በቶጎ አባት የጀመረዉን ልጅ | የጋዜጦች አምድ | DW | 08.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

በቶጎ አባት የጀመረዉን ልጅ

ነፃነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ በስልጣን ላይ የወጡት አምባገነን መሆናቸዉ የሚነገርላቸዉ የቶጎዉ ፕሬዝዳንት ጌናሲንግቤ ኢያዴማን ሞት ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን ቃለመኃላ የፈፀሙት ልጃቸዉ ፌኡሬ ጌናሲንግቤ ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል።

አዲሱ የቶጎ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሃላ የፈፀሙት ፌኡሬ ጌናሲንግቤ ወደ ስልጣን የወጡት የአገሪቱ መተዳደሪያ ህግ በማይፈቅደዉ መንገድ በመሆኑ ድርጊቱ በአፍሪካ ህብረትም አልተደገፈም።
በአገሪቱ ህግ መሰረት የኢያዴማን ሞት ተከትሎ የፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን የግድ ለሁለት ወራት መያዝ የነበረበት የአገሪቱ ፓርላማ አፈጉባኤ እንጂ ልጃቸዉ አልነበረም።
ህገ መንግስታቸዉ በሚፈቅደዉ መሰረት ጊዜያዊ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን የተሰጠዉ አካል በተሰጠዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ በአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በማካሄድ የቶጎን ብሄራዊ ፕሬዝዳንት ያስመርጣል።
ሆኖም ግን በቶጎ ዋና ከተማ ሎሜ የኢያዴማን ሞት ተከትሎ የአገሪቱ ህግ አዉጪዎች እሁድ እለት ስራበዝቶባቸዉ ነበር የዋሉት ህገ መንግስቱን ወደጎን በመተዉ የኢያዴማን ልጅ ወደስልጣን ለማዉጣት የሚያስችል ህግ ሲያረቁ።
በወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የታጀበዉ የህግ አርቃቂዎች ተግባር የማዕድን፤ የፓስታና ቴሌኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩትን የኢያዴማን ልጅ አፈጉባኤ ከማድረጋቸዉ በፊት የፓርላማ አባል የማድረግ ስራ ሰርተዋል።
ከዚያም የ39 አመቱን ወጣት ሚኒስትር 81 አባላት ካሉት የአገሪቱ ህግ አርቃቂዎች መካከል 67ቱ በተገኙበት በሙሉ ድምፅ ለአገሪቱ ፕሬዝዳንትነት መምረጣቸዉን አሳወቁ።
በመቀጠልም ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ በማድረግ ተመራጩ ፕሬዝዳንት አባታቸዉ በህወት ቢኖሩ እስከሚቆዩበት የስልጣን ዘመን ማለትም እስከ መጪዉ የፈረንጆቹ 2008 ዓ.ም. ድረስ አገሪቱን እንዲያስተዳድሩ አደረጉ።
ተቃዋሚዎች በሟች አባታቸዉ እግር ለመተካት የቆሙት የ39አመቱን ጌናሲግቤ ለፕሬዝንዳንትነት ያበቃዉ የአገሪቱ የጦር ኃይል የተከተለዉ መንገድ የአገሪቱን ህገመንግስት የሚፃረር ነዉ ሲሉ የአፍሪካ ህብረትም ድርጊቱ መፈንቅለ መንግስት ነዉ በማለት አዉግዟል።
በአገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የተካሄደዉን የፕሬዝዳንት ምርጫ ህዝቡ በተቃዉሞ እንዲያሳይ ቅስቀሳ አካሂደዋል።
ህዝቡም ተቃዉሞዉን ጌናሲግቤ የፕሬዝዳንታዊ ቃለ መሃላ በፈፀሙበት እለት ቤቱ በመከተት 4.7 ሚሊዮን ህዝብ አለባት የምትባለዉን አገር የሙታን መንደር አስመስለዋት ዉለዋል።
በመቀጠልም በትናንትናዉ እለት የሁለት ወራት የሃዘን ጊዜ ይሰጠን በማለት ለተቃዉሞ የወጣዉን ህዝብ ችላ በማለት የአገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ አኪላ ኤሶ ቦኮ በፕሬዝዳንታቸዉ ሞት ምክንያት ተዘግተዉ የነበሩ የባህር፤ የየብስና የአየር በሮቻቸዉን ከፍተዋል።
የሟቹን ፕሬዝዳንት ልጅ በመደገፍ ወታደራዊ ኃይሉ የተጫወተዉን ሚና በተመለከተ አለም አቀፉን ተቃዉሞ የሚመራዉ የአፍሪካ ህብረት ተቃዉሞዉን በቃል አቀባዩ አዳም ቲማን አማካኝነት እያሰማነዉ።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ በቶጎ የተካሄደዉ ህገ መንግስትን ያልተከተለ የስልጣን ሽግግር ባስቸኳይ ማስተካከያ ካልተደረገ በቀር ቶጎ ማዕቀብ ይጣልባታል።
ሆኖም በከፍተኛ ጥበቃ ስር የሚገኘዉ ቤተመንግስት ይህን ሁሉ ተቃዉሞና ትችት ወደ ጎን በመተዉ ሚኒስትሮች፤ ህግ አዉጪዎች፤ የቻይና፤ የሊቢያና የኮንጎን አምባሳደሮች ጨምሮ በርካታ ዲፕሎማቶች በተገኙበት ፌኡሬ ግናሲንግቤ የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ እንዲፈፅሙ አደረገ።
ኮከብ ባለበት የቶጎ ሰንደቅ አላማ ተከበዉ ግናሲግቤ ቀኝ እጃቸዉን ማንሳት በአገሪቱ አጠቃላይ ፍላጎት ለመመራትና ሰብአዊ መብትን ለማክበር ቃል እገባለሁ በማለት መሃላቸዉን ፈፀሙ።
ፈረንሳይ አገር በስደት ላይ የሚገኙት የተቃዋሞ እንቅስቃሴ መሪ ጊልሽሪስት ኦሊምፓ በወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የግናሲንግቤ በሟች አባታቸዉ እግር መተካት በቶጎ ብጥብጥ ያስነሳል የሚል ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
15 አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ሃብት ማህበረሰብ ሰኞ እለት ጋኔሲግቤ እንደተሾሙ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮፊ ሳማ ጋር ቆይታ ካደረገ በኋላ ቶጎን ለቆ ኒጀር ዋና ከተማ አስቸኳይ ስብሰባ በነገዉ እለት ለማካሄድ ወጥቷል።
የኒጀር የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሉት እንደ ምዕራብ አፍሪካ ማህበረሰብነታቸዉ በቶጎ ግጭት ሳይሆን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም መረጋጋትን በዘላቂነት ሰፍኖ ማይተት ነዉ።
ወደዉጪ አገር ለህክምና ሊወሰዱ ሲሉ ስራ ቦታቸዉ እንዳሉ መሞታቸዉ የተነገረዉ ኢያዴማ በወታደራዊ ኃይል ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት እ.ኤ.አ.1967ዓ.ም. የቶጎ ፕሬዝዳንት ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ህወታቸዉ እስካለፈችበት እለት ድረስ በአገሪቱ የተቃዉሞ እንቅስቃሴን በማፈን በአምባ ገነንነት የቆዩ ነበሩ።
በልጃቸዉ ዘመን ደግሞ ምን ሊሰራ እንደሚችል በጉጉት እየተጠበቀ ነዉ ስልጣናቸዉ ግን ገና ከጅምሩ ተቃዉሞ አጅቦታል።