በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሳይንስ ትኩረት እና ተግዳሮቶቹ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 04.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሳይንስ ትኩረት እና ተግዳሮቶቹ

ካለፉት አምስት ዓመታት ገደማ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተፈጥሮ እና ለኢንጅነሪንግ ሳይንስ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጾዋል። ይህም ሆኖ 12ኛ ክፍል ጨርሰው ዩኒቨርስቲ መግባት ከቻሉት ተማሪዎች 70% ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ፣30% ወደ ማህበራዊ ሳይንስ እንዲገቡ መንግሥት ያወጣው ፖሊሲ ከትምህርቱ ይልቅ ወደ ፖለቲካ ቁጥጥር እንደሚያደላ የሚተቹ አልጠፉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:29 ደቂቃ

Wissnschaft (Äthio. Ausbildung schwerpunkt auf Naturwissenschaft&die Auswirkung) - MP3-Stereo

አትንኩት አላምረዉ ይባላል፣ 31 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እያለ በጎንደር ዩኚቨርሲቲ በሕክምና እና ሳይንስ ኮለጅ በጤና ኢንፎርማቲክስ የትምህርት ዘርፍ ላለፉት 9 ዓመታት በመምህርነት፣ በተመራማርነት እና በትምህርት ክፍለ ኃላፊነት ሢሠራ ቆይቶዋል። ወደ ጀርመን አገር ከመጣ ገና ሶስት ወሩ ነዉ፣ የጀርመን የትምህርት ልውውጥ አገልግሎት ሰጭ፣ በምጽህረ ቃሉ «ዳድ»(DAAD) በሰጠዉ ነፃ የትምህርት ዕድል የዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት በጤና ኢንፎርማቲክስ በኦልድንቡርግ ዩኒቨርሲቲ ምርምሩን ለመሥራት እንደመጣ ይናገራል። የጀርመኑ የትምህርት ልውውጥ አገልግሎት ሰጭዉ DAAD ለአትንኩት እና ለሌሎች ስድስት ከኢትዮጵያ ለመጡት ተማርዎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ዶክትሬት ዲግሪያቸዉን የሚያገኙበትን እድል ነዉ የሰጠዉ። ከእነዚህ ዉስጥም እሱን ጨምሮ ሶስቱ በተፈጥሮ ሳይንስ ዶክትሬት ዲግሪያቸዉን እንደሚሠሩ ታዉቆዋል።

አንድ የጀርመን የትምህርት እና የጥናት መረጃ የሚያቀርብ ተቋም፣ በጀርመንኛ አጠራሩ ቪስንሻፍት ቬልትኦፍን (Wissenschaft Weltoffen) በአዉሮጳዉያኑ 2015,ም ባዘጋጀዉ ዘገባ፣ ወደ ጀርመን አገር ለትምህርት የሚመጡ የተማሪዎች ቁጥር ለመጀመርያ ግዜ ከተጠበቀዉ በላይ መሆኑን ያትታል። ዘገባዉ 2014 በጀርመን የሚማሩ የዉጭ አገር ተማሪዎች 300,000 በላይ መሆናቸዉን ከተጠቀሰ በኋላይህም 2013 ዓም ጋር ሲነፃፀር 19,000 ገደማ መጨመሩንም ይገልፃል። ጀርመን ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከታላቋ ብሪታንያ ቀጥላ የዉጭ አገር ተማሪዎችን በመቀበል ሶስተኛ ደረጃ ስትሆን አብዛኛዉ ተማሪ የተሰማራዉ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል።

ከተጠቀሰዉ ቁጥር መካከል ከኢትዮጵያ የሚመጡ እንዳሉም በጀርመን የትምህርት ልውውጥ አገልግሎት «ዳድ» የአፍሪቃ የነፃ ትምህርት እድል ክፍለ-ኃላፊ የሆኑት ከይ ኤትዞልድ ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል።

«ተከታታይ የነፃ የትምህርት እድል ፕሮግራሞች አሉን። ከ130 የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን ከሚሠሩ ተማርዎች በተጨማሪ አሁን አዲስ የተጀመረ በጀርመን የኤኮኖሚ እና የልማት ትብብር ፌዴራል ሚኒስቴር የተመሰረተ ወደ 1000 የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎችን በፕሮግራሙ ከተለያዩ የአፍሪቃ አገሮች ተቀብሎ ያስተምራል። በ2014 በአጠቃላይ ከአፍሪቃ 4783 ከጀርመን ደግሞ 1942 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተቀብሏል። በ2015 ከአፍሪቃ 4700 ተማሪዎችን ተቀብሏል። ሆኖም ግን ደረጃ ሰጥተን ካየነዉ ደቡብ አፍሪቃ እና ኬንያን ተከትላ ኢትዮጵያ በሦስተኛ ደረጀ ላይ ትገኛለች፣ ከኢትዮጵያ የመጡት 667 ሲሆኑ እነሱም የዶክትሬት እና የሁለተኛ ዲግሪያቸዉን የሚሠሩ፤ እንዲሁም በትምህርት ልዉዉት፣ ለጥናት እና ለተለያየ ትምህርት የሚመጡም አሉ።»

2014 ከኢትዮጵያ ለመጡት 188 ተማሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በኢንጅነሪንግ የትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ መሆኑን «ዳድ» የአፍሪቃ የነፃ ትምህርት እድል ክፍለ-ኃላፊዉ ከይ ኤትዞልድ ይናገራሉ። 2010 ኢትዮጵያ መንግስት የተማሪዎችን ምደባ በተመለከተ ባወጣዉ የትምህርት መመሪያዉ 70 በመቶ የሚሆኑ ወደ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች፣ ቀሪዉን 30 በመቶ ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ለማሠልጠን መታሰቡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ባለፈዉ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በምክር ቤት ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ፣ አገራቸዉ መለስተኛ የግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርታ ብትገኝም፣ የሰዉ ኃይል ኣቅም እንደሚያንሳት ጠቅሰዋል። ይህንን ክፍተት ለመሙላትም ለሳይንስና ቴክኖሎጂዉ ከተመደበዉ 70 በመቶ፣ 40 በመቶዉ ወደ ምህንድስና የሚገባ ኃይል እንደሆነ ተናግረዋል።

ተማሪዉ አትንኩት አላምረዉ «ኢትዮጵያ ወደ ሳይንስ ትኩረት መስጠቷ የበለጠ ኣገሪቱ ዉስጥ የሚደረገዉን ልማት በጣም ያግዛል።» ሲል ይናገራል። ለተፈጥሮ ሳይንስ የተሰጠው ትኩረት «አገሪቷ የምታልመው ኢኮኖሚ ላይ እንድትደርስ ያደርጋታል» የሚል እምነት ያለው አትንኩት ለሳይንስ ትምህርትና የጥናትና ምርምር ዘርፎች የተሰጠው ትኩረት መልካም መሆኑን ተናግሯል።

«ቢ ቢ ሲ» የተሰኘዉ የብሪታንያ የዜና አዉታር ባወጣዉ ዘገባ ይህ አይነቱን ድልድል በተመለከተ የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል ወይስ ፖለቲካዉን ለመቆጣጠር በማለት መጠይቁ ይታወሳል። መንግሥት በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ብቻ ላይ ማትኮሩ የግል የትምህርት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የማህበራዊ ትምህርት በተለይም የመምህርነት ሥልጠና እና የሕግ ትምህርት እንዳይሰጡ ፖሊሲዉ ያግዳል ይላል ዘገባው። በመሆኑም የፖሊሲዉ ዓላማ የትምህርት ጥራት ከማሻሻል እና ለሥራ ገበያዉ ከማለም ይልቅ፣ ተማሪዎችን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ብቻ እንዲገቡና እዛም በሚያገኙት ስልጠና የመንግሥትን መንገድ ተከትለዉ እንዲያስቡና፣ የገዢዉ ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ማድረግ ነዉ በሚል የሚተቹ መኖራቸዉንም ጠቅሷል። ይህን ትችት የትምህርት ሚኒስትሩ አጣጥለዋል።

ወደ ጀርመን ከሚመጡት አብዛኞቹ እንደሚመለሱ ኤትዞልድ ይናገራሉ። አስቻለዉ ገላ «ዳድ» የነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ በላይብሲሽ ዩኒቨርሲቲ በማይክሮ ባይሎጂ የዶክትሬት ዲግሪዉን ለመሥራት እንደመጣ ለዶቼ ቬሌ በመግለፅ፣ ትምህርቱን አጠናቆ ሲመለስ ያለውን እቅድ እና ኃላፊነት አስረድቷል። «መጥቼ ትምህርቴን እንድማር የፈቀደልኝ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው። የተወሰነ ድጋፍ ያደርግልኛል። ትምህርቴን እንደጨረስኩኝ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በተማርኩት የትምህርት ዘርፍ አገልግሎት መስጠት አለብኝ።» እንደ አስቻለው ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ ለትምህርት ወደ ጀርመን የተጓዘው አትንኩት ዩኒቨርሲቲውን የማገልገል ሃላፊነት ተጥሎበታል «ከዛ በኋላ አሁን ከምሰራበት ዩኒቨርሲቲና ካገሬ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን መስራት» ቀጣይ እቅዱ መሆኑንም ተናግሯል።

የጀርመኑ የትምህርት ልውውጥ አገልግሎት ሰጪ፤ የትምህርት እድሉን የሚሰጠዉ አብዛኛዉ ለተፈጥሮ ሳይንስ ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚገኙት 13 ዩኒቨርሲቲዎች አገር በቀል በሚል በዓመት እስከ 40 ተማሪዎች እዛዉ ባሉበት ዩኒቨርሲቲዎች እየተማሩ ለስድስት ወር ጀርመን መጥተዉ ጥናታቸዉን በሳይንስና ቴክኖሎጂ መቀጠል እንዳስቻላቸዉ የአፍሪቃ የነፃ ትምህርት እድል ክፍል ኃላፊዉ ኤትዞልድ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ይህ የመንግሥት ዉሳኔ ቢሆንም፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የትምህርት ዘርፎች ክፍት መሆን እንዳለበት  ኤትዞልድ ይናገራሉ። «ዳድ» መንግሥት የዘረጋዉ 70 30 ድልድል አጋር መሆኑን በመጥቀስ፣ ድልድሉ ጤናማ ሚዛን ቢኖረዉ ተመራጭ መሆኑንም ያመለክታል።

«ይህ ድልድል የመንግስት ዉሳኔ ነዉ። መንግሥት የትምህርት ሚኒስቴር እቅዱን ሲገነባ ወደፊት ጠንካራ የኢንጅነሪንግ ሳይንስን እንደሚያበረታታ ነዉ የተናገረዉ። ግን እኔ እንደማምነዉ ከሆነ፣ መንግሥት ጤናማ የሆነ ሚዛንን በተፈጥሮ ሳይንስ እና በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ መጠበቅ አለበት። ዩኒቨርሲቲዎችን ለመገንባት የግዴታ የተፈጥሮ ሳይንስ ከማህበራዊ ሳይንስ ጋር ተመጣጥኖ ማደግ አለበት። ለዚህም ነዉ እኛ ለኢንጅነሪንግ ሳይንስ እና ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማርዎች ብቻ ሳይሆን በሩን ለሁሉም የትምህርት ዘርፎች የከፈትነዉ። ያ አንደኛዉ ነዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ፣ በእርግጥ ብዙ የትምህርት ማመልከቻ የሚመጣዉ ከተፈጥሮ ሳይንስ እና ከኢንጅነሪንግ ሳይንስ ነዉ፣ ምክንያቱም ከማህበራዊ ሳይንስ ይልቅ ለእነዚህ የትምህርት ዘርፎች ትልቅ ፍላጎት ስላለ ነዉ። በቀላሉ ብዙ አመልካች ስላለና የትምህርት ጥራቱም ጥሩ ስለሆነ ነዉ።»

መረሳት የሌለበት ጉዳይ ግን ይላሉ ኤትዞልድ፣ ይህ ኣይነቱ የትምህርት ፖሊሲ የሥራ ገበያዉን ከግምት ዉስጥ ማስገባት እንዳለበት እና ከዚያም አልፎ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ መገንባትም አለበት ይላሉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic