ስደት፤ መከራዉ እና መፍትሔዉ | ኢትዮጵያ | DW | 27.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ስደት፤ መከራዉ እና መፍትሔዉ

ወደ የመን ይቀዝፉ የነበሩ 280 ኢትዮጵያዉያንና ሶማሊያዉያን ስደተኞች ከጀልባ ተወርዉረዉ ባሕር ዉስጥ ሰጥመዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ግፉን «ልብ የሚሰብር» ብለዉታል። የጉተሬሽ መስሪያ ቤቶች ባልደረቦች ግን ስደተኞችን በማንገላታት፤ በጥቅም እየደለሉ በመድፈር እና ጉቦ በመቀበል ይወቀሳሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 29:55

ውይይት፦ ስደት፤ መከራዉ እና መፍትሔዉ

ሶማሊያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የላትም።ሊቢያ የአሸባሪዎች፤ የወሮበሎች እና የዘራፊዎች መናኸሪያ ከሆነች አምስተኛ ዓመቷን አገባደደች።የመን በጦርነት፤ በረሐብ እና ኮሌራ ሚሊዮኖች ይረግፉ፤ይራቡ፤ ይታመሙባታል።ከኬንያ እስከ ደቡብ አፍሪቃ የተዘረጋዉ መስመር የአዉሬ፤የዘራፊ እና አጨበርባሪ መፈንጫ ነዉ።

አረቦች ስደተኛ ያባርራሉ። አሜሪካኖች እና አዉሮጶች ሥደተኛ እንዳይገባባቸዉ በራቸዉን ይዘጋሉ። የገባዉን ወደየሐገሩ ያግዛሉ። ኢትዮጵያዉን ግን ወደ ሁሉም ሥፍራ፤ በሁሉም አቅጣጫ ይሰደዳሉ። ካሰቡት ሳይደርሱ ይሞታሉ፤ይገደላሉ፤ ይደፈራሉ፤ ይገረፋሉ።

የካቲት 2007 የISIS አሸባሪዎች ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች ሊቢያ የገቡ ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን በካራ ገዝግዘዉ መገደላቸዉ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ዋሽግተን፤ ከለንደን እስከ ዱባይ የሚገኝ ኢትዮጵያዊን በቁጣ፤ ሐዘን፤ አሳድሞ ነበር።ኢትዮጵያዉን ግን ዛሬም ወደ ሜድትራኒያን ባሕር በገፍ ይሰደዳሉ።

በ2004 ታንዛኒያ ዉስጥ በአንድ የጭነት መኪና ኮንቴነር ዉስጥ የታጨቁ አርባ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሙቀት ተቀቅለዉ ማለቃቸዉ ሲሰማ ያለዘነ፤ያልደነገጠ፤ቀሪዎችን ያላስጠነቀቀ አልነበረም።በ2002 ከሶማሊያ የወደብ ከተማ ወደ የመን ሲቀዝፉ የተሳፈሩባት ጀልባ ሰምጣ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉንና

የሶማሊያ ዜጎች ማለቃቸዉ ለቀሪዎች ጥሩ ማስጠንቀቂያ በሆነ ነበር። ግን አልሆነም። ኢትዮጵያዉን በስደተኛ ወገኞቻቸዉ ሞት አዝነዉ ሳያበቁ የሌሎች ስደተኞችን መገደል፤ መደፈር፤ የሰዉነታቸዉን መተልተል፤ በረሐ ላይ መቅረት፤ ባሕር ዉስጥ መስመጥ ይሰማሉ። ግን ሌሎች ይሰደዳሉ።

ሶማሊያ፤ ኬንያ፤ ሱዳን፤ ደቡብ አፍሪቃ፤ የመን፤ ሊቢያ፤ግብፅ፤ እስራኤል፤ሌላዉ ቀርቶ ሮምና ካሌ የሚገኙ ስደተኞች የሚደርስባቸዉን በደል እና ግፍ ዘግናኝነት ይዘረዝራሉ።ከችግሩ ለመላቀቅም ድጋፍ ይማፀናሉ።ሌሎች ግን ይሰደዳሉ።

ከሁለት ሳምንት

በፊት ወደ የመን ይቀዝፉ የነበሩ 280 ኢትዮጵያዉያንና ሶማሊያዉያን ስደተኞች በአሸጋጋሪዎቻቸዉ ከጀልባ ተወርዉረዉ ባሕር ዉስጥ ሰጥመዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ግፉን «ልብ የሚሰብር» ብለዉታል። ለስደተኞች ድጋፍ ለማድረግ የተመሠቱት የጉተሬሽ መስሪያ ቤቶች ባልደረቦች ግን ስደተኞችን በማንገላታት፤ በጥቅም እየደለሉ በመድፈር እና ጉቦ በመቀበል ይወቀሳሉ። ስደት፤ መከራዉና መፍትሔዉ የዛሬው ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች