅ በርካታ ምዕራባዊያን በተለይ በአዝማሪዎች የሙዚቃ አጨዋወት እየሳቡ መምጣቱ እና ጥበቡን ምስጢሩን ሲያጠኑ ማየቱ የሚያስደስት ነዉ።

default

አለማቀፉ የአዝማሪ ጉባኤ በሂልደስ ሃይም ጀርመን

«በትግራይም ዋጣ ወሎ ላሊበላ፣ በጎንደር አዝማሪ የተናቀዉ ፈላ ታሪክ መርማሪዎች ተፈላሳፊዎች በኮንፈረንስ ዋሉ ማሲንቆዎቻችን፣ ጀርመን ተከበረ በኢትዮጽያ ልጆች በዜጎዎቻችን» ሲል አዚሞዋል እዉቁ አዝማሪ ደጀን ማንችሎት ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ ላይ እዚህ በጀርመን ሃኖቨር ከተማ አካባቢ በምትገኘዋ ሂልደስ ሃይም በተሰኝችዉ አነስ ያለች ከተማ በሚገኝዉ ሴንተር ፎር ዎርልድ ሙዚክ ዉስጥ በተዘጋጀዉ የመጀመርያዉ የአዝማሪ ጉባኤ ላይ። ሴንተር ወርልድ ሙዚክ የአለም የሙዚቃ ማዕከል ዉስጥ በተዘጋጀዉ የሶስት ቀን ጥናታዊ ጉባኤ ላይ ከአለም አገራት የተዉጣጡ የሙዚቃ የታሪክ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጽያዉያን አዝማሪዎችም ተገኝተዉ በሞያዉ ላይ ልዩ ትንተና ሰጥተዋል። በኢትዮጽያ ባህላዊ ሙዚቃ መሳርያ እና ቅላጼ አኳያ ከኢትዮጽያዉያን ይልቅ በርካታ ምዕራባዊያን በተለይ በአዝማሪዎች የሙዚቃ አጨዋወት እየሳቡ መምጣቱ፣ ጥበቡን እና ምስጢሩን ሲያጠኑ ማየቱ እና አዝማሪዎችን ከነሙዚቃ መሳርያቸዉ በአለም መድረኮች ለማስተዋወቅ ሲጥሩ ማየቱ የሚያስደንቅ፣ ለኢትዮጽያዉያን ደግሞ የሚያኮራና የሚያስደስት ነዉ።
በጉባኤዉ ላይ የኢትዮጽያ የመጀመርያዉ አዝማሪ የዛሪ መቶ አመት ግድም ለመጀመርያ ግዜ በጀርመን አገር ሙዚቃን ሸኽላ ማሳተሙ ዛሪ ከመቶ አመት ግድም በኋላ ደግሞ የመጀመርያዉ የአዝማሪ ጉባኤ እዚሁ ጀርመን አገር መደረጉ በጉባኤዉ ላይ የተገኙትን የሙዚቃ ጥናት አዋቂዎችንም ሆነ ባላሞያዎችን እንዲሁም እንደኔ አይነቱን የአዝማሪን ስራ ወዳጆች አስደምሞአል።

Konferenz über Azmari Kultur aus Äthiopien Universität Hildesheim

በጉባኤዉ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አዝማሪዎች ከግራ ወደ ገቀኝ ደጀን ማንችሎት እና ኢድሪስ ሃሰን

የጀርመን እና የኢትዮጽያ ባህላዊ ግንኙነት ጥንታዊነቱንም አስመስክሮአል። የዚህ ጉባኤ ዋና አዘጋጅ የሆኑት በጀርመን አገር ሃንቡርግ ዪንቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጽያ ጥናቶች ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዪ ይህ ጉባኤ እንዲካሄድ የፈለጉበት ዋና ምክንያትን ሲገልጹ
« በማስተምርበት እና በምሰራበት የአፍሪቃና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል ዉስጥ ስለ አፍሪቃ ባህል፣ ፊክሎር፣ ስነ -ጽሁፍ፣ ሙዚቃ፣ ታሪክ እናስተምራለን። በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ በደቡብ አፍሪቃ አካባቢ ያለዉ ባህላዊ ሙዚቃ በጣም የተስፋፋ እና እጅግ የሚታወቅ ነዉ። በእኛ አገር ግን የሙዚቃ ባህል በሳይንሳዊ መንገድ ያልተጠና፣ በተለይ ደግሞ ባለሞያዎች እና አዝማሪ ብለን ይህንን አለም አቀፍ ጉባኤ ያዘጋጀንላቸዉ ሰዎች ሞያቸዉ ማንነታቸዉ የማይታወቅ የማይከበር ስለሆነ ይህንን በአለም አቀፍ ደረጃ አንስተን ለምን አናጠናዉም? ለምን አንድ ጉባኤ አናዘጋጅም? የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነዉ፤ ከፕሪፊሰር ቤንደር ጋር ይህንን የጀመርነዉ።  ጀርመን አገር እ.ጎ.አ 1910 አ.ም የመጀመርያዉ የኢትዮጽያ ምናልባትም የአፍሪቃ ወይም የጥቁር ህዝቦች ሸክላ ሙዚቃ ተቀድቶአል። ይህም የሙዚቃ ሸክላ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ መሰንቆ እየተጫወቱ የተቀረጸዉ ሙዚቃ ነዉ። እናም ይህ ሸክላ ከብዙ አመታት በኋላ በፕሮፊሰር ቤንደር አማካኝነት እና በልጅ ልጃቸዉ በአቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ አማካኝነት ተገኝቶ ብዙ ታሪካዊ ጥናት ከተደረገበት ባኋላ ባለፈዉ አመት አዲስ አበባ ላይ አንድ ጉባኤ ተደርጎ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የአዝማሪ ሙዚቃ ዘፈኖች የተቀረጹበት አንድ መቶኛ አመት በሚል በጎተ ኢንስቲቱት ዉይይት አድርገን ነበር። አቶ ታደለም አዝማሪ ተሰማ እሸቴ ብለዉ አያታቸዉን አክብረዉ የመጀመርያዉ ሰዉ አድርገዉ በምሁራን መካከል መናገራቸዉ እና በዉይይቱ ላይ ማቅረባቸዉ በጣም ትልቅ ምስጋና የሚገባቸዉ ነዉ። ፕሮፊሰር ቤንደርም አብረዉ ስለነበሩ ይህንን ቀጣይነት ያለዉ ሳይንሳዊ ጉባኤ አካሂደን ባለሞያዎችን ስብስበን ለምን አንድ ጉባኤ አናዘጋጅም በሚል እንግዲህ ከሁለት አመት ጀምረን በጉዳዩ ላይ እንወያይ ነበር»
የአዝማሪ ጉባኤ አዘጋጅ የሆኑት ጀርመናዊዉ ፕሮፊሰር ዎልፍስ ጋንግ ቤንደር ስለ ጉባኤ በአጭሩ ሲገልጹ አንደኛ ደረጃ ዶክተር ገላይ በኢትዮጽያ ሙዚቃ ዙርያ የሆነ ነገር እንድንሰራ ስለጠየቀኝ ሌላዉ ይላሉ

Konferenz über Azmari Kultur aus Äthiopien Universität Hildesheim

የጉባኤዉ አዘጋጆች በስተግራ ፕሮፊሰር ዎልፍ ጋንግ ቤንደር ዶክተር ጌቲ ገላይ እና ዶክተር አንድሪያስ ቬተር


«ሌላዉ ስለ አዝማሪ ጉዳይ ምንም የሰራነዉ ሰፋ ያለ ጥናት ባለመኖሩ ስለ አዝማሪ ለመስራት አሰብኩ። ስለአዝማሪ ጥናት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ደግሞ አዉቅ ነበር። ይህን ያወኩት የተሰማ እሸቴን ታሪክ በማወቄ ነዉ። አዝማሪ በህብረተሰቡ ዘንድ የተናቀ እና ክብር ያልተሰጠዉ ሞያ መሆኑን ተገንዝቤ ነዉ። እንደ እኔ እንደ እኔ ግን አዝማሪ የተከበረ እና በህብረተሰቡ ትልቅ ትርጓሜን የያዘ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጽያ ብዙ ሚናን የሚጫወት ሞያ ነዉ። ግን በአብዛኛዉ እንዳየነዉ አንድ አዝማሪ፤ አዝማሪ በመሆኑ ብቻ የሚያፍርበት ሁኔታም አለ። ይህን ችግር ለመፍታት ነዉ ታድያ ዛሪ በችግሩ ዙርያ ለመወያየት እና ለመስራት ይህንን ጉባኤ ያዘጋጀነዉ። በኢትዮጽያም ቢሆን ስለዚህ ጉዳይ ለብዙሃኑ ለመንገር ለመመራመር እና ይህ ሞያ ምን ያህል ጠቃሚነቱን ለማሳየት ነዉ»
በጉባኤዉ ላይ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ ተካፋይ በመሆናቸዉ ጀርማናዉያኑን እጅግ አስደስቶአል፣ ኢትዮጵያዉያኑንም ቢሆኑ ኮርተዋል፣ በጉባኤዉ ላይም ስለ አያታቸዉ የአዝማሪነት ሞያ እንዲሁም ቅኔ አዋቂነታቸዉ በሰፊዉ ትንተና ሰተዋል። አቶ ታደለ ስለ አያታቸዉ ሲገልጹ « ተሰማ እሸቴ በዜማቸዉ ሲነሳ አዝማሪ ተሰማ ነዉ የሚባሉት በእኛ አገር ዘመን ያመጣዉ አርቲስት የሚባል ነገር አለ። አማረኛችን በጣም ዉብ ቋንቋ ነዉ። አዝማሪን አዝማሪ ብሎ ሲጠራዉ ከነመሰንቆዉ ከነ እንቅስቃሴዉ ከነ ግጥም ድርሰቱ እዛዉ በዝያዉ ስለሚገጥመዉ፣ ሁሉንም ነገር አጠቃሎ ነዉ። አዝማሪን አርቲስት የሚለዉ ቃል እንዴት ብሎ ነዉ የሚገልጸዉ? አርቲስት እንዴት ብሎ ነዉ ድምጻዊን የሚገልጸዉ? ከአሁን በፊትም አዲስ አበባ ጎተ ኢንስቲቱት በዚህ ጉዳይ ላይ ዉይይት ነበረን። ብዙ ሰዉ ተሰማን አዝማሪ ለምን አልክ ብሎ ተቀይሞኝ ነበር። የኔ እምነት ግን የሳቸዉም እምነት ነዉ። እራሴ የወሰድኩት ሳይሆን እራሳቸዉ ተሰማ እሸቴ በጉዳዪ ያምኑበት ነበር። በቋንቋችን የማፈር ነገር አልነበረባቸዉም። እንደዉም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ግጥም ገጥመዋል። ይህንን ሲገጥሙ ኢትዮጽያ የሙዚቃ አዳራሽ አልነበራት፥ እሳቸዉ ይህን የሙዚቃ ሸክላ በተቀዱበት ዘመን የዘመናዊ ሙዚቃ አልነበረም። ዘመናዊ ሙዚቀኞችም አልነበሩም። ጥላሁን ገሰሰ እራሱ ገና አልተወለደም። ተሰማ እሸቴ በሸክላ ከተቀዱ ከሰላሳ አራት አመት በኋላ ነዉ የአገር ፍቅር ትያትር የመጀመርያዉ የሙዚቃ አዳራሽ ማይክራፎን መጠቀም የጀመረዉ። በዝያን ግዜ ተሰማ እሸቴ በአገር ፍቅር ትያትር እንደድንገት ተገኝተዉ አንድ ግጥም ገጥመዋል “መሰንቆ በገና ዋሽንትና ክራር ከባዳነታቸዉ፣ መኮንን ሃብተወልድ አስተራረቃቸዉ” ....»

Konferenz über Azmari Kultur aus Äthiopien Universität Hildesheim

አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ


 
በአዝማሪ ስራ እና ስለ አያታቸዉ የሙዚቃ ስራ ጥናት ከጀመሩ ረዘም ያለ ግዜ በፊት እንደሆነ የገለጹልን አቶ ታደለ አያታቸዉ ጀርመን አገር መተዉ ስለተቀዱት የሙዚቃ ሸክላ ጉዳይም እንዲሁ በሰፊዉ አጫዉተዉናል።
የአዝማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ትልቅ ሚና እንዳለዉ የገለጹት እዚሁ በጀርመን በኑረንበር ከተማ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ መሪ ጌታ ዳዊት ከፍ ያለዉ እንደ አነጋገሩም ይላሉ እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና ይባላል። ዳዊት በገና ደርዳሪ ብቻ ሳይሆን መሰንቆንም በመጫወቱ አዝማሪ ነበር ሲሉ ሰፋ ያለ ትንታኔን ሰጥተዉናል።
በአዝማሪ ጉባኤ ላይ ዶክተር ጌቲ ገላይ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ እንዲሁም ሌሎች የሙዚቃ ምሁራ እና የሞያዉ ባለሞያዎች የሰጡን ልዩ ገንቢ አስተያየቶችን ይዘን ለዛሪ የተመደበል ሰአት በመጠናቀቁ ለሚቀጥለዉ ሳምንት ይዘን እንደምንቀርብ ቀጠሮ ይዘን እንሰናበታለን። በለቱ የያዝነዉን ሙሉ ቅንብር ግን ያድምጡ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ 

Audios and videos on the topic