ቤርጎልዮ አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ቤርጎልዮ አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት

ርዕሰነ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከአውሮፓ ክፍለ አለም ውጭ የተመረጡ የመጀመሪያው የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትና የመጀመሪያው የኢየሱሳውያን ማህበር አባል ናቸው ።

በካርዲናሎች ጉባኤ ትናንት የተመረጡት አዲሱ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ዛሬ ሮም በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ፀሎት ማድረጋቸው ተዘገበ ። አርጀንቲናዊው የቀድሞው የቡየነስ አይረስ ሊቀጳጳስ ካርዲናል ኾርኼ ማርዮ ቤርጎልዮ ከፀሎት መልስ በቫቲካኑ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ወደ 100 ሺህ ለሚጠጋ ምዕመን ቃል ምዕዳን ሰጥተዋል ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መመረጣቸው ትናንት ይፋ እንደሆነ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በፈቃዳቸው ከመንበራቸው የተነሱትን ቤኔዲክት 16ተኛን የተኩት የ76 አመቱ ቤርጎግልዮ በአምስተኛ ድምፅ አሰጣጥ እንደተመረጡ ተዘግቧል ።

ካርዲናል ቤርጎልዮ ራሳቸውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ብለው የሰየሙት ህይወቱን በሙሉ ድሆችን ሲረዳ ባሳለፈው በአሳሲው ቅዱስ ፍራንሲስ ስም ነው ። ርዕሰነ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከአውሮፓ ክፍለ አለም ውጭ የተመረጡ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመጀመሪያው የኢየሱሳውያን ማህበር አባል ናቸው ። ቤርጎልዮ ቤኔዲክት 16 ተኛ በተመረጡበት እጎአ በ2005 ቱ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሁለተኛውን ደረጃ አግኝተው ነበር ። የፍራንሲስ መመረጥ ላቲን አሜሪካውያንን አስፈንድቋል ላቲን አሜሪካ ከአለም ካቶሊኮች የ 40 በመቶው መኖሪያ ነው ። ቤርጎልዮ መመረጣቸው እንደተነገረ የበቦነስ አይረስ ነዋሪዎች የመኪና ጡሩንባ ድምፅ በማሰማት ደስታቸው ገልፀዋል ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ቤተክርስቲያኗን በድህነት ወደተቆራመደው አካባቢ የማቅረብ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ