ምርጫ በዝምባብዌ፣ | ዓለም | DW | 31.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ምርጫ በዝምባብዌ፣

የዝምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በዛሬው ምርጫ የሚሸነፉ ከሆነ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ። አያሌ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩት ሙጋቤ፣ ተፎካካሪአቸውን ጠ/ሚንስትር ሞርጋን ቻንጊራይን ለማሸነፍ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመኑም ገልጸዋል። በሃራሬ

 የዶቸ  ቨለ ዘጋቢ ኮለምበስ ማቭሁንጋ የላከውን ዘገባ --ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ፣ የዛሬው ምርጫ ለእርሳቸውና  ለ «ዛኑ-ፒ ኤፍ» ፓርቲያቸው ድልን የሚያጎናጽፍ እንደሚሆን ነው ያስረዱት። ከጠ/ሚንስትር ሞርጋን ቻንጊራይ ጋር  ሌላ ተጣማሪ አስተዳደር መሥረት የሚቻልበት አጋጣሚ ሁኔታ ይኖር እንደሁ ተጠይቀው ሲመልሱ፣---

«አይ፣ ያ አጋጣሚ በአሁኑ ጊዜ ይከሠታል ብለን አላከተትነውም ፤ ያለፈው ጊዜ ዓይነት  ሳይሆን የማያዳግም ዓይነት ውጤት እንደሚገኘው ነው የምንጠብቀው። ቀጥተኛ ውጤት ካላገኘን እንመክርበታለን። መተንበይ አንችልም። ተጨባጩን እውነታ እንደርስበታለን።  ይህ ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ እውነታ  ደግሞ የሚወሰነው፣  ድምጽ በሚሰጡ መራጮች  ነው።»

እ ጎ አ  በ 2008 ዓ ም ምርጫ፣ ያሁኑ ጠ/ሚንስትር ሞርገና ቻንጊራይ፤ የተቃውሞው ወገን መሪ ነበሩ። በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ፣ ሙጋቤን በነጥብ ቢበልጡም በሁለተኛው ዙር ፤ በሁለተኛው ዙር ወሳኝ ውድድር እ ጎ አ ከ 1980 ዓ ም አንስቶ በሥልጣን ኮርቻ ላይ የሚገኙትን በአፍሪቃ የረጅም ዘመን መሪ የሆኑትን አዛውንቱን ሙጋቤን ማፈናቀል አልተቻላቸውም። የአፍሪቃ መሪዎች የያኔውን ሁከት ያጀበውን ፣ ሙጋቤ ድል አድርጌአለሁ ሲሉ አዋጅ ያሰሙበትን የዳግም ምርጫ ውጤት አንቀበለውም  ነበረ ያሉት። ከዛሬው ምርጫ በፊት በመጨረሻው የምርቻ ዘመቻ  ንግግራቸው፣ ቻንጊራይ፤ ሥልጣኑን ከሙጋቤ መውሰዳቸው እንደማይቀር ነው የተናገሩት።

«በእኔ አስተዳደር ምሬታችሁ ይወገዳል። አዲሲቱን ዝምባብዊዌን በመገንባቱ ረገድ ተባበሩኝ። በመጀመሪያ በጠላትነት ዓይን እንተያይ ከነበረው ወገኖች ጋር ብስለትን በማሳየት፣  አዲሲቱን ዝምባብዌን  በመገንባቱ ረገድ እጅ ለእጅ  ተያይዘን ጉዞ እንቀጥል።ፕሬዚዳንት  ሙጋቤ፤ የጡረታ ዘመናቸውን ፤ በሰላምና ድሎት በትውልድ ሃገራቸው እንዲያሳልፉ ነው የምፈልገው።»

ሞርገን ቻንጊራይ፤ ሙጋቤ፤ የደቡባዊ አፍሪቃዊቷን ሀገር ኤኮኖሚ እንዲደቅ አድርገዋል በማለት ይወቅሳሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ሮበርት ሙጋቤ፣ ምርጫን የማያከብሩ አምባገነን እየተባሉ የሚሠነዘሩባቸውን አሉባልታዎች ዋጋቢስ አስተያየቶች ናቸው በማለት ለማጣጣል ሳይነሣሱ አልቀሩም ነው የተባለው። ሙጋቤ፣ የሚነቅፏቸው ወገኖች እንደሚሉት ምርጫዎችን እንደማያጭበረብሩ ነው የገለጡት።የዝምባብዌው ርእሰ ብሔር፣  በዛሬው ምርጫ ቢሸነፉ ከሥልጣን ይወርዱ እንደሁ ተጠይቀውም ሲመልሱ--

«ይህ መሆን ያለበት የተለመደ ጉዳይ ነው። ሁሉንም መሆን አትችልም ፣ ታሸንፋለህ ወይም ትሸነፋለህ። በምርጫው ካልቀናህ፤ ላሸነፉት እጅ መስጠት አለብህ። ካሸነፍህ፤ የተሸነፉት ወገኖች፣ ሽንፈትን   በጸጋ መቀበል ይኖርባቸዋል። ይህ ነው ፤ የምንደርገውም ይህንኑ ነው። ህጉ የሚለውን ተከትሎ መፈጸም!»

የ 89 ዓመቱ ጎምቱው የዝምባብዌ መሪ፤ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን፣ የምርጫውን ውጤት በተዓማኒነት የሚያቀርብ ገለልተኛ ተቋም ነው ሲሉም አስገንዝበዋል። የጠ/ሚንስትር ቻንጊራይ፤ ንቅናቄ ለዴሞክራቲክ ለውጥ(MDC) የምርጫ ኮሚሽኑ፤ በማጭበርበር የመራጮችን ድምጽ ፤ ለሙጋቤ «ዛኑ ፒ ኤፍ» ፓርቲ ይሰጣል በማለት መክሰሱ አልታበለም።  ከ 2 ሳምንታት በፊት፤ የዝምባብዌ መቅድማዊ ምርጫ በፀጥታ አስከባሪዎች ሲከናወን በህግ ከተፈቀደው በላይ ለ 3 ቀናት ተካሂዷል ነው ያለው-- MDC።

የዛሬው የዝምባባዌ ምርጫ፣ እ ጎ አ በ 2008 ዓ ም፤ ሁከት የተንጸባረቀበትና አነታራኪ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ፤ ሙጋቤና ቻንጊራይ ያቋቋሙት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት፣ አሁን በይፋ ያከትምለታል። የትኛው ፓርቲ በተናጠል መምራት የሚያስችለውን ውጤት ያስመዘግብ ይሆን ? ከዛሬ ጀምሮ በሚከተሉት 5 ቀናት ውስጥ በይፋ ይታወቃል።

ዛሬ ምርጫው እንዴት እየተካሄደ እንደሆነ፣ አንድ ከደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ (SADC)የተወከሉ ታዛቢ እንዲህ ነበር ያሉት--

«እስካሁን አንዳች የማስፈራሪያ እርምጃም ሆነ ሁከት አልታየም የድምፅ አሰጣጡ ተግባር  በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ነው። እርግጥ ገና በመሆኑ አጠቃሎ መናገር ያስቸግራል። በሌሎች የሀጋሪቱ ክፍሎች ምን እንዳለ አናውቅም። እስካሁን በሐራሬ ያየሁት ግን በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ነው።  

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic