ቡሩንዲና የአፍሪቃ ኅብረት የፀጥታ አስከባሪ | አፍሪቃ | DW | 22.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ቡሩንዲና የአፍሪቃ ኅብረት የፀጥታ አስከባሪ

የአፍሪቃ ኅብረት ወደቡሩንዲ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ ያቀረበዉ እቅድ በሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተቃዉሞ ገጠመዉ። ትናንት በጉዳዩ ላይ የመከረዉ የቡሩንዲ ምክር ቤት የኅብረቱን የሰላም አስከባሪ ኃይል «ወራሪ» በማለት ኮንኖ፤ መንግሥት ተልዕኮዉን እንዳይቀበል አሳስቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:11

ቡሩንዲ እና የአፍሪቃ ኅብረት

54 አባል ሃገራት ያሉት የአፍሪቃ ኅብረት ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ነዉ ቡሩንዲ ዉስጥ የቀጠለዉ አመፅ ተባብሶ ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዳይሸጋገር ይረዳል ያለዉን የሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ መወሰኑን ያሳወቀዉ። ለዚህ ዉሳኔዉም የቡሩንዲ መንግሥትን ይሁንታ ለማግኘት የአራት ቀናት ጊዜን ሰጥቷል። በዚህ ጊዜ ምላሽ ባያገኝም ግን የተነሳዉን አመፅ ማብረድ የሚችል 5,000 የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚልክ ነዉ የተነገረዉ። የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ቃል አቀባይ ቀደም ብለዉ መንግሥታቸዉ የኅብረቱን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆነ ተናግረዋል። የመንግሥታቸዉን ይሁንታ ሳያገኝ ኅብረቱ ጦር የሚልክ ከሆነም ወራሪ ኃይል ስለሚሆን የቡሩንዲ መንግሥት መብቱን የማስጠበቅ ርምጃ የመዉሰድ መብት እንዳለዉም አመልክተዋል። የቡሩንዲ ምክር ቤት ትናንት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ባወጣዉ መግለጫ መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በፀጥታ ማረጋጋት ስም በባዕዳን እንዳያስይዝ ተማፅኗል። «ወራሪ ኃይል» ያለዉን ሰላም አስከባሪ ጦር ለመቀበልም ከኅብረቱ ጋር መስማማት እንደማይኖርበት አሳስቧል።

Burundi Gewalt ARCHIVBILD

የቀጠለዉ አመፅ

የምክር ቤት አባል የሆኑት ሪቨሪየን ናዲኩሪዮ የኅብረቱን ዉሳኔ ደግፈዉ የሰላም አስከባሪ ወታደር ለመላክ ካቀዱ ሃገራት ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ ነዉ የጠቆሙት፤

«የዚህ ህዝብ ወኪሎች እንደመሆናችን ወደቡሩንዲ ወታደሮች ለመላክ የሚስማሙ ሃገራትን እንጎበኛለን። ምክር ቤቶቻቸዉ ቡሩንዲን ለማጥቃት ይፈልጉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን። እዚያም ቢሆን ሰዎች አለመሞታቸዉን እንጠይቃለን ምክንያቱም መሞት እና የዘር ማጥፋት ልዩነት አለዉና። አራት ሰዉ ከሞተ ዘር ማጥፋት አይደለም። ምክር ቤት ስላለዉ ወደአፍሪቃ ኅብረትም ሄደን የፓን አፍሪቃ ፓርላማ እንዴት ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር ሊተባበር እንደቻለ እንጠይቃለን።»

ቡሩንዲ ዉስጥ በተካሄደዉ ምርጫ አሸንፈዉ ምርጫዉ ተዓማኒና ሚዛናዊ አይደለም በሚል ምክር ቤት አልገባም ያሉት የብሔራዊ ምክር ቤት አንድነት ፓርቲ ተመራጭ በበኩላቸዉ ገዢዉ ፓርቲ ከተቆጣጠረዉ ምክር ቤት የሚፈፀመዉ ግድያ የዘር ማጥፋት መሆኑን ሊያምን እንደማይችል ነዉ የሚናገሩት፤

«90 በመቶዉ የምክር ቤት ተመራጭ የCNDD-FDD አባል በሆነበት ምክር ቤት እንዲህ ያለዉን ወንጀል ማጣጣል በጣም የተለመደ ነዉ። ገዢዉ ፓርቲ በወንጀሉ ኃላፊነት አለበት። ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል የሚመጣዉን የዉጭ ጣልቃ ገብነት ያለዉን ኃይል በሙሉ ተጠቅሞ ይታገላል።»

የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥትን ጥሰዉ ለሶስተኛ ዘመነ-ሥልጣን ለመመረጥ ከወሰኑ እና በሐምሌ ወርም ተመርጠዉ መልሰዉ ስልጣናቸዉን ካደላደሉ ወዲህ የሐገሪቱ ሠላም ተናግቷል።

African Union Hauptquartier in Addis Abeba

የአፍሪቃ ኅብረት

ለወራት የዘለቀዉ የጎዳና ላይ ተቃዉሞ አመፅን ከማስፋፋቱ በላይ በየምሽቱ የታጠቁ ኃይሎች ተኩስ እንደናጣት ነዉ። ዘገባዎች እንደሚሉትም በየጎዳናዎቿ የሰዎች አስከሬን በየቀኑ ይታያል። ባለፈዉ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ወታደሮች ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ሞክረዋል፤ የቡሩንዲ መንግሥት እንዲህ ላየዉ ጎረቤት ሩዋንዳን አማፅያንን በማሰልጠንና በመደገፍ ይከሳል፤ ኪጋሊ ዉድቅ ብታደርገዉም። በፀጥታ ኃይሎች እና በመንግሥት ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ከቀላል መሣሪያ አንስቶ እስከአዳፍኔ ጥቃቶች ይደርሳሉ። የቡሩንዲ ምክር ቤት አባላት ግን ሀገራቸዉ ከአጎራባች ሃገራት ያልተናነሰ ሰላም የሰፈነባት መሆኗን ነዉ የሚናገሩት። የምክር ቤቱ እና የገዢዉ CNDD FDD ፓርቲ ሊቀመንበር ፓስካል ኒይቤንዳ ችግር ካለም በዋና ከተማ ቡጁምቡራ ጥቂት አካባቢዎች ነዉ ማለታቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ጠቅሷል።

የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፉ እንደሚያሳዝናቸዉ የገለፁት የቡሩንዲ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አጋቶን ራዋሳም ቢሆኑ የሰላም አስከባሪ ወደዚያች ሀገር ይላካል መባሉን የተቀበሉት አይመስሉም፤

«ዛሬ ምንነቱ ባልታወቀ አጋጣሚ የሚገደሉ ቡሩንዲያዉያን መኖራቸዉ በጣም አሳዛኝ ነዉ። ምናልባትም ግን የከፋ ችግር ያለባቸዉ ጎረቤት ሃገራት ይኖራሉ። በአንዲት መንደር እንኳን ቢሆን ያም ችግር ነዉ። ቡሩንዲ አንድ ናት። ይህም ብሔራዊ ችግር መሆኑን መረዳት አለብን።»

ባለፈዉ ሳምንት የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙን ወደእርስበር ጦርነት ለመግባት አፋፍ ላይ ደርሷ ያሉት የቡሩንዲ ቀዉስ አካባቢዉን በመላ ሊያዳርስ እንደሚችል ስጋታቸዉን ተናግረዋል።

Burundi Gewalt und Tote

አስከሬኖች በጎዳና ላይ

አመፁን ለማረጋጋት የተመድን የሰላም አስከባሪ ኃይል የመላክ አማራጭንም አቅርበዋል። ሆኖም ዋና ፀሐፊዉ አስቀድሞ የቡሩንዲን ቀዉስ በዉይይት ለመፍታት አንድ የልዑካን ቡድን ወደዚያ እንደሚልኩም አስታዉቀዋል።

በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር የቡሩንዲ መንግሥት የአፍሪቃ ኅብረትን የሰላም አስከባሪ ኃይል አልቀበልም ያለበትን አቋም አስተካክሎ የመጨረሻ ያሉትን ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋቸዉን ገልጸዋል። እሳቸዉ እንደሚሉትም የሰላም አስከባሪ ኃይል ስምሪቱ ለሲቪሉ ኅብረተሰብ መተማመን እና ጥበቃ ይደረግልኛል የሚል ስሜትን ይፈጥራል። ቡሩንዲ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1993 እስከ 2006,ም ድረስ በእርስ በርስ ጦርነት ታምሳለች። በወቅቱም ሁቱዎች የሚበዙባቸዉ አማፅያን እና ቱትሲዎች የሚያመዝኑበት የጦር ኃይል ባካሄዱት ዉጊያ የ300,000 ሰዎችን ህይወት ፈጅቷል። ሀገሪቱ አሁንም ወደተመሳሳይ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ የሚል ስጋት አለ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic