በተበጠበጠው ቀጠና የተረጋጋ ምርጫ የምታካሒደው ጋና | አፍሪቃ | DW | 06.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በተበጠበጠው ቀጠና የተረጋጋ ምርጫ የምታካሒደው ጋና

ጋናውያን ነገ አዲስ ፕሬዝዳንት እና የምክር ቤት አባላትን ሊመርጡ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያቀናሉ። ፕሬዝዳንት ማሕማ እና ተፎካካሪያቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ ናና አኩፎ አዶን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ዕለተ-ሰኞ ድረስ ድምፅ ሰጪዎችን ለማሳመን በብርቱ ሲፎካከሩ ሰንብተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:51

የጋና ምርጫ

በዕለተ ረቡዕ በሚካሔደው የጋና ምርጫ የሚሳተፉት ሁሉም ፖለቲካዊ ፓርቲዎች እጅጉን አድካሚ ጊዜ አሳልፈዋል። የምርጫው ቀዳሚ ተፎካካሪዎች በስልጣን ላይ የሚገኙት የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ ፓርቲ ተወካይ ጆን ማሕማ እና አዲስ አርበኝነት(አገር ወዳድነት) ፓርቲ ተወካይ ናና አኩፎ አዶ ናቸው። የምረጡኝ ዘመቻው በሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ፍክክር ተካሒዶበታል። በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ጆን ማሕማ ለምን በድጋሚ መመረጥ እንዳለባቸው ለማስረዳት ያላደረጉት ሙከራ የለም። 
«በዲሴምበር 7 የእዚች አገር እጣ ፈንታ እጃችን ላይ ይወድቃል። የለውጡን ሰዓት ወደ ኋላ ለመመለስ ፈለግንም ወደ ፊት ለመጓዝ ውሳኔው በእጃችን ነው። ማድረግ ያለብኝን ሁሉ አድርጊያለሁ። የቀረውን ለእናንተ ትቻለሁ። እርግጠኛ ነኝ ትክክለኛውን ውሳኔ ትወስናላችሁ። ቀላል እና ምክንያታዊ ነው።» 
ተፎካካሪያቸው ናና አኩፎም በምረጡኝ ዘመቻው ታታሪ ሆነው ተስተውለዋል። ናና አዶ በስልጣን ላይ የሚገኙት ጆን ማሕማ ሁለተኛ ዙር ለመመረጥ የሚያበቃ ሥራ አልሰሩም ሲሉ ይወቅሷቸዋል። እንዲያውም የእሳቸው የጋናን ኢንዱስትሪ የማሳደግ እቅድ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ድምፃቸውን እንዲሰጧቸው ያግባባል የሚል እምነት አድሮባቸዋል። 

«በባሕር ዳርቻዎች ለሚገኙ አሳ አስጋሪ ማሕበረሰቦች ሥራ ለመፍጠር አዳዲስ ወደቦች እና መጋዘኖች እንገነባለን። እናደርገዋለን። በእያንዳንዱ መንደር ፋብሪካ እንገነባለን።»
 በምረጡኝ ዘመቻው የሁለቱ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ይጋጫሉ የሚል ሥጋት በጋናውያን ዘንድ አንዣብቦ ነበር። የጋና ፖሊስ አዛዥ ሆን ኩዳሎር እንዲህ አይነት ስጋቶች በድጋሚ እንዳይፈጠር የደህንነት ጥበቃው መከለሱን ተናግረዋል። የፖሊስ አዛዡ የምርጫ ሒደቱ ነፃ እና ሰላማዊ እንደሚሆን እርግጠኛ ናቸው። 
«ከምርጫው በፊት፤ በምርጫው ወቅት እና በኋላ ሕብረተሰቡ ሊወስድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች የሚያብራሩ በራሪ ወረቀቶች የአደባባይ ማስታወቂያዎች አዘጋጅተናል። መረጃዎቹ  ሕብረተሰቡን ለመጪው አጠቃላይ ምርጫ በሚገባ እንዳዘጋጀው እርግጠኛ ነኝ።»በነገው ምርጫ የሚሳተፉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ የምርጫ ሒደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ የተገባ የጋራ ቃል-ኪዳን ነው። ፓርቲዎቹሥምምነቱን በጋራ እንዲፈራረሙ ያመቻቸው ናሽናል ሐውስ ኦፍ ቺፍስ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ደግሞ ቶግቤ አፌዴ ናቸው።

«ይኸን ቀን ማክበር አለብን። የዚህ ቀን ታላቅ ክብር ደግሞ ለራሳችን፤ ለአገራችን መስራች አባቶች እና ለዜጎቻችን የጋና ሰላም ቋሚ እና ዘላቂ መሆኑን የምናረጋግጥበት ነው።የአገራችን ሰላም የሁላችንም ኃላፊነት ነው።» ጋና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚከበሩባት የተረጋጋች አገር ተደርጋ ትቆጠራለች። የምርጫው ሒደት ከፍተኛ ውድድር ቢታይበትም መጠነ-ሰፊ ኹከት ይቀሰቀሳል የሚል ሥጋት ግን የለም። ረቡዕ የማይመቻቸው ወገኖች በሁለት ዙር አስቀድመው ድምፅ ሰጥተዋል። ይኽ የጸጥታ ጥበቃ ኃይሎች፤ጋዜጠኞች እና የምርጫ ኃፊዎችን ይጨምራል። ከምርጫ ዝርዝር ውስጥ የተወሰኑ ስሞች በመጥፋታቸው ሒደቱ እንቅፋት ገጥሞት ነበር። የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ተመሳሳይ ችግሮች በነገው ዕለት እንደማይከሰቱ ቃል ገብቷል። የአውሮጳ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ኃላፊ ታማስ ሜስዜሪክስ የድምፅ አሰጣጡ በሰላም እንደሚጠናቀቅ ከወዲሁ ማረጋገጫዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
«አሁን መናገር የምንችለው የምርጫ ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ቀን ከተፈጠሩ ጥቃቅን እንከኖች ጠቃቅን ትምህርቶች መቅሰማቸውን ነው። ምርጫ ሁልጊዜም በእያንዳንዱ አገር የመማር ሒደት ነው። ይኽ ለጋና የተለየ አይደለም። በዚህ በኩል በዲሴምበር በሰባተኛው ቀን የሚካሔደው ምርጫ በሰላም ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለኝ።»

የምረጡኝ ዘመቻው ተጠናቋል። ጋናውያንም አዲስ ፕሬዝዳንት እና የምክር ቤት አባላት ለመምረጥ ዝግጁ ናቸው። ውድድሩ የከረረ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

 

ኢዛክ ካሌድዚ/እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች