1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ ሣይንቲስት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 23 2009

በሕይወት ዘመን ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ነው ጀርመን ውስጥ እጅግ ታዋቂ በኾነው ተቋም ተሸላሚ የኾኑት። የተለያዩ ሀገር-በቀል ቅጠላ ቅጠሎች እና እጽዋት ላይ ምርምር በማከናወን መድኃኒቶችን ቀምመው በስማቸው አስመዝግበዋል፤ በጀርመን ሀገር ልዩ ክብር በሚሰጠው የአሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም ተሸላሚው ፕሮፌሰር።

https://p.dw.com/p/2S3Oe
Professor Tsige Gebre-Mariam
ምስል Privat

ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም

በጀርመን ሀገር ልዩ ክብር በሚሰጠው የአሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም ለሽልማት የበቁት ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ቴክኖሎጂ ክፍል በሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የጊኦርግ ፎስተር የምርምር ተሸላሚ ለመኾን አንድ አጥኚ በሕይወት ዘመኑ ስኬታማ ሥራዎችን መፈጸም ይኖርበታል። ይኽ ስኬታማ ተግባርም በተመራማሪው የሙያ ዘርፍ እና ከዚያም ባሻገር ልዩ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይገባል። ፕሮፌሰር ጽጌ ደግሞ የመድኃኒት ምርምር እና ሥነ-ቅመማ የረቀቁበት እና የተጠበቡበት ዘርፍ ነው፤ ለሽልማትም ያበቃቸው።

ሽልማቱ ከሐምሌ ጀምሮ ተዘጋጅቶ እንደነበር የተናገሩት ፕሮፌሰር እስካሁን ሽልማታቸውን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ሲያብራሩ፦ «የቤት ሥራ ነበረኝ። የምጨርሳቸው ሥራዎች አሉ። የኢትዮጵያን የሣይንስ አካዳሚ ወክዬ የባዮቴክኖሎጂ ስትራቴጂ ዕቅድ ሠነድን  እያዘጋጀን ነበር። አሁን ወደመጠናቀቁ ደርሷ» ሲሉ አንደኛውን ምክንያት ያስረዳሉ። «ሁለተኛው ደግሞ እዚህ እያስተማርኩ፣ ተማሪዎችንም እያማከርኩ ስለነበር አመቺ ጊዜ ለመወሰን ስል ነበር የቆየሁት። በእነሱ በኩል ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ዝግጁ ነበሩ» ሲሉ አክለዋል። 

«ከእነሱ ጋር ተነጋግሬ በየካቲት ወይንም መጋቢት መጀመሪያ ላይ ከሁለት አንዱ፤ ምናልባት መጋቢት ላይ ይኾናል ወደ ጀርመን እሄዳለሁ። ሽልማቱን በተመለከተ ሁሉም ነገር፤ ደብዳቤውም  ደርሶኛል። ከራሴ ጊዜ እና ከሥራ ጋር ከማመቻቸት አኳያ ነው የቆየሁት። መጋቢት ላይ በእርግጠኝነት እዛ እሄዳለሁ። እዛ ደግሞ ለተወሰኑ ወራት ምርምር ላይ እቆያለሁ» ያሉት ፕሮፌሰሩ ከሽልማቱ ሌላ ለአንድ ዓመት የሚደርስ በተለያየ ጊዜ እየተመላለሱ ከጀርመን የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ ምርምራቸውን ይቀጥላሉ።

Humboldt-Universitaet Deutschland Berlin
ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያምን የሸለመው የሁምቦልድት ዩኒቨርሲቲምስል picture alliance/blickwinkel/F. Herrmann


ፕሮፌሰር ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እጽዋት እና ቅጠላቅጠሎች መድኃኒቶችን ቀምመው ሠርተዋል። ለአብነት ያኽልም መተሬ ከሚባለው ቅጠል የሠሩት መድሃኒት ከትንሿ አንጀት እንደ ኮሦ ያሉ ሕዋሳትን  ያስወግዳል። ፕሮፌሰሩ ከእዚህ ቅጠል በእንክብል መልክ መድሃኒት አዘጋጅተዋል። ፕሉምባጎ ዛይሌኒካ ከሚባለው እጽ  ደግሞ ችፌን ለማከም የሚውል መድሃኒት ቀምመዋል። ችፌ ቆዳ ላይ ሽፍ ብሎ የሚያሳክክ ስር የሰደደ ቁስል ነው። መድሃኒቶቹ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ በማድረግ ዓለም አቀፍ ዕውቅናም በስማቸው አስመዝግበዋል። ፕሮፌሰር ጽጌ በስማቸው ያስመዘገቧቸው መድሃኒቶች እነዚህ ሁለቱ ብቻ አይደሉም።

በርካታ መድኃኒቶችንም ሀገር በቀል የሆኑ እጽዋትን በመቀመም ሠርተዋል። «ሌሎችም አሉ፤ እዚህ ሀገር ብቻ የሚገኙ እጽዋቶች አሉ። ለምሳሌ በተለምዶ የኪንታሮት በሽታ ለምንለው ቅባት ሠርተናል። ያ ቅባት ኪንታሮትን ያስታግሳል። በኪኒን ደረጃ ከማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ ጋር፣ ከእነ ፕሮፌሰር ኖይበርት ጋር በመተባበር፣ በክኒን ደረጃ ሠርተን፣ በቤተ-ሙከራ ደረጃ  የሚቆጣ የሰውነት አካልን ሊያስታግስ የሚችል ንጥረ-ነገር ከውስጣቸው አውጥተን ሠርተናል።»

ፕሮፌሰር ጽጌ የሠሩት ይኼ ብቻ አይደለም። «እንደገና ደግሞ መድኃኒት የሌላቸው፤ በተሐዋሲ ሊመጡ የሚችሉ፣ በሽታዎችን ሊያክሙ የሚችሉ ከኢትዮጵያ እጽዋት የወጡ ንጥረ-ነገሮችን አውጥተን ፈዋሽነታቸውን በቤተ-ሙከራ ደረጃ አረጋግጠናል፤ በእርግጥ ሰው ላይ አልተሞከረም። በርካታ እጽዋቶች አሉ ከእዚህ አንፃር የፈተሽናቸው» ብለዋል።

ፕሮፌሰር ጽጌ መድኃኒቶቹን የሚሠሩት ብዙውን ጊዜ ከባሕላዊ ሐኪሞች ጋር በመመካከር ነው። እንደ ጀርመን ባሉ የበለጸጉ ሃገራትም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት ያደረጉት ባሕላዊ ህክምናዎች ላይ ማተኮር ጠቃሚ እንደሆነም ገልጠዋል። ሆኖም የምርምር ውጤቶች ኅብረተሰቡ ጋር ለመድረስ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። 

«የታዳጊ ሃገራት የምርምር ውጤቶች ኅብረተሰቡ ጋር ለመድረስ የዩኒቨርሲቲ፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ያስፈልጋል። ይኼ ትስስር ጠንካራ አይደለም። እንደውም ውጪ ያሉት የመንግሥት፣ የኢንዱስትሪ፣ የምርምር ወይንም ዩኒቨርሲቲዎች ስር ያሉ የምርምር ተቋማት ትስስር  ይጠይቃል። ከዚህ አልፎ በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡም የሚካፈልበት ነው» ይላሉ። ፕሮፌሰር ጽጌ የአንድ የምርምር ውጤት ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርስ ወሳኝ ነጥቦችን ያብራራሉ። «የባሕል መድኃኒት አዋቂዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ኢንዱስትሪ እና የመንግሥት ትብብር የግድ ያስፈልጋል» ሲሉ አራቱን ወሳኝ ተቋማት ጠቅሰዋል።

Professor Tsige Gebre-Mariam
በጀርመኑ የሁምቦልድት ዩኒቨርሲቲ ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰርምስል Privat

የእነዚህ ተቋማት ትስስር በታዳጊ ሃገራት ውስጥ ጠንካራ አለመኾኑን ግን ያሰምሩበታል።  «ትስስሩ እንዲፈጠር፣ ምርምሩ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲደርስ ወደ መጨረሻ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ክፍል እንዲደርስ ይኽ ትስስር ያስፈልጋል» ሲሉ ተናግረዋል።

ትስስሩ ሲጠናከር የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ጽጌ ለምርምር የሚሰጠው በጀት በየጊዜው ሲጨምር፤ ተመራማሪዎችን ለማነቃቃት የሚሠጠው ማበረታቻ ከፍ እያለ ሲሄድ፤ ኅብረተሰቡም፣ የባሕል መድሃኒት አዋቂዎችም አንድ ላይ መመራመር ሲጀምሩ በዘርፉ ለውጥ እንደሚመጣ ያምናሉ። 

እስካሁን በመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ የሚከናወነው ምርምር በተነጣጠለ እና በተበታተነ መልኩ ነበር። በተመራማሪው ፍላጎት የሚከወነው ምርምር ከኅብረተሰቡ ጋር ሊገናኝም ላይገናኝም የሚችል ነበር። ከኢንዱስትሪዎች ጋርም ቁርኝት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል የእስከአሁኑ ሂደት። በአጠቃላይ ሥርአት አልነበረውም እንደ ፕሮፌሰር ጽጌ ገለጣ። በዚህ ኹኔታ ውስጥ ግን ፕሮፌሰር ጽጌ የግል ጥረታቸውም ታክሎበት በርካታ ስኬቶችን እና ምርምሮችን አከናውነዋል።

በመድኃኒት ቅመማ ዘርፍ ፕሮፌሰር ጽጌ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሣይንሳዊ፣ ጥልቅ፣ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸው ለኅትመት እንዲበቃም አድርገዋል። «ትምህርቴን ሁል ጊዜ በፍላጎት ነበር የምከታተለው» ያሉት ተመራማሪ ምርምሩንም የሚያከናውኑት በፍላጎት እንደሆነ ተናግረዋል። «በግዴታ የሰራሁበት ጊዜ የለም። በአጋጣሚ ሆኖ ፍላጎቱ አድሮብኝ እዚህ ደረጃ ደርሻለሁ። ወጣቱም አጭር መንገድ ሳይሆን የወደፊቱን በማለም ተግቶ ከሠራ የላቀ ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል። ይኼ እንዲሁ ምሳሌ ይኾን እንደሆን እንጂ  ከእዚህ በላይ ወጣቱ የመሄድ ዕድል አለው። ዛሬ የኢንተርኔት ዘመን ነው። ዓለም በአጽናፋዊነት ትስስር ስር የምትገኝበት ዘመን በመሆኑ፣ ወጣቱ የተሻለ ዕድል ስላለው እኔ ከደረስኩበት በብዙ  ልቆ መሄድ ይችላል።»

Hauptgebäude der Humboldt Universität in Berlin
ጀርመን የሚገኘው የሁምቦልድት ዩኒቨርሲቲምስል picture-alliance/dpa

በእርግጥም ወጣቱ ተዝቆ የማያልቅ ዕውቀት የኢንተርኔሩ ዓለም ውስጥ ይጠብቀዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይኽ ግንዛቤ የተሰጠው አይመስልም። በየአጋጣሚው የኢንተርኔት መቋረጥ እና መዘጋት ወጣቱን በቀላሉ ሊያገኘው ከሚችለው የዕውቀት አምባ መገደብ ነው።
 
ፕሮፌሰር ጽጌ ዕወቃታቸውን ያለገደብ በመስጠት ለከፍተኛ ደረጃ ያደረሷቸው ተመራማሪዎች ቁጥር በርካታ ናቸው። ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ማለትም ለማስትሬት ዲግሪ የሚያጠኑ ከ100 በላይ ተማሪዎችን እንዳማከሩ ፕሮፌሰር ጽጌ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ ግን ዛሬም ይኽን ዝግጅት በምናቀናብርበት ወቅት ፕሮፌሰር ጽጌ ከ40 በላይ ተማሪዎችን አማክረዋል የሚል ጽሑፍ ነው ያሰፈረው። በዚህ አጋጣሚ ዩኒቨርሲቲው የምርምር እና የጥናት ማዕከል እንደመሆኑ መጠን መረጃዎቹን እየተከታታለ ለውጥ ሲኖር በተቀላጠፈ መልኩ ወቅታዊ ቢያደርጋቸው መልካም ነው። 

ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር በአሁኑ ወቅት አንድ ጀርመናዊን ጨምሮ ወደ አምስት የሚጠጉ ተማሪዎችን ደግሞ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው እያማከሩ ነው። ጀርመናዊው በፕሮፌሰር ጽጌ ስር ኾኖ ለዶክትሬቱ የሚያጠናው በተለያየ ምክንያት የቆዳ መሸብሸብን ለመከላከል የሚያስችል መድሃኒት ለማግኘት ነው። በፕሮፌሰር ጽጌ ስር የሚገኘው ጀርመናዊ ጥናቱን የሚያከናውነው በኢትዮጵያ እጽዋት ላይ ነው። 
 
ከዚያ ባሻገር እስካሁን ፕሮፌሰር ጽጌ ለዶክትሬት ጥናት ወደ ጀርመን ሀገር ከተላኩ ተማሪዎች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑትን ያማክሩ እንደነበረም ተናግረዋል። ተማሪዎችን ከማነጹ ባሻገር በርካታ እጽዋት እና ቅጠላ ቅጠሎችን ለመድሃኒትነት ያበቁት ፕሮፌሰር ጽጌ ወደፊት የልፋታቸው ውጤት በስፋት ተመርቶ ለኅብረተሰቡ እንደሚደርስ ተስፋ ሰንቀዋል። በጀርመን ሀገር በዘመናዊ መልክ ገበያ ላይ የሚገኙ መድኃኒቶች 40 ከመቶ ያኽሎቹ ከእጽዋት የሚገኙ ናቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ ለመድሃኒት አገልግሎት ሊውሉ በሚችሉ ዕጽዋት እና ቅጠላቅሎች የታደለች ናት። እናም ሥነ-ቅመማ እና የመድኃኒት ግኝት ምርምር በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት ከሚያሻቸው ዘርፎች አንዱ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ