1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ተቃዉሞ ሠልፍና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

የተቃዉሞ ሠልፍ መደረጉን፥ አንዳዶች ገዢዉ ፓርቲ ላለፉት ስምንት ዓመታት ይከተለዉ ከነበረዉ መርኹ የመለሳለሱ ምልክት ይሉታል።ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመጠናከራቸዉ ማሳያ ነዉ-ባዮችም አሉ። ሌሎች ደግሞ ቢያንስ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚደግፈዉ ሕዝብ ተቃዉሞዉን ለማሰማት ዶክተር ነጋሶ እንዳሉት የመቁረጡ አብነት ነዉ።

ደሴና ጎንደር፥ትናንት..... ተቃዋሚ ሠልኛዉ.... ከሠልፉ አደራጆች አንዱ....

«ከእነዚሕ ሠልፈኞቹ አብዛኞቹ እስላማዊ ፅንፈኞች ናቸዉ» የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዜና ወኪል።

የፖለቲካ ተንታኝ።የተቃዉሞ ሠልፉ መነሻ፥ እስከ ሠልፉ የነበረዉ ሒደት ማጣቃሸ፥ እድምታዉ መድረሻችን ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የ1997 ቱ አጠቃላይ ምርጫ የመቶዎችን ሕይወት ባጠፋ ደም አፋሳሽ ግጭት ካሳረገ ወዲሕ የሐገሪቱን መንግሥት የሚቃወም የአደባባይ ሠልፍ ሲደረግ የትናንቱ ሁለተኛዉ ነዉ። የመጀመሪያዉ ሠማያዊ ፓርቲ ያዘጋጀዉ የተቃዉሞ ሠልፍ ነበር። ባለፈዉ ግንቦት አዲስ አበባ ተደረገ።የትናንቱን ሠልፍ የጠራዉ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት ባጭሩ) ፓርቲ ነዉ።

በግንቦቱም በትናንቱም ሰልፎች የተሳተፈዉ ሕዝብ ያነሳቸዉ ጥያቄዎች ብዙ ግን ተመሳሳይ ናቸዉ።
ሕገ-መንግሥቱ ይከበር።በፀረ-ሽብር አዋጅ ወይም ደንብ ሰበብ የታሠሩ ፖለቲከኞች፥ የሐይማኖት መሪዎች እና ጋዜጠኞች ይፈቱ።የዜጎች ሠብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ።እና ሌሎችም። አንድነት እንደዚሕ አይነት አጠቃላይ ብሔራዊ ጥያቄዎችን ያዘሉ የአደባባይ ተቃዉሞ ሠልፎችን ከርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባ ይልቅ ጎንደርና ደሴ የጠራበት ምክንያት ሠልፉ ከመደረጉ እኩል እያነጋገረ ነዉ።የፓርቲዉ ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ መልስ አላቸዉ።የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳም ፓርቲያቸዉ ለሠወስት ወር የነደፈዉ የአደባባይ ተቃዉሞ ሠልፍ፥ ፊርማ የማሰባሰብ፥ እና ሕዝባዊ ሰብሰባ ማድረጉን ይቀጥላል።

እኒያ ዲሞክራሲያዊ የሚባሉት የምዕራብ ሐገራትን በርግጥ ለሰላማዊ የተቃዉሞ ሠልፍ፥ ለንንፅር መጠቅሱ አይመችም።ባለፉት ጥቂት አመታት ቱኒዚያ፥ ግብፅ፥ ቱርክ፥ ብራዚሎችም ቅሬታን፥ በአደባባይ ሕዝባዊ ሠልፍ መግለፅ-ሳይሆን አለመግለፅ እንግዳቸዉ እየሆነ ነዉ።

ለኢትዮጵያ ግን ተቃራኒዉ ነዉ-እዉነቱ።በተለይ ከ1997 ወዲሕ ሕዝብ መንግሥትን ተቃዉሞ አደባባይ መዉጣቱ አዲስ ነዉ።አዲሱ ወይም እንግዳዉ የተቃዉሞ ሠልፍ መደረጉን፥ አንዳዶች ገዢዉ ፓርቲ ላለፉት ስምንት ዓመታት ይከተለዉ ከነበረዉ መርኹ የመለሳለሱ ምልክት ይሉታል።ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመጠናከራቸዉ ማሳያ ነዉ-ባዮችም አሉ። ሌሎች ደግሞ ቢያንስ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚደግፈዉ ሕዝብ ተቃዉሞዉን ለማሰማት ዶክተር ነጋሶ እንዳሉት የመቁረጡ አብነት ነዉ።

ISS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የአፍሪቃ የፀጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሐሌሉያ ሉሌ ከሰወስቱ አንዱን ለምረጥ ዋል አደር ብለን እንየዉ ይላሉ።ይሁንና በመጠኑም ቢሆን መንግሥት ለስለስ ማለቱን መጠቆሙ አይቀርም እንደ አቶ ሐሌሉያ እምነት።

የሠብአዊ መብት ተሟጋች እና የሕግ ባለሙያ አቶ ያሬድ ሐይለ ማርያም እንደሚሉት ደግሞ የሰወስቱም ድምር ዉጤት ነዉ-ማለቱ ይሻላል።

ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሥልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሞክረናል።አንዱ ዉጪ ሐገር ናቸዉ።የተቀሩት ሥልካቸዉን አያነሱም።የመንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ትናንት በሰጡት መግለጫ ግን በትናንቱ የተቃዉሞ ሠልፍ የተሳተፉትን «አብዛኞቹ ሙስሊም አክራሪዎች ወይም ፅንፈኞች ናቸዉ።» ብለዋለዋቸዋል። በዚሕም ምክንያት አቶ ሽመልስ ከማል፥ «መንግሥት ይሕ የተቃዉሞ ሠልፍ አያሳስበዉም።እነሱ (ሠልፈኞቹ) በሕይማኖት ጉዳይ የጥያቄ የሚገቡ እና ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን ከፖለቲካ ጋር የሚቀይጡ ናቸዉ።»

መንግሥት ሰልፈኛዉና ጥያቄዉ ካላሳሰበዉ ሥለ ሠልፈኞቹ ፅንፈኝነት ለመግለፅ ያሰበበትን ምክንያት የሚያዉቁት በርግጥ አቶ ሽመልስ ብቻ ናቸዉ።ሠልፉ ግን የጎንደሩን ሠልፍ ባስተባበሩት በአቶ አሥራት ጣሴ አገላለፅ የግጭት «ኮሽታም» ያልተሰማበት-ሠላማዊ ነበር።

እስከ ሠልፉ ድረስ ፥ የአንድነት ፓርቲ በተደጋጋሚ እንዳስታወቀዉ በርካታ አባላቱ መታሰር፥ መታገት፥ መንገላታት ግድ ነበረባቸዉ።እስካሁን የታሠሩም አሉ። ሠልፈኛዉም አደባባይ እንዳይወጣ የተደረጉበትን የተለያዩ ማስፈራራቶችና እንቅፋቶችን መጋፈጥ ነበረበት።

በጫናዉ፥ በዉዝግብ፥ ዉግዘቱም መሐል ሠልፉ መደረጉ የፖለቲካ ተንታኝ ሐሌሉያ ሉሌ እንደሚያምኑት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ የመንቀሳቀሱ፥ የሩቅም ቢሆን ጥሩ ምልክት ነዉ።


የሠብአዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ሐይለ ማርያምም ተመሳሳይ ተስፋ አላቸዉ።

እና ዶክተር ነጋሶ እንዳሉት ወደፊትም ተቃዉሞን ባደባባይ መግለፁ «የፈለገዉ» ቢደርስ ይቀጥላል።
ሲሆን ለማየት ያብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌAudios and videos on the topic