በገና- እንደርድር | ባህል | DW | 11.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

በገና- እንደርድር

እንደ ዋልያ እና እንደ ቀበሮ የመጥፋት አዝማምያ ላይ የበረዉ ጥንታዊዉና ባህላዊ በገናችን፤ በወጣቱ ፍቅርና ጽናት እያበበ መሆኑ እየተነገረለት ነዉ።

በቤተ-መንግስት በመኳንቶች እና ሹማምንቶች ዘንድ እንደኖረ የሚነገርለት ጥንታዊዉና ባህላዊ የዜማ መሳርያ በገና፤ ተረስቶ ቆይቶ አሁን በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ተነግሮአል። በሀገራችን አሉ በሚባሉት በገና ደርዳሪዎች መካከል የበገና አባት እንደሆኑ በሚነገርላቸዉ በመጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ፤ ጽኑ የበገና ፍቅር ትዉፊቱ ሳይዳፈን እስከዛሬ መቆየቱን ወጣቱ የበገና ደርዳሪ ይመሰክርላቸዋል።

የበገና ዜማ ልብን የሚነካ፤ ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘት እራስንም ለማግኘት ጥቅም ላይ የሚዉል ምስጋና ማቅረብያ የዜማ መሳርያ ነዉ የሚሉንን ባለሞያች ይዘን ስለበገና ዜማ መሳርያ ታሪክና ምንነት በጥቂቱ እንቃኝ!

ስለ በገና ለማንሳት መንደርደርያ የሆነን ወቅቱ የፋሲካ የጾም ወራት በመሆኑ ነዉ። እዉቅ የሀገራችን ሹማምንቶች እና አገረ ገዥዎች ይጠቀሙበት ነበር። እጅግ የተከበረ፤ ትላልቅ ሰዎች ጋር የኖረም ነበር በገና ብለዉናል፤ መጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ። በአጠቃላይ ከአምስት ሽ ስምንት መቶ ዓመት እድሜ በላይም ሆኖታል።

የሰዉን ልጅ ስሜት የመግዛት ከፍተኛ ሃይል እንዳለዉ የሚነገርለት የበገና ድርድር በተለይ በጾም ወራት መደመጡ ለምን ይሆን? መጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ ፤ በጾም ወራት እንዲሰማ የሆነዉ። በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አብይ ጾም ወቅት በራድዮ ስለሚደመጥ ነበር እንጂ በገና ሁሌ የሚደመጥ ነዉ።

በገና በገዳማዉያንም ዘንድ የተወደደና የተከበረ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ። ግን ኋላ ኋላ የመጥፋት አዝማምያ ገጥት በዓለሙ አጋ የበገና ፍቅር ጽኑነት፤ ዳግም ለትንሳኤ በቅቶአል ይላል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ ስለ በገና። «በአገራችን አጼ ቴዎድሮስ በገና በመደርደራቸዉ ይታወቃሉ» በጾም ወቅትም ወደራስ የመመለሻም ግዜ ስለሆነ ነዉ።

መምህር ሲሳይ በገና ይባላሉ፤ በገናን በመስራት በማስተማራቸዉ በገና የሚል መጠርያን ማግኘታቸዉን ይናገራሉ፤ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት መምህር ሲሳይ መጀመርያ በገናን የሰሩት የዓለሙ አጋን ማስታወቅያ ተመልክተዉ መሆኑንም ነግረዉናል። ዘመኑ የበገና ሆንዋል የሚለን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤ እንደገለጸልን፤ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት በገናን አፍቃሪ በመሆኑ በገና ድርደራን እየተማረ ነዉ። በገና የመጥፋት ላይ ነበር በገና ትንሳኤ እንዲኖረዉ ያደረጉት አለሙ አጋ ናቸዉ። ለበገና ያላቸዉ ፍቅር ጽኑ በመሆኑ ነዉ። አሁን አሁን ደግሞ በሰንበት ትምህርትቤቶች፤ ማህበረቅዱሳን ፤ እንዲሁም አንዳንድ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች በገና ድርደራን በስፋት ያስተምራሉ።

በገና የዜማ መሳርያ አመጣጥ መነሻዉ ከየት ይሆን ? እንደ መጋቤ ስብሃት ዓለሙ አጋ፤ ሁለት መነሻዎች አሉት የሚል አመለካከት አለ። «አንደኛዉ በገና ብለን የምንጠራዉ እኛ ራሳችን ኢትዮጵያዉያኖች ስለሆንና፤ ኢትዮጵያ የሰዉ ልጅ መገኛ ስለሆነች በገና የራሳችን ነዉ ወደ እስራኤል ከኢትዮጵያ ተወስዶ ነዉ የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ደግሞ በገናን ይበልጥ እንዲታወቅ ያደረገዉ ቅዱስ ያሪድ በመሆኑ፤ ቅዱስ ያሪድ ደግሞ የንጉስ ሰለሞን አባት በመሆኑ እና በሰለሞን ስርወ መንግስት ግዜ አብሮ ወደ ኢትዮጵያ መጣ የሚል እምነት አለ»

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤ መገኛዉ እስራኤል ነዉ ባይ ነዉ። «ከእስራኤል ነዉ በነዳዊት ነዉ እንደዉም ዳዊት ነዉ ከፋፍሎ የበገና መዝሙር ፤ የማስንቆ መዝሙር የጽናጽል የከበሮ እያለ መዘምራኑን ለአራት በአሰማራበት ግዜ ነዉ ይበልጥ የታወቀዉ። በባቢሎን አካባቢም በገናን የሚመስሉ ምስሎች ተገኝተዋል። ከዝያ በኋላ የኦሪትን ቱፍት ስንወር አብረን ወርሰነዉ ኢትዮጵያዊ አድርገን ተጠቅመንበታል»

እንደበርካቶች እምነት በገና ደርዳሪ ወንዶች ብቻ ናቸዉ፤ ነገር ግን በገና ጾታ አይመርጥም የሚለን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመቀጠል፤« በጥንት ግዜ ሁሉ ሴት በገና ደርዳሪዎች ነበሩ፤ አሁን ም ቢሆን በገና ደርዳሪዎቹም ተማሪዎቹም በብዛት ሴቶች ናቸዉ። የጎንደርዋ እትዪ ምንትዋብም በብዛት የሚታወቁት በበገና ደርዳሪነታቸዉ ነዉ» ሌላዋ በገና ደርዳሪዎች ወንዶች ብቻ ናቸዉ የሚለዉን እምነት አልስማማበትም የምትለን የበገና ድርደራ መምህርትዋ ወ/ት ገነት አለማየሁ፤ በምታስተምርበት የበገና ድርደራ ትምህርት ቤት የዘጠኝ ወር ኮርስ እንደሚሰጥ አጫዉታናለች።

የበገና ግጥሞች ሀገራዊ ፤ሰምና ወርቅ፤ እንዲሁም ታሪካዊ በመሆናቸዉ፤ ሊጠበቁ ይገባል የሚሉን የበገና አባት መጋቤ ስብሃት አለሙ አጋ፤ በተለያዩ የአዉሮጳ ሀገሮች ተዘዋዉረዉ የበገና ድርደራቸዉን አቅርበዋል። ወደጀርመንም ብዙ ግዜ ተመላልሰዉ በተለያዩ ከተሞች ዝግጅታቸዉን አሳይተዋል። ከሁለት ወር በኋላም በኮለኝ ከተማ ከሌሎች ተማሪዎቻቸዉ ጋር በመምጣት ትልቅ ዝግጅትን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ አጫዉተዉናል። የበገና ባህላዊ የዜማ መሳርያችን ይላሉ መጋቤ ስብሃት ዓለሙ፤« በገና የመጸለያ ምስጋና የማቅረብያ እንደመሆኑ፤ በዚሁ መቀጠል አለበት እንጂ ከደንቡ ዉጭ የመጠቀሙን ሁናቴ እንዲቆም በጥብቅ መከልከል አለብን።»

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic