ምስጢራዊ መረጃዎችን የሚበይን ደንብ ሊጸድቅ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 02.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ምስጢራዊ መረጃዎችን የሚበይን ደንብ ሊጸድቅ ነው

የኢትዮጵያ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የመረጃ ነጻነት አዋጅን ለማስፈጸም ይረዳሉ ያላቸውን ደንብ እና መመሪያዎች ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ደንቡ የምስጢራዊ መረጃዎች ምደባን የሚደነግግ ሲሆን መመሪያዎቹ ደግሞ መረጃ ለማግኘት የሚፈጸም ክፍያ አወሳሰን እና መረጃ አሾላኪዎች ህጋዊ ጥበቃ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ናቸው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:52
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
02:52 ደቂቃ

ለመረጃ አሾላኪዎች ጥበቃ የሚያደርግ መመሪያም ተዘጋጅቷል

የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነትን የደነገገው ህግ ከጸደቀ ስምንት ዓመት ቢሞላውም አዋጁን ለማስፈጸም ይወጣሉ የተባሉት ደንቦች ግን ሳይዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ በአዋጁ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስለተከለከሉ መረጃዎች አጠባበቅና ምደባ እንደዚሁም ምስጢርነታቸው ስለሚቀርበት ሁኔታ ደንብ እንዲያወጣ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ምክር ቤቱ ለተለያዩ የመረጃ ዓይነቶች ተፈጻሚ ስለሚሆነው የክፍያ ተመን፣ ክፍያዎች ስለሚቀንሱበት ወይም መረጃ በነጻ ስለሚሰጥበት ሁኔታ ዝርዝር ደንብ እንዲያወጣም ይጠበቅበት ነበር፡፡

የቀድሞውን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ስልጣን እና ኃላፊነትን የተረከበው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት በአዋጁ የተጠቀሰውን ደንብ እና ለመረጃ አሾላኪዎች (whistleblowers) ህጋዊ ጥበቃ የሚደረግበትን ስርዓት የሚያስቀምጥ ተጨማሪ መመሪያ አዘጋጅቶ መጨረሱን አሳውቋል፡፡ የደንብ እና መመሪያ ረቂቆቹ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተላኩ ሁለት ወር እንዳለፋቸው በጽህፈት ቤቱ የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰኢድ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡

ምስጥራዊ እና ይፋ የማይደረጉ መረጃዎችን አስመልክቶ የተዘጋጀው ደንብ ምን ይዘት እንዳለው እና ጠቀሜታውን አቶ መሐመድ  አብራርተዋል፡፡ 

“ይፋ የሚደረጉ መረጃዎች የትኞቹ ናቸው? ይፋ የማይደረጉ መረጃዎች የትኞቹ ናቸው? ከዚህ ጋር ደግሞ በተገናኘ ይፋ የማይደረጉ መረጃዎች ደግሞ ለምን ያህል ጊዜ ነው ይፋ የማይደረጉት? የጊዜ ገደብ ጭምር በሚገልጽ እና በሚተነትን መልኩ የተብራራበት ነው፡፡ ይህ የትኛውን ችግር ይቀርፋል ብለን ስናይ ከግንዛቤ እጥረት የተቋማት ኃላፊዎችና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መረጃ ለሚዲያ ከመስጠት አኳያ ይሄ ይፋ የማይደረግ መረጃ ነው በሚል ዝግ እንዳያደርጉ ጭምር በግልጽ መረጃዎቹን ይፋ የማይደረጉ  (classified) አድርጎ የለየበት ነው፡፡ ይሄ በቀላሉ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው” ብለዋል፡፡

የመረጃ ነጻነት አዋጁ ስለመከላከያ፣ ደህንነት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የተመለከቱ መረጃዎች ክልከላ ሊጣልባቸው እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ካቢኔ ለህዝብ በይፋ እንዲገለጹ ከወሰናቸው መረጃዎች በስተቀር በካቢኔው ሰነድ ውስጥ የሚገኝ መረጃን ለማግኘት ወይም የመረጃውን መኖር ወይም አለመኖር ለማረጋገጥ የቀረበ ማንኛውም ጥያቄ ውድቅ እንደሚደረግም አውጇል፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ወይም የፋይናንስ ደህንነት ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል አሊያም መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስተዳደር ያለውን አቅም ሊያዳክም ይችላል የተባለ መረጃም እንዳይሰጥ ሊከለከል እንደሚችልም በአዋጁ ተካትቷል፡፡

በደንቡ በዝርዝር ከሚገለጹ ይፋ የማይደረጉ መረጃዎች ውጭ ያሉትን ለጠያቂዎች ለማቅረብ በክፍያ እና በነጻ የሚሰጡትን የሚለይ መመሪያ መረቀቁንም አቶ መሐመድ ይናገራሉ፡፡ መመሪያው ክፍያ የሚጠየቅባቸው መረጃዎችን አይነት እና የተመን ዝርዝሮችን የያዘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ጽህፈት ቤታቸው ያዘጋጀው መመሪያ ለመረጃ አሾላኪዎች ጥበቃ ለማድረግ የሚረዳ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

“በየተቋሙ ያሉ መረጃ አፈትላኪዎች እነርሱን ለመጠበቅና ለመከላከል፣ ዋስትና ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ነው” ብለዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቡንና መመሪያዎቹን ተመልክቶ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቁ እንደሚልካቸው አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic