1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ማሕበራት ጥያቄ

ዓርብ፣ ነሐሴ 13 2014

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሀገራዊ እና ክልላዊ ሲቪል ማሕበራት ለ15 ወራት በትግራይ እንደተዘጉ የሚነገረው ሁሉም ዓይነት መሠረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲከፈቱ ጠየቁ። ሲቪል ተቋማቱ እንደሚገልፁት በትግራይ በተጣለው የመሠረታዊ አገልግሎቶች ክልከላ ምክንያት ህዝቡ ለከፋ ችግር ተጋልጦ ይገኛል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4Fmsi
ምስል Million Hailesilassie/DW

ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወዲህ በትግራይ ባንኮች ተዘግተው እንደሚገኙ የገለፀልን የመቀሌ ወኪል ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ፥ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ ሐይል አቅርቦት እና ሌሎች መሠረታዊ የህዝብ አገልግሎቶችም እንደተቋረጡ ናቸው ይላል። የሴቶች እና ወጣቶች ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ አደረጃጀቶች፣ የሙያ ማሕበራት፣ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶች እና ሌሎች በአጠቃላይ 72 ሲቪል ተቋማት ያቀፈው የትግራይ ሲቪል ማሕበራት ሕብረት፥ በትግራይ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ ከመጥሮ ወደ ከፋ ሁኔታ እየተሸጋገረ ይገኛል ብሏል። የሕብረቱ ሰብሳቢ አቶ ያሬድ በርሃ "ያለው ሰብአዊ ቀውስ ለማቃለል የሚረዳ ከዓመት በላይ ሙሉ በሙሉ የተዘጉ እንደ ባንክ፣ የኤሌክትሪክና ቴሌኮም አገልግሎት የመሳሰሉ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች ሊከፈቱ ይገባለ" የሚሉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘጉት እነዚህ አገልግሎቶች ዳግም ለማስጀመር የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ጫና ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። 

ከ750 ሺህ በላይ አባላት ያሉት የትግራይ ሴቶች ማሕበር በበኩሉ፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ በተለይም ለሴቶች ፈታኝ መሆኑ ይገልፃል። የትግራይ ሴቶች ማሕበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አበባ ኃይለሥላሴ "ከትግራይ እናቶች ሕግ ተማምነው፥ ከመቀነታቸው ፈትተው በባንክ ያስቀመጡት ገንዘብ ማግኘት ተከልክለዋል፣ በዚህም ልጆቻቸው ለረሀብ እየተጋለጡ ነው" ሲሉ ያለው ሁኔታ ይገልፃሉ። በሴትች ዙርያ የሚሰሩ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ አደረጃጀቶች በትግራይ ያለው አስከፊ ሰብአዊ ሁኔታ ለማቃለል እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ