ሳይንስና እስፖርት | ጤና እና አካባቢ | DW | 27.08.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ሳይንስና እስፖርት

በአሁኑ ወቅት፣ በዓለም ውስጥ እጅግ ፈጣኑ ሰው፣ ጃማይካዊው አትሌት ዩሴይን ቦልት፣ መሆኑ የታወቀ ነው።

default

ዩሴይን ቦልት

በየብስ ከሚኖሩት ዐራዊትና እንስሳት ሁሉ እጅግ ፈጣኑ አቦሸማኔ መሆኑ የታወቀ ነው። ይህ የድመት ዘር፣ (ትልቅ ድመት ) አንበሳም ትልቅ ድመት ነው የሚባለው፤ አቦሸማኔ፣ በሰዓት 120 ኪሎሜትር ድረስ፣ እንደሚሸመጥጥ የታወቀ, ሲሆን ፣ ሰው፣ ምንም ያህል ቢፈጥን፣ ፍጥነቱ፣ ከአቦሸማኔ ጋር ሲነጻጸር፣ የዔሊና የጥንቸል ዓይነት ሩጫ ነው ማለት ይቻል ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት፣ በዓለም ውስጥ እጅግ ፈጣኑ ሰው፣ ጃማይካዊው አትሌት ዩሴይን ቦልት፣ መሆኑ የታወቀ ነው። 100 ውን ሜትር ርቀት፣ በ 9,69 ሴኮንድ ያጠናቀቀው፣ ብዙ እየተነገረለት ያለው እስፖርተኛ!

የቦልት ፍጥነት እንዴት ይገመገማል? ቦልት፣ ቤይጂንግ ውስጥ፣ በ 100 ሜትር እሽቅድድም ፣ ከፊሉን ርቀት፣ ማለትም፣ ከ 50 -80 ሜትር፣ በአማካዩ፣ በሰዓት ፣ 43,9 ኪሎሜትር ፍጥነት በመፈትለክ ነው ያጠናቀቀው። ለጠቅላላው 100 ሜትር ርቀት፣ አማካዩ ፍጥነት በሰዓት 37,15 ኪሎሜትር ነበረ ማለት ነው። ቦልት፣ የግቡን መሥመር ከማቋረጡ በፊት፤ 20ዎቹን ሜትሮች በመሃል በነበረው በሰዓት 43,9 ኪሎሜትር ፍጥነት ቢፈጽም ኖሮ ፣ 100ውን ሜትር በ9,69 ሳይሆን በ 9,60 ሴኮንድ ማጠናቀቅ ይችል እንደነበረ፣ የእስፖርት ሳይንቲስቶች ይገልጻሉ።

ለመሆኑ እስፖርተኞች ምን ያህል መራመድ፣ መሮጥ፣ መዝለልና ክብደትም ማንሣት ይችላሉ? የሰው ልጅ አካላት አደጋ የሚያጋጥማቸው ምን ደረጃ ላይ ሲደረስ ነው? መለኪያ አለ ወይ? አዎ! መለኪያ አለ፤ በእስፖርት ሳይንቲስቶች ተጠንቶ የተደረሰበት!

ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ በጀርመን ሀገር በእሽቱትጋርት ከተማ የሚገኘው የዩኒቨርስቲው የእስፖርት ሳይንሳዊ ተቋም፣ በመሽከርከር፣በመዝለል፣ አንድ አትሌት ያለውን ኃይልና ፍጥነት፣ የጀርባና የሆድ ዕቃ ጡንቻዎች ጉልበት መጠን ፣ ሁሉንም መለካት ይቻላል። የትኛው ጡንቻ፣ ምን ያህል ልምምድ እንደሚያሻው፣ በዚሁ መሣሪያ አማካኝነት ማመላከት የሚቻል ሲሆን፣ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመው እስፖርተኛም፣ ተመልሶ ጡንቻውን ለተወሰነ የእስፖርት ውድድር ብቁ ማድረግ የሚቻልበትን ዘዴ ያውቀዋል ማለት ነው።

እዚህም ላይ፧ የኦሊምፒክ እስፖርት ተወዳዳሪዎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። የተጠቀሰው የሽቱትጋርቱ ዩኒቨርስቲ የእስፖርት ተቋም፧ የተለያዩ እስፖርተኞችን የጡንቻ ኃይል የሚለካው፧ እንበል፧ አንድ እስፖርተኛ፧ ECG በመሰለ መሣሪያ፧ በአንድ ልዩ ወንበር ቀጥ ብሎ እንዲቀመጥ ተደርጎ፧ ትከሻዎቹ ላይ ወፈር ያሉ መሸፈኛዎቸ ተደርገውለት፧ በሚሰጠው ትእዛዝ መሠረት በኃይል ከተነፈሰ በኋላ ባለ- በሌለ ኃይሉ ወደፊት እስከቻለበት ቅጽበተ ድረስ ሲንቀሳቀስ ፧ መሣሪያው፧ እስፖርተኛው የቱን ያህል ጉልበት እንዳለው ይመዘግባል። በእንዲህ ዓይነቱ እንቅሥቃሤ እንበል 317 ነጥብ ያስመዘገበ እስፖርተኛ 317 Newtonmeter የጡንቻ ኃይል አለው ማለት ነው።የአንድን እስፖርተኛ የጡንቻ ክፍሎች ኃይል መጠን በ «ኒውተንሜትር« አማካኝነት ማሳወቅ መቻሉ፧ ለእስፖርተኛ ብቻ ሳይሆን ስለ እስፖርት ደንታ ለሌለው ሰውም ቢሆን ጠቃሚ ነው። አሎሎ ለመወርወር፧ ከፍተኛ ዝላይ ለመዝለል፧ መቶ ሜትር ሽምጥ ሩጫ፧ ለመሮጥ፧ የተለያዩ ጡንቻዎች የላቀ አስተዋጽዖ እንደማድረጋቸው መጠን የተፈለገ ውጤት ለማስመዝገብ፧ የተወሰነ ጡንቻን የጉልበት መጠን ማወቁ ለእስፖርተኞችና ለአሠልጣኞች የተለየ ትርጉም አለው። ከጡንቻ ጉልበት መጠን ሌላሥነ-ልቡናም ተጨማሪ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑን የእስፖርት ሳይንስ ተበብት አልካዱም። ከተመልካቾች የሚሰጥ የጭብጨባ ድጋፍ፧ ወይም የአሠልጣኞች የማበረታቻ ቃላት ለአንዳንድ እስፖርተኞች፧ ቀላል የማይባል እገዛ ነው የሚያደርጉት። ቀለል ላሉ የአትሌቲክስ ዓይነቶች 188-216 ኒውቶሜትር፧ የጡንቻ ጉልበት መጠን፧ ለጉዳት የሚዳርግ አይደለም። አሎሎና የመሳሰሉትን ለመወርወር ግን ተፈላጊ የሆኑ ጡንቻዎችን ለይቶ ይበልጥ ማጠንከር የሚቻልበትን የእስፖርት ዓይነት መሥራት የግድ ይላል።

የሰው ፍጥነት፧ ምጥቀት፧ ጉልበት፧ ገደቡ፧ ምን ላይ ድረስ ሊሆን ይቻላል? በእሽቱትጋርት ዩኒቨርስቲ፧ የእስፖርት ሳይንሳዊ ተቋም ባልደረባ፧ ፕሮፌሰር ዶክተር ዊንፍሪድ አልት፧ እንዲህ ይላሉ።.......

«አንድ መቶ ሜትር፧ ርቀትን፧ በዘጠኝ ወይም ስምንት ሴኮንድ ማጠናቀቅ፧ ከቶ አንችልም። ምንም ዓይነት ሁለንተናዊ መሻሻል ብናሳይ፧ ቢያንስ በሚመጡት መቶ ዓመታት ውስጥ ልናሳካው አንችልም። ነገር ግን ፍጹም ገደቡ፧ እዚህ ድረስ ነው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም። ምክንያቱም፧ በየጊዜው የተለያዩ ቅድመ-ግዴታዎችን የሚያሟሉ አስደናቂ አትሌቶች ብቅ-ብቅ ማለታቸው አይቀርምና!

በ አንድ መቶ ሜትር ሩ፧ በምድር ዝላይም ሆነ በከፍታ ዝላይ፧ በጥቂቱም ቢሆን ወደፊት አዳዲስ ክብረ-ወሰን መመዝገቡ አይቀሬ ነው። ሆኖም ግን፧ በአቃላይ፧ በትክክል፧ ይህ ነው ብለን፧ ለመጥቀስም ሆነ በስሌት ልንገልጸው የምንችል አይደለም።«

የጥንቱና የዛሬው ሰሐራ፧

በሳሔል መቀነት ከሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች አንዷ ኒዠር፧ በአሁኑ ዘመን፧ በዓለም ውስጥ ሣር-ቅጠሉ የተመናመነባት ደረቅ ሀገር ስለመሆኗ ነው የሚነገረው። ስለጥንታዊው ሰውም ሆነ ቅድመ-ሰው የሚመራመሩ ጠበብት፧ እንደሚያስረዱት ከሆነ፧ ከ አሥር ሺ ዓመት በፊት የዝች ሀገርም ሆነ የአካባቢው ገጽ ፍጹም የተለየ እንደነበረ ለመገመት ከባድ አይሆንም። በቱዓሬጎች ቋንቋ፧ «ጎቤሮ« የሚል ስያሜ የተሰጠውን አንድ ጣቢያ፧ ከስምንት ዓመት በፊት ያገኙትና አሁን በዚያ ስለተገኘው ዝርዝር ዘገባ በማቅረብ ላይ የሚገኙት የቺካጎ ዩኒቨርስቲ የቅሪተ-አካል ተመራማሪ ፖል ሴሬኖ፧ የዳይኖሰር አጽም ሲፈልጉ፧ በድንገት፧ የሰውና የእንስሳት እንዲሁም የዐራዊትና የአሣ አጽም፧ በተጨማሪም ቅርሳ-ቅርስ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ሰሃራ አረንጓዴ በነበረበት ዘመን፧ የኑት ሰዎች፧ ሁለት ሠፈሮች፧ የአንድ ሺ ዓመት የዕድሜ ልዩነት ያላቸው፧ መሆኑንና አንደኛው ጣቢያ፧ ቢያንስ ሁለት መቶ የመቃብር ቦታዎች ን ያቀፈ መሆኑን ከሰሬኖ ጥናት ለመረዳት ተችሏል። አስደናቂ ያሉት፧ አንደኛው፧ አንዲት ሴትዮና ሁለት ልጆቻቸው፧ ከአምስት ሺ ዓመታት ገደማ በፊት፧ አበባ በተጎዘጎዘ መቃብር ውስጥ እንዲቀበሩ ተደርጎ በዚያ ሊገኙ የቻሉበት ሁኔታ ነው። የመጀመሪያው ጣቢያ መካነ-መቃብር፧ በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎች«ኪፊያንስ« የሚባሉት፧ ረዣዥሞችና ጠንካሮች አዳኞች እንደነበሩ ፍንጭ መገኙቱን፧ በዚያ አካባቢ የነበረ ግዙፍና ጥልቅ ሐይቅ፧ ከ ስምንት ሺ ዓመት ገደማ በፊት ሲደርቅ፧ ኑዋሪዎቹ፧ ቦታውን ለቀው፧ ወደ ሌላ ሥፍራ ሳይፈልሱ እንዳልቀሩም የተመራማሪው’ ጥናት ያስረዳል።

ጎቤሮ አካባቢ፧ ከ ሰባት ሺ ዓመት ገደማ በፊት፧ አንስቶ እስከ ዐራት ሺ አምስት መቶ ዓመት፧ ባለው ጊዜ መካከል፧ የሠፈሩት ሁለተኛ ዙር ኑዋሪዎች፧ በአደን፧ ከብት በማርባትና አሣ በማጥመድ የሚተዳደሩ፧ በቁመናም ረገድ አጠር ያሉ ሰዎች ነበሩ። የመጀመሪያዎቹና የኋለኞቹ፧ ሠፋሪዎች፧ ሁለቱም ወገኞች፧ የተውአቸው ከሸክላ የተሠሩ ማብሰያ እቃዎች፧ አሣ ማጥመጃ መሣሪያዎችና ጌጣ-ጌጦችም ተገኝተዋል።

በዓለም ውስጥ ካሉት ምድረ-በዳዎች ሁሉ በስፋት ወደር የሌለው፧ ሰሐራ ሲሆን፧ አሁን በያመቱ ይበልጥ እየሰፋ በሳሄል መቀነት የሚገኙትን አገሮች እያስጨነቀ ነው።

ከ 12,000 ዓመት ገደማ በፊት በምድር ምኀዋር ረገድ ያጋጠመ ለውጥ፧ የዝናም ወቅት ይበልጥ ወደ ሰሜን እንዲገፋ ማድረጉ ነው የሚነገረው። በመሆኑም ከግብፅ እስከ ሞሪታንያ ድረስ፧ ወቅታዊ ዝናም ይጥል እንደነበረ ነው ተመረማሪዎች የሚገልጹት። ከዚያም የተወሰኑ አምዐት፧ በእንዲህ ከቀጠለ በኋላ፧ ከ 8 ሺ ዓመት በፊት ዝናሙ ከነአካቴው ተቋርጦ፧ ለሰሃራ አሁን ያለውን ገጽ ለማግኘት ቻለ። ከተፈጥሮ የአየር ለውጥ ባሻገር፧ የሰው፧ ተፈጥሮን ክፉኛ ማራቆት፧ ብዙ ሰሓራዎች እንዲከሠቱ ከሚያደርግበት የጥፋት ጎዳና እንዲወጣ፧ በየጊዜው የሚነገረው ማስጠንቀቂያ ሰሚ ካላገኘ፧ ምድራችን ወደ ጨረቃነት ብትለወጥ የሚያስገርም አይሆንም።