ቀይ ባህርን የሚያቋርጡ ስደተኞች እጣ ፋንታ  | ወጣቶች | DW | 25.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ወጣቶች

ቀይ ባህርን የሚያቋርጡ ስደተኞች እጣ ፋንታ 

የጀርመን ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲ  ዎች ፣ ኤርትሪያዊው አባ ሙሴ ዘርዓይ የመሠረቱት ኤጄንሲያ-ሐበሻ እና ወጣት ጀርመናውያን የመሠረቱት ዩግንድ ሬተት ድርጅቶች ከሊቢያ ጠረፍ ስደተኞችን ለማዳን መንቀሳቀስ ካቆሙት ድርጅቶች ጥቂቶቹ ናቸው።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:04

ባህር ያቋረጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ከሊቢያ ተነስተው የሜድትራኒያንን ባሕር ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት አደጋ የሚጋለጡ ስደተኞችን ከመስመጥ የሚያድኑ ድርጅቶች ተራ በተራ ሥራ ማቋረጣቸውን እያሳወቁ ነው። ይህም በአንድ በኩል ሕገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪዎችን ተባብራችኋል በሚል ጥርጣሬ በኢጣልያ ምርመራ እየተካሄደባቸው በመሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሊቢያ ባህር ኃይል የውጭ ሀገር መርከቦች ወደ ጠረፉ እንዳይጠጉ እገዳ በማስተላለፉ ነው።

የጀርመን ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲ  ዎች ፣ ኤርትሪያዊው አባ ሙሴ ዘርዓይ የመሠረቱት ኤጄንሲያ-ሐበሻ እና ወጣት ጀርመናውያን የመሠረቱት ዩግንድ ሬተት ድርጅቶች ከሊቢያ ጠረፍ ስደተኞችን ለማዳን መንቀሳቀስ ካቆሙት ድርጅቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ምክንያታቸው ይለያያል። በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከመስመጥ ያዳኑት ድርጅቶች ኢጣሊያ ከሰው አሸጋግሪዎች ጋር ተባብረው ሰርተዋል በሚል አንዳንዶቹ ላይ ክስ ስትመሰርት፤ ሌሎች ጭራሽ በሊቢያ ባህር ኃይል ተኩስ ተተኩሶባቸዉ ሸሽተዋል። እንደ ድርጅቶቹ ከሆነ፤ በዚህ ምክንያት ባህር ሰጥሞ የሚሞተው ስደተኛ ቁጥር ወደፊት ይጨምራል።

Italien Untergang Flüchtlingsboot - gerettete Flüchtlinge aus Lybien (picture-alliance/AP Photo/C. Montanalampo)

ከሊቢያ በባህር አቋርጠው ጣሊያን የደረሱ የአፍሪቃ ስደተኞች

ኤርሚያስ እና ገበየሁ  ትክክለኛ ስማቸው ሳይሆን ለዚህ ዝግጅት እንድንጠቀምበት የሰጡን መጠሪያ ነው። ኢትዮጵያውያኑ፤ በሊቢያ በኩል ባህር አቋርጠው ነው አውሮጳ የገቡት። ገበየሁ በፊንላንድ መርከብ ከመስመጥ ሲድን ኤርሚያስን ያተረፈው ደግሞ የብሪታንያ መርከብ ነው። የድርጅቶቹ ስራ ማቆም የስደተኞቹን ቁጥር ይቀንሳል ብሎ ኤርሚያስ አያምንም።  ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሊቢያ ላይ ታስሮ የደረሰበት በደል ነው።
ኢትዮጵያውያኑ ባህር ሰምጦ መሞት ብቸኛ ስጋታቸው እንዳልሆነ የተረዱት ገና  ሀገራቸውን እንደለቀቁ ነው። ገበየሁ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል ከሚጠራው ቡድን አባላት እጅ ሱዳን  ላይ እንዴት እንደተረፈ አጫውቶናል። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን እያንዳንዳቸው ከ5000 ዩሮ በላይ ገንዘብ ከፍለው ነው ባህር የተሻገሩት። እንደ አብዛኞቹ ስደተኞች ለነሱ የከፈሉት ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ቤተሰብ ነው። 

Deutschland Passau Flüchtlinge Notunterkunft Paul-Hallen (DW/N. Rujevic)

ጀርመን ለስደተኞቹ መኖሪያ እስክታገኝ ድረስ የምታቀርብላቸው ጊዜያዊ መቆያ ይህን ይመስላል።

በጣሊያን በኩል አድርገው ጀርመን የገቡት ስደተኞች ዛሬ በአንድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ይኖራሉ። የተለያየ መንገድ ይጓዙ እና መከራ ይቅመሱ እንጂ ሁለቱም ከአውሮጳ የጠበቁት ተመሳሳይ ነገር ነበር። ያገኙት ግን ኤርሚያስ እንደሚለው ሌላ ነው። ገበየሁም ቢሆን ነገሮችን የተረዳው በራሱ ሲደርስ ነው።
ሁለቱም ወጣቶች አውሮጳ ለመግባት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በሕህይወት ለመትረፋቸውም ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። ዛሬ ምነው እግሬን ባላነሳው ኖሮ የሚለውን ገበየሁ፤ ያኔ ከዚህ ውሳኔ ለመድረስ የገፋፋው ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ማጣቱ ነበር። ዛሬ እንደተመኘው ጀርመን ሀገር በፈለገው ፍጥነት ትምህርቱን መከታተል አልቻለም። ኤርሚያስም ቢሆን ከጠበቀው ኑሮ ገና እሩቅ እንደሆነ ይናገራል። ሌሎች ኢትዮጵያ የሚያዉቁት ሰዎች ግን ፌስ ቡክ ላይ « በጣም ተስማምቶኸል» ይሉታል። እውነታውን ሲናገርም የሚያምነው የለም። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ከተሞክሮዋቸው ለሌሎች የሚመክሩት ስደትን ጨርሶ አለመጀመሩን ነው። ምክንያቱም አንዴ እግር ከተነሳ መመለሻው ይከብዳል ነዉ የሚሉት።  አሁን የባህሩ ጉዞ ለከፋዉ አደጋ ተጋልጧል። ዓለም አቀፍ ሕይወት አድን ድርጅቾቱ ሥራ ካቆሙ በኋላ በርግጥ የስደተኛው ቁጥር ይቀንስ ይሆን? ከጊዜ ጋር የሚታይ ይሆናል። 


ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ


 

Audios and videos on the topic