1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ሐረርጌ 61 ሰዎች ተገድለዋል፤ 735 የመኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2010

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምዕራብ ሐረርጌ ነዋሪዎች ቁጣ እና ሐዘን ተደበላልቆ ተጭኗቸዋል። "አካባቢው ላይ ያለው የሕዝቡ ስሜት መጥፎ ነው" ይላሉ አስተያየታቸው የሰጡ የዞኑ ነዋሪ። "ምንም የተረጋጋ ነገር የለም።" የሚሉት ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ግለሰብ "የደኅንነት ዋስትና ጠፍቷል" ሲሉ ያክላሉ።

https://p.dw.com/p/2pavb
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

በምዕራብ ሐረርጌ የተረጋጋ ነገር የለም-ነዋሪዎች

ከታኅሳስ 5 እስከ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. መረጋጋት ርቋቸው የነበሩት የምዕራብ ሐረርጌዎቹ ሐዊ ጉዲና እና ዳሮ ለቡ ወረዳዎች የጸጥታ አስከባሪዎች ተሰማርተዋል። የወረዳዋ ነዋሪዎች እና የዞኑ አስተዳደር ሰራተኞች እንደሚሉት ወረዳዎቹ እሁድ ታኅሳስ 8 እና ሰኞ ታኅሳስ ዘጠኝን በሰላም ውለዋል።

በሐዊ ጉዲና ወረዳ የሚገኙት ታዖ እና ኢብሳ ቀበሌዎች እንዲሁም የዳሮ ለቡዎቹ የቲ እና ዱረቲ ቀበሌዎች የኹከት ወላፈኑ ቀድሞ የደረሳቸው ናቸው። የምዕራብ ሐረርጌ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዱረዛቅ አሕመድ "ጦርነት" ሲሉ በጠሩት ክስተት ሰዎች መሞታቸውን፣መቁሰላቸውንና የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

"ባልታወቀ ሁኔታ በሶማሌ በታጠቀ ኃይል ታኅሳስ 6 ላይ በጠዋት ተኩስ ይከፈታል። ተኩስ ይከፈትና ሕዝቡ ከዛ ይሰደዳል። ሲሰደድ የታጠቀው የሶማሌ ኃይል ብዙ ቤቶችን ያቃጥላል ማለት ነው። በተመሳሳይ ሰዓት ነው ዒብሳ ላይም ጦርነቱ የተከፈተው። በዛ ሒደት ብዙ ቤቶች ተቃጠሉ።አርብ እና ቅዳሜ ታኅሳስ ስድስት እና ሰባት በሁለቱ ቀን የሰው ሕይወት በተለይ በኦሮሞ ወደ 29 የሚሆን የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ወደ 17 የሚሆኑ ቆስለዋል። ወደ 735 የሚሆኑ ቤቶችም ተቃጥለዋል።"

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እሁድ በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ሐተታ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በተቀሰቀሰው ኹከት 61 ሰዎች መገደላቸውን አትተዋል። ከሟቾቹ መካከል 32ቱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔረሰብ አባላት ናቸው። ኩነቱን ጠቅላይ ሚኒሥትር ሐይለማርያም ደሳለኝ "የጅምላ ግድያ" ብለውታል። "ችግሩ ኢጋዱሎ የምትባል ቀበሌ ላይ ነው። ይኼ ከጦርነቱ ጋ ወይም ከችግሩ ጋ የማይገናኝ ቀበሌ ነው።" የሚሉት አቶ አብዱረዛቅ አሕመድ "ከሞቱት ውስጥ አንዱ ወንድሙ በሌላ ቀበሌ ችግሩ በሌለበት ቀበሌ የግል እርምጃ" ወስዷል ሲሉ ግለሰባዊ በቀል እንደሆነ ተናግረዋል። "እርምጃው ተገቢ ነው ማለት አይደለም። እርምጃውን እናወግዛለን። ማንኛውም ዜጋ እንዲሞት አንፈቅድም። አሁን ያንን ጉዳይ የሚያጣራ ኮሚቴ ተዋቅሯል።" ሲሉም አክለዋል።

በጉዳዩ ላይ የፌድራል መንግሥት እና የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።  ጠቅላይ ምኒሥትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ-ኃይል መቋቋሙን ገልጠዋል።

የሐዊ ጉዲና ወረዳ ከአዲስ አበባ 519 ኪ.ሜ. ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር መቀመጫ ጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ደግሞ 180 ኪ.ሜ. ትርቃለች። የከተማ ነዋሪዎችም ሆኑ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ እንደሚሉት ወረዳዋ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔረሰብ ተወላጆች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች አንዷ ነበረች።

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልሎች መካከል የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ከቀሰቀሰው ኹከት በኋላ ግን እንደ ቀድሞዋ አይደለችም። ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የወረዳዋ ነዋሪ "ምንም የተረጋጋ ነገር የለውም። መውጫ የለንም። መግቢያ የለንም። ኑሯችን በጦር የተያዘባት ናት። እኛ 15 ቀን አንድ ገበያ ቆመን አናቅም። ትምህርት ቤት ከተዘጋ 15 ቀን አለፈ። ምንም የሚንቀሳቀስ ሰው የለም።" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አብዱረዛቅ በወረዳዎቹ የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ከቀደመው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ጋር ያገናኙታል። ኃላፊው ወረዳዎቹ ከሶማሌ ክልል ጋር ባይዋሰኑም እንኳ ድንበር የሚሻገሩ ታጣቂዎች ጥቃት ሲፈፅሙ ቆይተዋል ሲሉ ይከሳሉ። በሁለቱ ክልሎች መካከል በተቀሰቀሰው ውዝግብ በርካቶች ሞተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩም ተፈናቅለዋል። ችግሩ መቼ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል እስካሁን በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። አቶ አብዱረዛቅ እንደሚሉት ለሕግ የሚያቀርብ እና የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የሚመልስ እና የሚግዙ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ