ቡትሩስ ጋሊ | ዓለም | DW | 17.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ቡትሩስ ጋሊ

ቅብጥ ክርስቲያን-ናቸዉ።ቤተ-ሰቦቻቸዉ ክርስቲያኖች «ይጨቆናሉ» በሚባሉባት ግብፅ የናጠጡ ሐብታሞች፤እዉቅ ፖለቲከኞችና ሙሕራን ናቸዉ።---አረብ ናቸዉ-ክርስቲያን፤ ባለቤታቸዉ አረብ ግን የሁዲ።-ኋላ አጠመቋቸዉ።ግብፃዊ ናቸዉ።አረብም-አፍሪቃም።ዲፕሎማት ናቸዉ።ግን ከግድምድሞሹ አነጋገር ይልቅ እንደ ቆለኛ «አካፋን-አ-ካፋ» ማለቱን ይወዳሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:56

ቡትሩስ ጋሊ

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ በመሞታቸዉ የተለያዩ መንግሥታት እና ድርጅቶች ተጠሪዎች ሐዘናቸዉን እየገለጡ ነዉ።የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ ጋሊን «ታላቅ ግብፃዊ» እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «ታላቅ አገልጋይ» ብለዋቸዋል።የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማድሊን ኦል ብራይት ግን «ታላቅ ምሁር» በማለት አወድሰዉ «ለዉጥ አደናቃፊ» በማለት-ተችተዋቸዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ግን የዓለም አቀፉን ድርጅት ነፃነት ለማስከበር የታገሉ ነበሩ። ግብፃዊዉ ዲፕሎማት ዓለም አቀፉን ድርጅት እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1992 እስከ 1996 መርተዋል።

እንግሊዞች የእስያና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ተወላጆችን የሚጠሩበት አንድ የሥድብ ቃል አላቸዉ።የእንግሊዝ ጋዜጠኞች ደጋግመዉ ሲተቿቸዉ «አይ እኔ» ያቺን ቃል ጠሩና «ሥለሆንኩ ይሆናላ» አሉ ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ።ደሞ በተቃራኒዉ ስኮች ዉስኪ በዉሐ «ነብስ» ነዉ ይሉ ነበር።«ለምን?» ቢሏቸዉ እንግሊዞች ግብፅን ሰባ ዓመት ሲገዙ የለመድኩት ጥሩ ጣዕም እሱ ብቻ-ሥለሆነ።

ብዙ ተቃራኒዎችን አሰባጥረዉ የያዙ ናቸዉ።ከእንግዲሕ ነበሩ ነዉ የሚባል።ቅብጥ ክርስቲያን-ናቸዉ።ቤተ-ሰቦቻቸዉ ክርስቲያኖች «ይጨቆናሉ» በሚባሉባት ግብፅ የናጠጡ ሐብታሞች፤እዉቅ ፖለቲከኞችና ሙሕራን ናቸዉ።አያታቸዉ ቡትሩስ ጋሊ የግብፅ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።

እሳቸዉም ረጅም ጊዜ ምክትል ኋላ ተጠባባቂ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር።እንደ ቅኝ ግዛቱ ግንኙነት ወግ ብሪታንያ መማር ነበረባቸዉ።አላደረጉትም። ፓሪስ ተማሩ።አረብ ናቸዉ-ክርስቲያን፤ ባለቤታቸዉ አረብ ግን የሁዲ።-ኋላ ግን አጠመቋቸዉ።ግብፃዊ ናቸዉ።አረብም-አፍሪቃም።ዲፕሎማት ናቸዉ።ግን ከግድምድሞሹ አነጋገር ይልቅ እንደ ቆለኛ «አካፋን-አ-ካፋ» ማለቱን ይወዳሉ።

አዉሮጳ-አሜሪካኖች በዩጎዝላቪያዉ ጦርነት ብዙ ሰዉ ሞተ-እያሉ ሲጎተጉቷቸዉ «አፍሪቃ ዉስጥ ሥንት ምስኪን ያልቃል?» ብለዉ ጠየቁ፤ መለሱም «ይሕ የሐብታሞች ዉጊያ ነዉ» ብለዉ።አሜሪካኖች ከሶማሊያ የጦር አበጋዞች ዓሊ መሕዲን ደግፈዉ ሁሴይን አይዲድን መዉጋታቸዉን ለማቆም ሲወስኑ የአሜሪካንን መርሕ የቀየረዉ የሶማሊያ እዉነት አይደለም አሉ ቆለኛዉ ዲፕሎማት።እሕስ?«አንዱ ምስኪን አሜሪካዊ ወታደር በገሚስ ተራቁቶ ሞቃዲሾ አዉራ ጎዳና ላይ ሲጎተት መታየቱ ነዉ-በአሜሪካኖች አስተሳሰብ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረዉ።»

የመጣላቸዉን እንደመጣላቸዉ የመናገራቸዉን አባዜ ብዙዎች ቢያደንቁላቸዉም ከጥቂቶች ግን ከዓለም ዘዋሪዎች ቂም ነዉ ያተረፉት።የያኔዋ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ማድሊን ኦል ብራይት መንግሥታቸዉ አረብ-አፍሪቃዊዉን ዲፕሎማት እንደማይሻ አልሸሸጉም ነበር።«ዋና ፀሐፊዉ ታላቅ ምሁራዊና ዲፕሎማሲያዊ ክሒል አላቸዉ።እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ያደረጉት አስተዋፅኦ ግን ዉስን ነዉ።የድርጅቱን የተሐድሶ ለዉጥ ከማራመድ ይልቅ ጎታች ናቸዉ።»

ሰዉዬ ግን ከማይጋፏቸዉ ጋር መጋፋቱን አላቆሙም።በአፍሪቃና ባዉሮጳ ጦርነት ሰበብ የሚመሩት ድርጅት ሲብጠለጠል «ሐቁን እንናገር » አሉ።«ሶማሊያ፤ ሩዋንዳ፤ ይጎዝላቪያ ለተፈፀመዉ ስሕተት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጠያቂ አይደለም አላልኩም።እዉነቱን እንናገር ከተባለ ግን ሐላፊነቱን አባል ሐገራትና ድርጅቱ እኩል መጋራት አለባቸዉ።»

Boutros Boutros-Ghali

ዋሽግተኖች አልታገሷቸዉም።ለሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን እንዳይመረጡ ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣናቸዉ አገዷቸዉ።የመጀመሪያዉ አረብ-አፍሪቃዊ ዋና ፀሐፊ፤ ባንድ ዘመነ-ሥልጣን የተገደቡ የመጀመሪያዉ ዋና ፀሐፊም ሆኑ።በ1999 ባሳተሙት ማስታወሻ «የእስራኤልን መርሕ በቃወሜ፤ በኢራቅ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሉን ባለመደገፌ፤ ከሁሉም በላይ የድርጅቱን ነፃነት ለማስከበር በመታገሌ----የከፈልኩት ዋጋ» ብለዉታል።

ብዙዎቹን ምክንያቶች ያሁኑ ዋና ፀሐፊም ፓን ጊ ሙንም መሰከሩላቸዉ።«ለአባል ሐገራት ፈታኝ ጥያቄዎችን በማንሳት ፅናታቸዉን አስመስክረዋል።የቢሯቸዉን እና የባልደረቦቻቸዉን ነፃነት ለማስከበር ተገቢ ትግል አድርገዋል።»

ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ የኤርትራን ነፃነት ይደግፋሉ ተብለዉ በሚተቹ፤በሚወቀሱበት መሐል አዲስ አበባ ገቡ፤የአደባባይ ሠልፍ ጠበቃቸዉ።ከሞቃዲሾ እስከ ሳርዬቮ፤ ከኪጋሊ እስከ ባግዳድ ተቃዉሞ የተቃዉሞ ሠልፍ አልተለያቸዉም።እንኳን «ሕዝባዊ ሠልፍ» የፅንፈኞችን ተቃዉሞ ካይሮ ልምጄዋለሁ ይሉ ነበር።ካይሮ ተወለዱ፤ ድፍን ዓለም ዞሩ፤ ካይሮ ኖሩ፤ ካይሮ ሞቱ።93 ዓመታቸዉ ነበር።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic