በሳይንስ የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.10.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በሳይንስ የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣

የዲናሚት (ዳይናማይት ) ፈልስፊ በሆኑት እስዊድናዊ የሥነ-ቅመማ(ኬሚስትሪ) ሊቅ አልፍረድ ኖቤል ስም ፣ እ ጎ አ ከ 1901 ዓ ም አንስቶ በያመቱ በሳይንስ፣ ሥነ ጽሑፍና ሰላም አሸናፊዎች የሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ሥም እንደሚገለጥ ሁሉ፣

default

የዘንድሮዎቹ አሸናፊዎችም እነማን እንደሆኑ ፣ ሸላሚው ድርጅት በዚህ ሰሞን ማስታወቅ የጀመረ ሲሆን፣ ከትናንት በስቲያ በህክምና ሳይንስ ፣ ትናንት በፊዚክስ፤ ያሸነፉት የታወቁ ሲሆን ፤ በሥነ ቅመማ(ኬሚስትሪ ) ደግሞ አንድ አሜሪካዊና ሁለት ጃፓናውያን አሸናፊዎች መሆባናቸው በዛሬው ዕለት ተገልጿል። ጤናይስጥልን እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ በሳይንስ ምርምር፤ የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችን ፣ በተለይም በፊዚክስ ተመራማሪዎቹ ውጤት ዙሪያ ያጠናቀርነውን ይሆናል የምናሰማችሁ።

እ ጎ አ፣ ጥቅምት 21 ቀን 1833 በእስቶክሆልም እስዊድን ተወልደው ታኅሳስ 10 ቀን 1896 ዓ ም፣ በሳን ሬሞ ኢጣልያ ፤ በህመም ሳቢያ በ63 ዓመታቸው ያረፉት አልፍረድ ኖቤል፤ በኑዛዜአቸው መሠረት፣94 ከመቶ ከነበራቸው ንብረትም ሆነ ጥሪት፣ (31 ሚልዮን የአስዊድን ክሮነ) እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም እንደተተመነው 186 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ታውቋል። እናም የእስዊድንና የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴዎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጠቀሱት የምርምር ዘርፎችና ለዓለም ሰላም ላቅ ያለ ድርሻ አበርክተዋል ብለው ላመኑባቸው ፣ ከዚህ ገንዘብ እየቆነጠሩ ይሸልማሉ። በሳይንስ ረገድ ተሸላሚዎቹን የሚሰየሙት የእስዊድን የምርምር ተቋማት ናቸው። የሰላም ሽልማቱን የሚሰጠው የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ነው።

አሜሪካዊው ሪቻርድ ሄክ፤ እንዲሁም፣ አይ ኢቺ ነጊሺና አኪራ ሱዙኪ የተሰኙት ጃፓናውያን የዘንድሮው የሥነ ቅመማ ሽልማት አሸናፊዎች ለመሆን የበቁት፤ በካርበን አቶሞች ስብጥር ወህደት አዳዲስ መድኀኒቶችን ለመቀመምና የተለያዩ ፕላስቲክ መሰል መሣሪያዎችንም ለማምረት በሚያስችለው ምርምራቸው ነው። የ 3 ቱ ሰዎች የምርምር ሂደት ፣ በዓለም ዙሪያ፤ መድኀኒት በሚቀምሙና በኤሌክትሮኒክ ኢንዱስትሪዎች ዘንድም ከሞላ ጎደል ይታወቃል።

ከ 32 ዓመት ገደማ በፊት ፣ ከማህፀን ውጭ በቤተ-ሙከራ፤ ፅንስ፣ አድጎ ፣ ህጻን ልጅ እንድትወለድ ያበቁት የ 85 ዓመቱ አዛውንት ተመራማሪ ሮበርት ኤድዋርድስ ከትናንት በስቲያ፤ በህክምና ሳይንስ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ታውቋል። የኤድዋርድስ ምርምር ፣ መጸነስ ለማይችሉ ሴቶች ብሥራት ሆኖ ነበር የቀረበው። ይህ፣ በሳይንስ አመለካከትና ልጅ ለማግኘት ተስኗቸው ምኞታቸው በተሳካላቸው ወላጆች በተለይም እናቶች እይታ እንጂ የብዙዎቹን የሃይማኖት አባቶች አስተሳሰብ አይወክልም። እዚህ ላይ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች በዚህ ረገድ የተገኘውን የምርምር ውጤት ያወገዙት መሆናቸው፤ የሮበርት ኤድዋርድስን ለሽልማት መታጨትም በበጎ ዐይን እንዳልተመለከቱት የታወቀ ነው። ያም ሆነ ይህ ፣ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጌዜ፣ በቤተ ሙከራ በትልቅ ብርጭቆ ፣ ከፅንስ ወደ ህጻን አድጋ እ ጎ አ ሐምሌ 25 ቀን 1978 ዓ ም ለመወለድ ከበቃችው፤ ከሉዒዘ ጄይ ብራውን ወዲህ፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በተመሳሳይ ሁኔታ የዝችን ዓለም ብርሃን ለማየት የበቁት ህጻናት ቁጥር፣ ከ 4 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። በዕድሜ እጅግ የገፉ ጎምቱዎች፣ እንክባካቤ እየተደረገላቸው የመጨረሻ የህይወት ዘመናቸውን በሚያሳልፉበት ቦታ የሚገኙት፣ አሁን በእርጅናና ህመም ሳቢያ ደከም ያሉት ሮበርት ኤድዋርድስ፣ እጅግ ቢዘገይም የሽልማቱ አሸናፊ መሆናቸው ልዩ እርካታ አሳድሮባቸው እንዲህ ነበረ ያሉት።

« ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይንስና ህክምና ከሰው ልጅ አስተሳሰብ ወሳኝ በሆነ መልኩ መሥረጻቸውን ለማወቅ ችለናል። ከእንግዲህ ወዲያ የምናተኩረው፤ በጽንስ በሚከሠቱ በሽታዎችና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ይሆናል።»

በፊዚክስ ሽልማት ለማግኘት የበቁት ሁለቱም ተማራማሪ ጠበብት በትውልድ ሩሲያውያን ናቸው። ኑሮአቸው በኢንግላንድና ኔደርላንድ ነው። በማንቼስተር ዩኒቨርስቲ የሚመራመሩት የ 36 ዓመቱ ጎልማሣ፤ ኮንስታንቲን ኖቮሴሎቭ የሩሲያና የብሪታንያ ፣ የ 51 ዓመቱ አንድሬ ጋይም ደግሞ የኔደርላንድ ዜግነት ነው ያላቸው።

እ ጎ አ ከ 1973 ዓ ም ወዲህ በፊዚክስ የሽልማት አሸናፊ ወጣት ተመራማሪ ኮንስታንቲን ኖቮሴሎቭ መሆናቸው ታውቋል። እ ጎ አ በ 1973 ዓ ም፤ በ 33 ዓመታቸው በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት የተጋሩት ፣እንግሊዛዊው ወጣት ተመራማሪ ብራያን ዴቪድ ጆሰፍሰን እንደነበሩ ይታወሳል።

አንድሬ ጋይም፤ በዚያው በማንቼስተር ዩኒቨርስቲ የረቂቅ ሥነ ቴክኒክ ማእከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ጋይም እ ጎ አ ሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ ም፤ በሃምበርግ ፣ ጀርመን ፣ 750 ሺ ዩውሮ የሚያሰጠውን የታወቀውን የ Körber ሽልማት ማግኘታቸው አይዘነጋም። ሁለቱን የፊዚክስ ሊቃውንት የሽልማት አሸናፊዎች ለመሆን ያበቃቸው፣ የካርበን ንጥረ-ነገር በሆነው፣ ጥቁር ፣ለስላሳ፤ እጅግ ስስ በሆነው፤ እንደ መስቲካ የሚሰበሰብና የሚለጠጥ ፤ የመጻፊያ እርሳስ ጭምር ከሚሠራበት ከ «ግራፋይት» በሚገኘው «ግራፊን» ላይ ባደረጉት ሰፊ ምርምር ነው። የፊዚክስ ፕሮፌሰርና፤ የኖቤል ኮሚቴ አባል ብዮርን ጆንሰን እንዳሉት፤«ይህ ልዩ የካርበን ንጥረ-ነገር ፣ ግራፊን፣ በጥንካሬው ብረታ ብረትን ከሁለት መቶ እጥፍ በላይ የሚያስከነዳ፤ 20 ከመቶ የሚዘረጋ ወይም የሚለጠጥ መሆኑም የታወቀ ነው። v

ግራፊን፤ ከበስተጀርባም ማየት የሚያስችል ስስ እስክሪን ለመሥራት ይበጃል። ፣ ቀላል ልብስ ሆኖም ሊቀርብ ይችላል። ፣ « ግራፊን፤ ኤልክትሪክ በፍጥነት በማስተላለፍም እስካሁን ወደር ያልተገኘለት በመሆኑ፣ ምናልባት የኤልክትሪክ ኃይል ለማጥመድ የሚረዳ የጸሐይ ብርሃንና ሙቀት አስተላላፊ መሣሪያ ለማምረት የሚያስችል ሳይሆን እንደማይቀርም ፤ ሽልማት ሰጪው የኖቤል ኮሚቴ አስታውቋል።

የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ከሆኑት መካከል፤ አንድሬ ጋይም ስለዚህ ንጥረ ነገር እንዲህ ይላሉ።

«ግራፊን በየጊዜው በአዳዲስና ባልተጠበቁ ባኅርያቱ ያስደምመናል። በፍጥረተ-ዓለም (ዩኒቨርስ) እጅግ ስስ ንጥረ ነገር ቢኖር ጋራፊን ነው። ከዚህ እጅግ የሳሳ ንጥረ-ነገር ይኖራል ብለን አናስብም። ከዚህም በተጨማሪ ግራፊን እስካሁን በተደረገው ፍተሻ በጥንካሬው ወደር የሌለው ነው። ከአንጸባራቂ ንጥረ ነገሮች የግራፊንን ያክል መጠኑ ሳይቀንስና ሳይጨምር እጅግ የሚኮማተርና የሚዘረጋ አንድም የለም። ግራፊን ከማንኛውም ቁስ በተሻለ ሁኔታም ኤሌክትሪክ የሚያስተላልፍ ነው።»

ሁለት የሩሲያ ዝርዮች ወደ ሌላ አገር ሄደው የፊዚክስ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው የቆጫቸው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ፣ ዛሬ ሞስኮ ውስጥ ከመምህራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ወደፊት ተሰጥዖ ያላቸው ተመራማሪዎች ባገራቸው፣ተግባራቸው እንዲያካሂዱ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። አንድሬ ጌይምና ኮንስታንቲን ኖቮሴሎቭ፣ የሞስኮ የፊዚክስና ሥነ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ምሩቃን መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ጌይም በ 1990ዎቹ መግቢያ ገደማ ነው ምዕራብ አውሮፓ የገቡት።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ