ትምህርት አፍ በፈቱበት ቋንቋ | ባህል | DW | 19.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ትምህርት አፍ በፈቱበት ቋንቋ

መጪው እሁድ ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚታሰቢያ ዕለት ነው። ይህ ቀን ታስቦ እንዲውል ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» ባደረገው ጥናት ሰዎች አፍ በፈቱበት ቋንቋ ሲማሩ የበለጠ ትምህርቱ እንደሚገባቸው ይገልጻል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:19
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:19 ደቂቃ

ትምህርት አፍ በፈቱበት ቋንቋ

ከ 230 በላይ ቋንቋ በሚነገርበት ካሜሮን ከመጀመሪያው ዓመት አንስቶ ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዘኛ ወይም በፈረንሳይኛ ቋንቋ ነው። ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያዎቹን አመታት ልጆች አፍ በፈቱበት ቋንቋ የሚማሩበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
ምዕራብ ካሜሮን ውስጥ በምትገኝ ምቦሀ በተባለች ትንሽ መንደር እንደ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ትምህርት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሳይሆን በአካባቢው አፍ መፍቻ ቋንቋ ኮም ነው የሚሰጠው። እዛም ህፃናት መጀመሪያ በቋንቋቸው መፃፍ እና ማንበብ ይማራሉ። ትምህርት ቤት ሄደው የማያውቁ በርካታ አርሶ አደሮች በሚኖሩበት በዚሁ አካባቢ 250 000 የሚጠጉ ሰዎች ይኖራሉ። እንግሊዘኛ ብዙም የተለመደ ቋንቋ አይደለም። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ከ1ኛ ክፍል አንስቶ ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ስለነበር በርካታ ተማሪዎች በቋንቋ ምክንያት ያንን ክፍል ለመከለስ ይገደዳሉ።


ዮንግ ኬን በአካባቢው በሚገኝ የአንደኛ እና መለስተኛ ትምህርት ቤት መምህር ናቸው። መምህሯ ከዚህ በፊት በነበሩበት ት/ቤት ትምህርቱ የሚሰጠው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነበር። ትምህርት አፍ በፈቱበት ቋንቋ መሰጠት መጀመሩን መምህሯ ያወድሳሉ።« ትምህርቱ በኮም ቋንቋ ከተጀመረ ህፃናት በቀላሉ ይገባቸዋል። ምክንያቱም እቤታቸው ከወላጆቻቸው ጋር የሚግባቡበትም ቋንቋ ነው። ስለዚህ ከቋንቋቸው ጀምረን ክፍል ውስጥ ስናናግራቸው በቀላሉ ይረዳሉ።»
መምህርቷ የሚያስተምሩበት ት/ቤት በአካባቢው በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር ከጀመሩ 18 ት/ቤቶች አንዱ ነው።በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ግን ትምህርት በእንግሊዘኛ ወይም በፈረንሳይኛ ቋንቋ ብቻ ነው የሚሰጠው። ምንም እንኳን ዮንግ ኬን በሚያስተምሩበት ት/ቤት ተማሪዎቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢማሩም ከፍ ሲሉ ጥሩ ያልሆነ እንግሊዘኛ ይናገራሉ ማለት አይደለም ይላሉ መምህርቷ « እንግሊዘኛውንም ቢሆን ከሌሎቹ በተሻለ መልኩ ይረዳሉ። ምክንያቱም እንግሊዘኛ ስናስተምራቸው ወደ ኮም ቀይረን እናስተዳቸዋለን። እዚህ ት/ቤት ስናስተምራቸው የኮም ፊደልን ያውቃሉ። ጥቂት የእንግሊዘኛን ፊደላት ስናሳያቸው በቀላሉ ይገባቸዋል።»


በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠት በጀመሩት ት/ቤቶች እንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት የሚጀምረው ከ2ኛ ክፍል አንስቶ ነው። እስከዛው ህፃናቱ ኮምን ማንበብ እና መፃፍ ይማራሉ። 3ኛ ክፍልም የመማሪያ ቋንቋ ኮም ነው። ከ4ኛ ክፍል በኋላ አብዛኞቹ የትምህርት አይነቶች በእንግሊዘኛ ቋንቋ መሰጠት ይጀምራሉ። ኬን ጎድፍሬይ ቹ ከ90ቹ አንስቶ በዚህ አካባቢ በኮም ቋንቋ የትምህርት መገልገያዎችን ሲያሰባስቡ ቆይተዋል። በአሁኑ ሰዓት በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ለትምህርት አሰጣጡ የሚሆኑ መምህሮችን ይመለምላሉ። « በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚያስተምሩ ት/ቤቶችን ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በጋር ፈትነናቸው ነበር።እና በቋንቋቸው የተማሩት በእንግሊዘኛ ከተማሩት ተማሪዎች በእጥፍ ተሽለው ነው ያገኘናቸው።»
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO»ም ባደረጋቸው በርካታ ጥናቶች ሰዎች አፍ በፈቱበት ቋንቋ ሲማሩ የበለጠ ትምህርቱ እንደሚገባቸው እና ቋንቋው መሠረት እንደሆነ ያስረዳል። ምንም እንኳን የካሜሮን መንግሥት ይህንን ጅማሬ ቢያወድስም ከቃል ያለፈ ድጋፍ እንዳላገኙ ትምህርት ቤቶች ይናገራሉ። ከ200 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባት ካሜሮን ይህ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስከሚሆንም ጊዜ ይወስዳል። እንደካሜሮንም ባይሆን በርካታ ቋንቋዎች በሚነገሩበት ኢትዮጵያም ትምህርት በአካባቢው አፍ መፍቻ ቋንቋ ይሰጣል። ጥቂት ወጣቶች ተሞክሮዋቸውን አካፍለውናል። ሙሉውን ዘገባ በድምፅ ያገኛሉ።


ሂልከ ፊሸር/ ልደት አበበ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic