በኢትዮጵያ ድንበር ስድስት ኬንያውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ | አፍሪቃ | DW | 27.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በኢትዮጵያ ድንበር ስድስት ኬንያውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ

በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር የሚገኙ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት የወረዳ ፖሊስ አዛዥ እና አስተዳዳሪን ጨምሮ ስድስት ኬንያውያንን “በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል” በሚል በቁጥጥር ስር አዋሉ፡፡ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኬንያውያኑን ለእስር ያበቃቸውን መነሻ እያጣሩ እንደሆነ ነገር ግን ታሳሪዎቹ እንደሚለቀቁ ገልጸዋል፡፡

ከታሰሩት ኬንያውን አምስቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው እሁድ እንደሆነ የማርሳቤት አውራጃ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ማክ ዋንጄላ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር የምትጋራው የኤልሬት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ሳሙኤል ናልያኛ እና የወረዳዋን አስተዳዳሪ ያካተተው የኬንያውያን ጓድ የኢትዮጵያን ድንበር የተሻገረው ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለ ኬንያዊ ተጠባባቂ የፖሊስ አባልን ለማስፈታት በሚል እንደነበር የፖሊስ መኮንኑ ያስረዳሉ፡፡

“ወደእዚያ የሄዱት የብሄራዊ ተጠባባቂ ፖሊስ አባልን ለመርዳት በሚል ነበር፡፡ እንደተረዳሁት እዚያ ሲደርሱ እንደታጠቃችሁ ወደሀገራችን በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል በሚል የኢትዮጵያ የኢሚግሬሽን ሰዎች አስረዋቸዋል፡፡”

ተጣባባቂ የፖሊስ አባሉ ሳሊም ካላ የታሰረው ባለፈው አርብ ኢትዮጵያን እና ኬንያን በሚያዋስነው ቱርካና ሀይቅ ላይ አሳ እያሰገረ በነበረበት ወቅት እንደነበር ማክ ዋንጄላ ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ወገን በሚገኘው የሀይቁ አካል ላይ “በህገወጥ መንገድ አሳ ሲያሰግር ተገኝቷል” በሚል ለእስር እንደበቃም ያብራራሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መነሻውን እንደማያውቁ እና እያጣሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሁነቱ ዲፕሎማሲያዊ ችግር ሳይፈጥር ቶሎ እልባት እንደሚያገኝም ያስረዳሉ፡፡

“መነሻውን አላወቅንም፡፡ እያጣራሁት ነው፡፡ የሆነ ነገር ነው ግን አሁን ጨርሰነዋል፡፡ ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ችግር እንዳይፈጥር በሚል ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡ [ፍቺያቸው] በሂደት ላይ ነው፡፡ እዚህ ካለውም ውጭ ጉዳይ ጋርም ተነጋግረን፣ አዲስ አበባም ከመንግስት ጋር ተነጋግረን እልባት እያገኘ ነው” ሲሉ ኬንያውያኑ በቅርቡ እንደሚፈቱ አምባሳደሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ስድስቱ ኬንያውን እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ አለመፈታታቸውን የፖሊስ መኮንኑ ይናገራሉ፡፡ ጉዳያቸውም ከፖሊስ ተሻግሮ በሀገሪቱ “ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተይዟል” ይላሉ፡፡ “ጉዳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲፈታው ወደዚያው ተመርቷል” ሲሉ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በየጊዜው በድንበር ግጭት የሚቆራቆሱ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ገብተው ጥቃት እንደሚያደርሱ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኃይሎች በአካባቢው ተሸሽገው ጥቃት ይፈጽሙብናል የሚሏቸውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂ ኃይሎችን ለመያዝ በሚል ወደ ኬንያ እንደሚገቡም ይነገራል፡፡

 ብዙውን ጊዜ ጥቃቶችን የምታስተናግደው ማርሳቤት አውራጃ ናት፡፡ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ፖሊሶች የመጡባት ኤልሬት ወረዳም በዚሁ አውራጃ ትገኛለች፡፡ እንደ ፖሊስ መኮንኑ ገለጻ በኤልሬት እና ከዚህ ቀደም ጥቃቶችን በተፈጸሙባት ሶሎሎ በተሰኘችው ሌላኛዋ የማርሳቤት ወረዳ መካካል በትንሹ የ500 ኪሎ ሜትር ርቀት አለ፡፡

በድንበር ላይ ችግሮች በየጊዜው እንደሚፈጠሩ አምባሳደር ዲናም ያምናሉ፡፡ ሆኖም ችግሮቹ “ከባድ አይደሉም” ባይ ናቸው፡፡ 

“የኢትዮጵያ እና የኬንያ ድነበር የሚለይም አይደለም፡፡ አንዳንዴ የእነርሱ የጸጥታ ኃላፊዎች ወደ እኛ የሚገቡበት፤ የእኛ ሰዎች ደግሞ ወደዚያ የሚገቡበት ሁኔታ ስላለ በየጊዜው የሚፈጠሩ ኢመደበኛ ነገሮች እንጂ ብዙም ከባድ አይደሉም፡፡ ይሄንን በመግባባት ፈትተነዋል” ይላሉ አምባሳደሩ፡፡  

እርሳቸው ይህን ቢሉም ከሁለት ሳምንት በፊት መቶ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ማርሳቤት ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል የኬንያ ጦር ሶሎሎ በተሰኘችው ወረዳ ላይ ሰፍሮ ነበር፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic