1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

በዓለም የረሀብ ደረጃ መዘርዝር

በመላዉ ዓለም ረሀብን ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት አዎንታዊ ርምጃን እያሳየ መሆኑን ዛሬ ይፋ የሆነዉ የዓለም የረሀብ ደረጃ መዘርዝር አመልክቷል። መዘርዝሩ በተለይ በአዳጊ ሃገራት የነበረዉ የረሀብ ሁኔታ 29 በመቶ መቀነሱን ቢጠቅስም፤ አሁንም ግን የረሀብ ደረጃዉ አሳሳቢ የሆነባቸዉ ሃገራት መኖራቸዉን ግልፅ አድርጓል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:38

የርሃብ መዘርዝር

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም አንስቶ በመላዉ ዓለም ረሀብን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረዉ እንቅስቃሴ ዉጤት አሳይቷል ቢባልም አሁንም ጥቂት በማይባሉ አዳጊ ሃገራት ዉስጥ ሁኔታዉ አሳሳቢ ወይም እጅግ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ። መዘርዝሩን የጠቀሱ ዘገባዎች እንደሚሉት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ፤ ቻድ እና ዛምቢያን ጨምሮ ሰባት ሃገራት ዉስጥ ያለዉ የረሀብ ሁኔታ አስጊ መሆኑ ተገልጿል። ሕንድ፣ ናይጀሪያ እና ኢንዶኔዥያን ጨምሮ ሌሎች 43 ሃገራት ደግሞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል። ከዓለም ከረሀብ ለመላቀቅ በምታደርገዉ ትግል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኘዉ የጀርመኑ ግብረ ሠናይ ድርጅት ቬልት ሁንገር ሂልፈ፤ የምግብ ዘርፍ ተጠሪ አንድሪያ ዞንታግ፤ መሥሪያ ቤታቸዉ ዛሬ በርሊን ላይ ይፋ ያደረገዉን የመዘርዝሩን ይዘት እንዲህ ገልጸዉልናል።

«በዓለም የርሃብ መዘርዝሩ ርሃብን ለማጥፋት የተደረገዉን ጥረት በማሳየት፤ አካባቢዉም ሆነ መንግሥታት በቀጣይ ሊያደርጉት የሚገባዉን ለማመላከት ነዉ። በዚህ ዓመት ካለፈዉ ይልቅ ርሃብን በመዋጋቱ አዎንታዊ ርምጃዎች ተደርገዋል። ከ16 ዓመታት ወዲህም በአዳጊ ሃገራት ርሃብን ለመዋጋት በተደረገዉ ጥረት ወደ 30 በመቶ እንዲቀነስ ማድረግ ተችሏል። 20 የሚሆኑ ሃገራት የሚገኙበትን ደረጃ በተጨማሪ ማሻሻል ችለዋል። እንዲያም ሆኖ አሁንም በ50 ሃገራት የርሃቡ ሁኔታ አሳሳቢ ወይም እጅግ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ ነዉ። ከእነዚህ ሃገራት አብዛኛዎቹ ደግሞ አፍሪቃ ዉስጥ ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙ ናቸዉ። ኢትዮጵያም በዚህ ዓመት ከእነዚህ ርሃቡ አሳሳቢ ከሆነባቸዉ ሃገራት ዉስጥ ትገኛለች።»

ከዚህ በፊት የከፋ የርሃብ ሁኔታ እንደነበረባቸዉ ከተመዘገበ ሃገራት መካከል አሁን ተሻሽለዉ የተገኙ ሃገራት መኖራቸዉ የዚህ ዓመቱ የዓለም የረሃብ ደረጃ መዘርዝር ካካተታቸዉ አዲስ ጉዳዮች ዋነኛዉ መሆኑን ነዉ አንድሪያ ዞንታግ የሚያስረዱት።

«እጅግ አሳሳቢ የርሃብ ይዞታ ከታየባቸዉ መካከል እንደ ሩዋንዳ፣ ካምቦዲያ እና ማይንማር ያሉት  ሃገራት ከፍተኛ የተባለዉ የመሻሻል ደረጃ ላይ ደርሰዋል። እነዚህ ሃገራት በጠንካራ ርሃብ የተጎዱ ቢሆኑም ያን ማሻሻል እንደሚቻል ያሳዩ ናቸዉ። ሌሎች ሦስት ሃገራትም እንደነሱ ወደተሻለ ደረጃ ለመምጣት ቀስ በቀስ እየጣሩ መሆናቸዉ ታይቷል።»

ዞንታግ እንደሚሉት በዚህ ዓመቱ መዘርዝር የ13 ሃገራት መረጃ ሊካተት አልቻለም። ከሃገራት መካከል ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ እንዲሁም ሶርያን ጠቅሰዋል። ይህም ቢሆን በተለይ የ10ሩ ሃገራት ይዞታ አሳሳቢ እንደሚሆን ይገመታል። በዘገባዉ ከዚህ በፊት የታየባቸዉ የርሃብ ይዞታ እንደተሻሻለ ከተነገረላቸዉ ሃገራት አንዷ አፍሪቃዊቱ ሃገር ሩዋንዳ አንዷ ናት። ለዚህ ደረጃ ያበቃት ምን እንደሆነ ዞንታግ እንደሚከተለዉ ያብራራሉ፤

«ሃገራቱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ በትክክል ሠርተዋል። በዚያ ላይ ደግሞ የልጆች እና ሴቶች የአመጋገብ ሥርዓትን የሚያሻሽል ስልት ቀይሰዋል። ርሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተለያዩ ምክንያቶች የሚያመጧቸዉ የተወሳሰቡ ነገሮች እንደመሆናቸዉ፤ በአንድ በኩል የምግብ ወይም የበቂ ምግብ አቅርቦት ጉዳይ፤ በዚያ ላይ የመጠጥ ዉኃ አቅርቦት እና የንጽሕና መጠበቂያ ስልት፤ በዚያም ላይ በሃገራቱ የሕፃናት ሞት እንዲቀንስ የጤና አገልግሎት አቅርቦትም ሆነ ሰዎች ራሳቸዉንም ሆነ ቤተሰባቸዉን መመገብ እንዲችሉ የተሻለ የገቢ መጠን እንዲኖራቸዉ ማድረግ ችለዋል።»

ጎርጎሪዮሳዊዉ ዓመት 2016 ኢትዮጵያን ጨምሮ በርከት ያሉ የአፍሪቃ ሃገራት የኤሊኒኞ ክስተት ባስከተለዉ የአየር ጠባይ ለዉጥ ምክንያት ለምግብ እጥረት እና ርሃብ የተጋለጡበት ዓመት ነዉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ በተጠቀሰዉ ጊዜ የገጠማት ባለፉት 50 ዓመታት ዉስጥ ያልታየ ነዉ። ሕፃናት አድን የተሰኘዉ ድርጅት ከሦስት ወራት በፊት ባወጣዉ ዘገባ በኤሊኒኞ መዘዝ ለድርቅ በተጋለጠዉ የአፍሪቃ ክፍል 26,5 ሚሊየን ሕፃናት ለተመጣጠነ የምግብ እና ዉኃ እጥረት መጋለጣቸዉን አመልክቷል። የተመድ በበኩሉ በምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ በሚገኙ ሃገራት በጥቅሉ ወደ 40 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ በቂ ምግብ እንደሌለዉ ገልጿል። ዛሬ ይፋ የሆነዉ የዓለም የርሃብ ደረጃ መዘርዝር በኢትዮጵያ የርሃቡ ይዞታ አሳሳቢ እንደሆነ ነዉ ያመለከተዉ። አንድሪያ ዞንታግ፤

«ኢትዮጵያ ዉስጥ የርሃቡ ይዞታ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል፤ ደረጃም ወደ እጅግ አሳሳቢ ከፍ ብሏል። ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከተቃኙት 118 ሃገራት 107ኛ ደረጃ ላይ ናት። ከሕዝቧ አንድ ሶስተኛ የሚሆነዉ በቂ ምግብ አያገኝም፤ ይም ማለት ከምግብ ከሚገኘዉ የኃይል መጠን በጣም ትንሽ ካሎሪ ነዉ የሚያገኘዉ። ከአምስት ዓመት እድሜ በታች ከሚገኙ ከ10 ልጆች አምስቱ ለዕድገት የሚያስፈልጋቸዉን በቂ ምግብ አያገኙም። ከሕፃናቱም ባጠቃላይ 9 በመቶ የሚሆኑት ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት የተጋለጡ ናቸዉ። እንዲያም ሆኖ ግን የዘንድሮዉ መዘርዝር ኢትዮጵያ ርሃብን ለመዋጋት በምታደርገዉ ጥረት አዎንታዊ ርምጃዎችን ማድረጓን ያሳያል። ከዛሬ 16 ዓመት አንስቶም በመላዉ ዓለም የርሃብ ደረጃዉ 40 በመቶ እንዲቀነስ ማድረግ ተችሏል። ምሥራቅ አፍሪቃን ስንመለከት ኢትዮጵያ ከማዳጋስካር እና ዛምቢያ የተሻለች ብትሆንም ከሌሎች ሃገራት ማለትም እንደ ሞዛምቢክ፤ ዚምባብዌ፣ ሩዋንዳ፣ ማላዊ፣ ኬንያና ዩጋንዳ ጋር ስትነጻጸር ግን ወደ ኋላ ትቀራለች።»

አክለዉም ዞንታግ ኢትዮጵያ ርሃብን ለመቀነስ በሚደረገዉ ጥረት ፍጥነት ካልጨመረች በጎርጎሪዮሳዊዉ 2030ዓ,ም ዓለም እንድትደርስበት ከታለመዉ እና ኢትዮጵያ ራሷም ከፈረመችዉ የዚህ ዘርፍ ግብ መድረስ እንደሚሳናት ጠቁመዋል። መዘርዝሩ እንደጠቆመዉ በመላዉ ዓለም 795 ሚሊየን ሕዝብ የተመጣጠነ ምግብ አያገኝም። ይህ ደግሞ ላለፉት አራት ዓመታት ምንም አልተለወጠም። የከፋ የምግብ አቅርቦት በሚታይባቸዉ ሃገራት መሠረታዊ የችግሩ ምክንያቶች ጦርነት፤ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የአየር ንብረት ለዉጥ ናቸዉ። በአንዳንድ ያደጉ ሃገራትም የግብርና ፖሊሲዉ እንቅፋት መሆኑን ተጠቅሷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

 

Audios and videos on the topic