በሶማሊያ የተሰበረዉ የተኩስ አቁም | የሶማልያ ውዝግብ | DW | 29.03.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የሶማልያ ውዝግብ

በሶማሊያ የተሰበረዉ የተኩስ አቁም

በሶማሊያ መዲና መቃዲሾ ዉጊያ ማገርሸቱ ተነገረ። በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች የሚረዳዉ የሽግግር መንግስቱ ኃይል በመዲናዋ የሸማቂዎቹ ዓይነተኛ ስፍራ የተባሉትን አካባቢዎች ማጥቃት መቀጠሉን የዜና ምንጮች ዛሬ ዘግበዋል።

የመቃዲሾ ተጎጂዎች

የመቃዲሾ ተጎጂዎች

አዲስ አበባ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሶማሊያ ከተላከዉ ኃይል ሁለት ሶስተኛዉ ወጥቷል ሲሉ ለምክር ቤቱ ዘገባ አቅርበዋል።

የሶማሊያ መዲና የመቃዲሾ ሁኔታ እየተዳፈነ የሚግም ሆኗል። ባለፈዉ ሰሞን በመዲናይቱ በተከታታይ የተሰማዉ የዉጊያ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ ጋብ እንዳለ ተነግሮ ነበር። ዛሬ ደግሞ የሽግግር መንግስቱና የኢትዮጵያ ወታደሮች በታንኮችና በሄሊኮፕተር እየታገዙ የሸማቂዎቹ ጠንካራ ይዞታ በተባሉ ስፍራዎች በማለዳ ጥቃት ከፍተዋል። እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላዉቅም የሚሉት የተደናገጡ የከተማዋ ነዋሪ ሁሴን ሃጂ የኢትዮጵያ ወታደሮች ትላልቁን መሳሪዎቻቸዉን በሚተኩሱበት ወቅት የቤቴ መስኮቶችና በሮች እርገፈገፋሉ በማለት ነዉ ለሮይተርስ ዘጋቢ የገለፁት። አጃንስ ፍራንስ ፕረስ በበኩሉ ሁለት የኢትዮጵያ ሄሊኮፕተሮች በደቡባዊ መቃዲሾ ሁለት ሚሳኤል መተኮሳቸዉን ዘግቧል። ሸማቂዎቹ በመሸጉባቸዉ አካባቢዎች በተካሄደዉ ዉጊያም ቢያንስ የ፩፲ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተነግሯ። የዛሬዉ ማለዳ የጥቃት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ትናንት የኢትዮጵያ ታንኮች የሸማቂዎቹ ጠንካራ ይዞታ ወደተባሉት ስፍራዎች አካባቢ ማቅናታቸዉ ተጠቁሟል። ከዚያም ዛሬ ጠዋት በመዲናይቱ ደቡባዊ አካባቢ ኢትዮጵያዉያኑ ጥቃት ሰነዘሩ ሲሉ አንድ በስፍራዉ የሚገኙ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አባል ለዘጋቢዎች ገልፀዋል። ለስድስት ቀናት የቆየዉ በቋፍ የነበረዉ የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ ሲሰበርም በዉጊያዉ የተጎዱ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ናቸዉ ተብሏል። ይህም የመዲናይቱን አብዛኛ ክፍል ከአዉሮፓዉያኑ 1991ዓ.ም ወዲህ በስፋት ከተዎታጠረዉ የሃዉያ ጎሳ ጋ የተጀመረዉ የተኩስ አቁም ተስፋ እንዲጨልም ሳያደርገዉ አልቀረም። ጥቃቱ ከተከፈተባቸዉ ስፍራዎች መካከል መሽገዉ አደጋ ሲጥሉ የከረሙት ሸማቂዎች የኢትዮጵያ ወታደሮችን በሶማሊያ ምድር መገኘት አጥብቀዉ የሚቃወሙ መሆናቸዉ ታዉቋል። አካባቢዉም የሽግግር መንግስቱና የኢትዮጵያ ወታደሮች የማይንቀሳቀሱበት እንደነበር ነዉ የሚነገረዉ።

በጎዳናዉ የሚነጉደዉ ፈንጂና የተኩስ ልዉዉጡ የአካባቢዉ ኗሪዎች በቤታቸዉ እንዲከተቱ እንዳስገደዳቸዉ የአይን ምስክርን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። የተጎዱትን በማስተናገድ የተጣደፉ አንድ የመዲና ሃኪም ብት ዶክተር ለዜና ዘጋቢዎች በስልክ እንደገለፁት ለእርዳታ ወደእነሱ የተወሰዱ ሰዎችን ቁጥር ለጊዜዉ መግለፅ በማይችሉበት ዉጥረት ላይ ነዉ የሚገኙት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚንትር መለስ ዜናዊ ዛሬ ለምክር ቤታቸዉ ባቀረቡት ዘገባ ወደሶማሊያ ከተላከዉ ፪/፫ኛ የሚሆኑት ወታደሮቻቸዉ ከአገሪቱ ምድር መልቀቃቸዉን ነዉ ያስታወቁት። ኢትዮጵያ ሶማሊያ ምድር የመሰንበትም ሆነ በሰላም ማስከበሩ ተልዕኮ ፍላጎት እንደሌላትም ተናግረዋል። ወደሶማሊያ የገቡበትን ምክንያት ሲያብራሩም ፅንፈኞች የጋረጡትን ስጋት ለማፈራረስ እንደነበር በመግለፅ ያ እንደተሳካላቸዉ ነዉ የተናገሩት። እናም አሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሶማሊያ ሁኔታ ከታሰበዉ የተለየ ሆነመገኘቱ ቀስ በቀስ በሁለት ዙር ወታደሮቻቸዉን ጨርሰዉ ያስወጣሉ። በተለይ ደግሞ የአፍሪቃ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይልን የመላኩ ጉዳይ እንደተገመተዉ ባለመሆኑ ጦራቸዉ ከሶማሊያ ምድር ሊወጣ ካሰቡበት ጊዜ ሊራዘም መቻሉን አስረድተዋል። በሶማሊያ የታየዉ እርምጃቸዉም ኤርትራን ጨምሮ ወራሪ ላሏቸዉ ኃይሎች ኢትዮጵያ የማይበገር አቋምና አቅም እንዳላት ያመላከተ መሆኑንም አስገንዝበዋል።