ትምህርትና ፍትኅ በጀርመን፤ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 25.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ትምህርትና ፍትኅ በጀርመን፤

በጀርመን ትምህርት በፍትኅ ነው የሚመራው። ይህ እንግዲህ በነባቤ ቃል የሠፈረው ነው። በተግባር እንደሚታየው ግን፤ የአካዳሚ ምሁራን የሆኑ ወላጆች የሌሉአቸው ልጆች፤ በአመዛኙ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመማር ፍላጎት አሳድረው አይወስኑም።

እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም የተመሠረተ «የሙያተኞች ልጆች» የተሰኘው ማኅበር ፤ ይዞታዎች ተለውጠው፤ በጀርመን ሀገር ማንኛውም ወጣት፤ ቤተሰቡ፣ ምንም ዓይነት የኑሮ ደረጃ ይኑረው በከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

ጀርመን ፤ በኢንዱስትሪ እጅግ የበለጸገች ሀገር ናት። ያም ሆኖ የትምህርትን ፍትኀዊነት በተመለከተ መስተካከል የሚገባቸው የሚቀሩ ጉዳዮች አሉ። ዩንቨርስቲዎች በእርግጥ ለሁሉም ክፍት ናቸው። እንደ ሁኔታው የትምህርት ቤት ክፍያ ላይኖር ይችላል። ከሆነም በጣም ዝቅተኛ ነው ። መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩም የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ፣ ከኢንዱስትሪ ሠራተኞች ልጆች፤ 25%ገደማው ብቻ ናቸው ዩንቨርስቲ ገብተው ለመማር የሚወስኑት። የአካዳሚ ትምህርት ካላቸው ቤተሰቦች፣ ደግሞ 70% የሚሆኑት ናቸው ወደ ዩንቨርስቲ ለመግባት ፍላጎቱ ያላቸው። ችግሩን ጠንቅቀው ያውቁታል ከተባሉት መካከል ወ/ሮ ካትያ ዑርባች የተሰኙት የቀድሞ የዩንቨርስቲ ተማሪ ተመክሮአቸውን እንዲህ አካፍለዋል።

«ከቤተሰቤ፤ዩንቨርስቲ ገብቼ የተማርሁ የመጀመሪያዋ እኔ ነኝ። በቤተሰብ ይህን ቀደም ሲል ያከናወነ አለመኖሩ ዩንቨርስቲ ለመግባት መወሰኑ በራሱ የቱን ያህል ከባድ መሆኑን ከተጀመረም በኃል የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች፤ እንርሱንም እንዴት መቋቋም እንደሚቻል በሚገባ ነበረ የተገነዝብሁ። ከራሴ ተመክሮ በመነሣት ፤ ከአኔ በኋላ የሚከተሉት እንዲቀልላቸው የወጠንኩት ፕሮጀክት፤ አሁን ትልቅ ሆኖ ፣ በነጻ አገልግሎት በሚሰጡ አያሌ ሰዎች በመካሄድ ላይ ነው።»

ይኸው ትልቅ ፕሮጀክት ወይም ማኅበር ፣ «የሠርቶ አደር ልጅ» ይባላል። ማኅበሩ፤ ከትምኅርት ዓለም የራቁ ቤተሰቦችን ልጆች በማነቃቃት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ያበረታታል።

በአሁኑ ጊዜ ፣ ስለትምህርት በነጻ የሚያማክሩ፣ በማስተማር የሚያግዙ ፣ በማኅበሩ ሥር የተደራጁ 80 አካባቢያዊ ቡድኖች ተቋቁመዋል። እነርሱም ፤ በት/ቤቶች፣ ወይም ቀጠሮ በመያዝ ነው ተማሪዎችን የሚያማክሩ። ከበርሊን ፣ በቤታሰባቸው የመጀመሪያው የዩንቨርስቲ ተማሪ የነበሩት፣ እስቬን ግራምእሽታት፣ የተባሉት ረዳት፤ የ«ሠርቶ አደር »ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሟቸው መሰናክሎች የትኞቹ እንደሆኑ ሲያስረዱ--

«ወላጆቼ ሊረዱኝ አልቻሉም፤ ወይም መርዳት ያቻላል ብለው አላሰቡም ነበር። መክፈል አልችልም፣ የሚለው ዓይነት አነጋገር፤ በትምህርት ፍትኅ ተግባራዊ አለመሆኑን የሚጠቁም ነው። በዚህ ሁኔታም ነው Arbeiterkind.DE ብቅ ያለው።

እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም፤ በተማሪዎች ተነሳሽነት በካትያ ዑርባች አስተባባሪነት የተጀመረው ትንሽ ቡድን አሁን ትልቅ ማኅበር ሆኖ በርሊን ውስጥ ጽ/ቤት ከፍቷል። በዚህ ላይ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው 80 የተደራጁ አካባቢያዊ ንዑስ ማኅበራትና 4,000 በነጻ አገልግሎት የሚሰጡ መምህራን አሉ። ካትያ ዑርባች፣ በቃለ-ምልልስ ማብራሪያ የሰጡት «አርባይተርኪንድ ዲ ኢ» የተባለው ማኅበር የራሱን ድረ-ገጽ በከፈተ ማግሥት ነው። ከዚያ ወዲህ ፤ ትምህርትና ፍትኅ በሚል ርእስ ብዙ ጥያቄዎች እየቀረቡላቸው፤ በቴሌቭዥንም የውይይት መድረክ እየተጋበዙ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

«እንደሚመስለኝ፣ የአካዳሚ ምሁራን ያይደሉ ቤተሰቦች ልጆች፣ወይም የአካዳሚ ትምህርት ያገኙ የመጀመሪያው ትውልድ አባላት ይዞታ፣ ከዚህ ቀደም ትኩረት ያገኘ ጉዳይ አልነበረም። ብዙዎች በዚህ ረገድ መሰናክሎች ያጋጠሟቸውም፤ እነርሱ ብቻ እንጂ ሌሎች ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው ይሆናል ብለው አያስቡም ነበር። እያንዳንዱ ይህ በእኔ ብቻ የደረሰ ችግር ነው ብሎ ነው የሚያስበው። ይሁን እንጂ በኅብረተሰቡ የአንድ ዘርፍ መሠረታዊ ችግር መሆኑ ቆይቶ ነው የተደረሰበት። በቤተሰቤ እንደ አርአያ የሚታይ፤ ሁኔታዎች እንዴት በሠመረ ሁኔታ ሊካሄዱ እንደሚችሉ፣ አስተማማኙና ትክክለኛው መንገድም የትኛው እንደሆነ የሚነግረኝ አልነበረም። »

ካትያ ዑርባችን ፣ አሁን በይበልጥ የሚያስደስታቸው፤ የሠርቶ አደሮችን ልጆች በተመለከተ፣ በትምህርት ረገድ ፍትኅ ስለመጓደሉ የተገነዘቡ የፖለቲካ ሰዎች አለመታጣታቸው ነው። አንዳንዴም ፣ ካትያ፣ ጉዳዩን በተመለከተ፣ በቀጥታ ነው የሚጠየቁት። ለተጠቀሰው የኅብረተሰብ ክፍል በተሻለ ሁኔታ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? ዑርባች፣ ወደ ክፍተኛ የትምህርት ደረጃ ለመሸጋገር ፣ ልጆች፤ ገና ከመጀመሪያው ፣ ከመዋዕለ-ህጻናትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ እጅግ ሊበረታቱ ይገባል ነው የሚሉት። በጀርመን ሀገር ፣ በነባቤ ቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር፣ ትምህርት፣ ፍትኅ ይኖርረው ዘንድ ፤ ገና ብዙ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል።

ተክሌ የኋላ

ናዲን ቦይቼክ

አርያም ተክሌ

 • ቀን 25.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/15L0z
 • ቀን 25.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/15L0z