ሣምንታዊ የስፖርት ጥንቅር | ስፖርት | DW | 03.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሣምንታዊ የስፖርት ጥንቅር

በጃፓኑ ማራቶን ኢትዮጵያ ትናንት ዳግም ድል ተቀዳጅታለች። በጀርመኑ የቡጢ ፍልሚያ አርቶ አብርሃም በስተመጨረሻ የተነጠቀውን ቀበቶ ማስመለስ ችሏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ እየገሰገሰ ነው። ናይጀሪያዊው ካኑ የልብ ቀዶ ጥገና ተደረገለት።

ኢትዮጵያዊው አትሌት በዙ ወርቁ ጃፓን ውስጥ በተደረገ የማራቶን ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። እዛው ጃፓን ውስጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባለፈው ሳምንት በማራቶን ሩጫ ድል ማስመዝገባቸው ይታወሳል። ጀርመን ውስጥ በተደረገ የቡጢ ፍልሚያ የ 35 ዓመቱ አርቶ አብርሃም ቀበቶውን ማስመለስ ችሏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ እንደ ቸልሲ የቀናው የለው። የጀርመን ቡንደስ ሊጋ፣ ላሊጋ እና ሴሪኣ ግጥሚያዎችንም እንመለከታለን።

ጃፓን ውስጥ ትናንት በተደረገ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት በዙ ወርቁ ማሸነፉ ታውቋል። የጃፓኑ ተፎካካሪ ሳቶሩ ሳሳኪ በስተመጨረሻ ላይ ኬንያዊው ቪንሰንት ኪፕሩቶን በመቅደም ሁለተኛ ለመሆን ችሏል። በውድድሩ የመጨረሻ ዙር ተፎካካሪ የነበሩት ሶስቱ ተወዳዳሪዎች ለብቻ ተነጥለው ነበር። ውድድሩ ሊጠናቀቅ አራት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት በዙ እና ቪንሰንት ጃፓናዊውን ወደ ኋላ ጥለው ፉክክሩን በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል አደረጉት። ቪንሰንት ከበዙ ጋር አንድ ኪሎ ሜትር ያህል አብሮ ከሮጠ በኋላ ግን እጅ መስጠቱ አልቀረም።

Miyagi Stadion in Japan

ቀሪውን ሶስት ኪሎ ሜትሮች በዙ ወርቁ ፍጥነቱን እየጨመረ ያለማንም ተፎካካሪ ለማጠናቀቅ ችሏል። የማራቶን ሩጫ ፉክክሩ በሚጠናቀቅበት ስታዲየም ውስጥ ጃፓናዊው ሳቶሩ ኃይሉን በማሰባሰብ ቪንሰንት ኪፕሩቶን ቀድሟል። በእዚህ የሩጫ ውድድር ጃፓናውያን ጎልተው ታይተዋል። ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ድረስ ተከታትለው በመግባት በስታዲየሙ የታደሙትን በርካታ ጃፓናውያን አስደስተዋል።

ከአትሌቲክስ ሠላማዊ ፍልሚያ ሳንወጣ ወደ ቡጢ ውድድር እንሻገር። እዚህ ጀርመን ማግደቡርግ ውስጥ የረዥም ጊዜ ባለድሉ አርቶ አብርሃም ተፎካካሪው ሮበርት ስታይግሊዝን በመካከለኛ ከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ በማሸነፍ የተነጠቀውን ቀበቶ ማስመለስ ችሏል። የአርመንያ ዝርያ ያለው የ35 አመቱ ጀርመናዊ አርቶ አብርሃም ከትውልደ ሩሲያዊው ጀርመናዊ ተፎካካሪ የ32 ዓመቱ ሮበርት ቀበቶውን ባስመለሰበት ምሽት 7500 ተመልካቾች ታዳሚ ሆነው ፍልሚያውን ተከታትለዋል።

«በቃ በቀላሉ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ አሁን ወደ እቤት መሄድ እችላለሁ፤ እዚያ እናቴ ድንች ጠብሳ ትጠብቀኛለች።»ሲል አሸናፊው ደስታውን ከቤተሰቡ ጋር ሊያጣጥም መቸኮሉን ገልጿል። ተሸናፊው ግን ሽንፈቴን አልቀበለም፤ የዳኛ ስህተት ነው ሲል አማሯል። አርቶ አብርሃም ሮበርት ስታይግሊዝን በዳኞች ውሳኔ 2 ለ1 በሆነ ነጥብ ነው ያሸነፈው።

አሁን የእግር ኳስ ጨዋታ ውጤቶችን እናቀርብላችኋለን። በእንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምር። ከትናንት በስትያ ፉልሀምን 3 ለ 1 የረታው ቸልሲ የፕሬሚየር ሊጉን የደረጃ ሠንጠረዥ በ63 ነጥብ በአንደኛነት እየመራ ይገኛል። ሊቨርፑል የቸልሲ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ባደረገው ግጥሚያ ሳውዝሐምፕተንን 3 ለ ባዶ አሰናብቶ የደረጃ ሠንጠረዡ ላይ በ59 ነጥብ ሁለተኛ መሆን ችሏል። በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ስቶክ ሲቲን 1 ለዜሮ አሸንፏል።

የቸልሲው አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ

የቸልሲው አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ

57 ነጥብ ይዞ በአራተኛ ደረጃ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ወደ አራተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። የፊታችን ቅዳሜ ከአስቶን ቪላ ጋር ይገናኛል። ሁለት ሠዓት ቀደም ብሎ 45 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሠንጠረዡ ላይ በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ዌስት ብሮሚች አልቢዮን ይገጥማል።

እስካሁን ፕሬሚየር ሊጉን የሊቨርፑሉ ግብ አዳኝ ሉዊስ ሱዋሬዝ እየመራ ይገኛል። 24 ግቦችን ከመረፍ ለማሳረፍ ችሏል። በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ሊቨርፑሎች የሚደርስባቸው ታጥቷል። ሌላኛው አጥቂ ዳኒኤል ስቱሪጅ 18 ግቦችን በማስቆጠር ሱዋሬዝን ይከተላል። 15 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የማንቸስተር ሲቲው ሰርጂዮ አጉዌሮ ሶስተኛ ነው።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙንሽንን የሚስተካከለው አልተገኘም። ከትናንት በስትያ ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለት ሻልካን 5 ለ 1 እንዳይሆን አድርጎ ሸኝቶታል። ባየር ሙንሽን በደረጃ ሠንጠረዡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ20 ነጥብ ርቀት 65 ነጥቦችን ሰብስቦ ዋንጫውን በእጁ እንደሚያስገባ ከወዲሁ እያስመሰከረ ነው። የባየር ሙንሽኑ አጥቂ ሆላንዳዊው አርያን ሮበን ከድል በኋላ ለቡድኑ ያለውን አድናቆት ገልጿል።

«ከፍተኛ አድናቆት ለቡድናችን። ጨዋታችን ድንቅ ነበር። በፈጣን የማጥቃት ስልት ሻልካዎችን ትንፋሽ በማሳጣት እንዳይጫወቱ አድርገናቸዋል። በዛ ላይ አራት ግቦችን ስታስቆጥር ተወኝ ባክህ የመጀመሪያው አጋማሽ እስከዛሬ ከገጠመኝ ሁሉ ድንቁ ነበር። » በማለት ገና ከመጀመሪያው አጋማሽ አንስቶ ባየርን ሙንሽን አይሎ እንደነበር ጠቅሷል።

አርያን ሮበን ሻልካ ላይ ሲያገባ

አርያን ሮበን ሻልካ ላይ ሲያገባ

ከትናንት በስትያ ባየር ሌቨርኩሰን ማይንስን 1 ለባዶ አሸንፏል። ፍራይቡርግ ከሔርታ ቤርልን ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ዶርትሙንድ ኑርንበርግን 3 ለዜሮ አሸንፏል። ቦሩስያ ሞንሽንግላድባህ ከአይንትራኅት ብራውንሽቫይግ፤ እንዲሁም ሐኖቨር ከአውስቡርግ አንድ እኩል አቻ ተለያይተዋል። ትናንት አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሽቱትጋርትን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ፤ ሆፈንሀይም ዎልፍስቡርግን 6 ለ 2 የጎል ጎተራ አድርጎታል።

በደረጃ ሠንጠረዡ ባየር ሌቨርኩሰን ከባየር ሙንሽን በ22 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ43 ነጥቦች በመወሰን በአራተኛነት ይገኛል። ሻልካ ከሌቨርኩሰን የሁለት ነጥቦች ነው ልዩነቱ። እንደ ባየር ሙንሽን ግስጋሴ ከሆነ ግን በቡንደስ ሊጋው የዋንጫ ፍልሚያው ላይ ለመድረስ አንድም ቡድን ተስፋ ያለው አይመስልም።

እስካሁን ድረስ 13 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የቦሩሲያ ዶርትሙንዱ ሌቫንዶቭስኪ ቡንደስ ሊጋውን በግብ ብዛት እየመራ ይገኛል። የባየር ሙንሽኑ ማንቹኪ በ12 ግቦች ይከተለዋል። የቦሩስያ ሞንሽንግላድባኹ ዴ አራዎ በ11 ግቦች ሶስተኛ ሆኗል።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ሁለት እኩል አቻ ተለያይቷል። ሌላኛው የላሊጋው ኮከብ ባርሴሎና አልሜሪያን 4 ለ 1 ቀጥቷል። ቫሌካኖ ቫሌንሺያን እንዲሁም ሴቪላ ሪያል ሶሴዳድን 1 ለ ዜሮ አሸንፈዋል። ቪላሪያ ከሪያል ቤቲስ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል።

12 ጨዋታዎች ሲቀሩት ሪያል ማድሪድ የሊጋውን የደረጃ ሰንጠረዥ በ64 ነጥብ ላሊጋውን እየመራ ይገኛል። ባርሴሎና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ62 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

አርቶ አብርሃም

አርቶ አብርሃም

የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 23 ከመረብ ባረፉ ግቦች ኮኮብ ግብ አግቢነቱን ተቆጣጥሯል። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዲዬጎ ኮስታ በ21 ግቦች ይከተላል። የባርሴሎናው አሌክሲስ ሳንቼዝ 16 ግቦችን ለማስቆጠር በመቻሉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጣሊያኑ ሴሪኣ ትናንት ጁቬንቱስ ኤስ ሚላልንን 2 ለ ባዶ፤ ላትሲዮ ፊዮሬንቲናን 1 ለ ዜሮ አሸንፈዋል። ቅዳሜ ዕለት ኢንተር ሚላን ከሮማ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።

የጁቬንቱሱ ካርሎስ ታቬዝ በ15 ግቦች የሴሪኣው ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ነው። የፊዮሬንቲናው ጁሲዬፔ ሮሲ በ14 ግቦች ሁለተኛ፤ የናፖሊው ጎንዛሎ ሂጉዋይን በ13 ከመረብ ያረፉ ግቦች ሶስተኛ ናቸው።

አጫጭር ስፖርት ነክ ዜናዎች

ናይጀሪያዊው አጥቂ ንዋንኮ ካኑ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መጠነኛ የልብ ቀዶ ጥገና ተደረገለት። የአርሰናል የቀድሞ አጥቂ የነበረው የ37 ዓመቱ ካኑ ቀዶ ጥገና እንደተደረገለት የተገለፀው ዛሬ ነው። የናይጀሪያ መንግሥት ሰሜኑና ደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል የተዋሀዱበትን መቶኛ ዓመት ትናንት ሲዘክር ልዩ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል ሲል ከዘረዘራቸው 100 ናይጀሪያውያን መካከል ካኑ ይገኝበታል።

የአፍሪቃ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ የሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ ተካሂዷል። ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሣላሃዲን ሣላህ ተሰልፎ ለሚጫወትበት የግብፁ ዋዲ ደግላ ቡድን ቀዳሚ የሆነችውን ግብ በቶጎው ዶዋኔስ ቡድን ላይ ሊያስቆጥር ችሏል። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ ዘግየት ብሎ ዶዋኔስ አቻ የምታደርገውን ግብ ከመረብ አሳርፏል።

በ16 ምድብ የተደለደለው የአፍሪቃ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ የመልስ ጨዋታ በሳምንቱ ማብቂያ ላይ እንደሚካሄድ ታውቋል። አሸናፊው ሆኖ ዋንጫ ለሚያነሳ ቡድን 480,000 ዩሮ ሽልማት መዘጋጀቱም ተዘግቧል።

ሊቨርፑል

ሊቨርፑል

የሊቨርፑሉ ባለቤት ጆን ኦንሪ የቡድናቸው አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬዝ ከእዚህ ቀደም በፈረመው ውል የ40 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ እንደተፈፀመ ዛሬ ለጋዜጠኞች ገለፁ። ሱዋሬዝ ከእዚህ ቀደም ሊቨርፑልን ለቆ ሊሄድ እንደሚችል በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል።

የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ቸልሲ ላይ መድረስ ለአርሰናል ሊከብድ ይችል ይሆናል አሉ። ቡድናቸውን በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ አንደኛ ማድረግ የተሳካላቸው የቸልሲው አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪህኖ በበኩላቸው ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫ የማግኘት ዕድሉ ተመናምኗል ሲሉ ተደምጠዋል።

የስፖርት ጥንቅራችን በተመለከተ አስተያየታችሁን ላኩልን፤ በዝግጅቱ በተለይ እንዲካተት የምትፈልጓቸውንም ነጥቦች ጠቁሙን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic