ማኅበረሰቡና  የሴቶች ትግል | ባህል | DW | 29.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ማኅበረሰቡና  የሴቶች ትግል

ማኅበረሰቡና  የሴቶች ትግል

«ኢትዮጵያ ገና በሴቶችዋ ወይም ገና በእናቶችዋ መጠቀም ያልቻለች ሃገር ናት።ለዝያ ነዉ አሁንም ወደ ኋላ የምንወድቀዉ ፤ የምናዝነዉ ፤ የምናለቅሰዉ። እናቶቻችንን ፤ እህቶቻችንን፤ ሴት ልጆቻችንን በፖለቲካ ዓለምም ሆነ በሌሎች ዘርፍ የሚችሉትን ቦታ መስጠት ስላልቻልን ነዉ።ኢትዮጵያ ገና በሴቶችዋ በእናቶችዋ መጠቀም ያልቻለች ሃገር ናት።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:43

ማኅበረሰቡና የሴቶች ትግል

 

« ለዝያ ነዉ አሁንም ወደ ኋላ የምንወድቀዉ ፤ የምናዝነዉ ፤ የምናለቅሰዉ። እናቶቻችንን ፤ እህቶቻችንን፤ ሴት ልጆቻችንን በፖለቲካ ዓለምም ሆነ በሌሎች ዘርፍ የሚችሉትን ቦታ መስጠት ስላልቻልን ነዉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ዓለም ራስዋ በዩኤስ አሜሪካ እጩ ፕሪዚዳንቶቹ በህላሪ ክሊንተንና ዶናልድ ትራምፕ በኩል የሚታየዉ ነገር ዓለምም ራስዋ ገና የሴትን እድገትና የሴትን ሃሳብ መቀበል የደረሰችበት ዓለም ላይ አይደለንም። » ጋዜጠኛ ቅድስት ተስፋዬ  

በዩኤስ አሜሪካ ለሚካሄደዉ ፕሬዚደንታዊ  ምርጫ የሚወዳደሩት የዴሞክራት ፓርቲ  እጩዋ ሂለሪ ክሊንተን በሀገሪቷ ታሪክ እስከ ዛሬ ዋይት ሃዉስ የፕሬዚዳንት መንበርን ለመያዝ ከተወዳደሩት ፖለቲከኞች ሁሉ እጅግ የዳበረ ልምድ ያላቸዉ የሴት ፕሬዚዳንት እጩ መሆናቸዉ እየተነገረላቸዉ ነዉ። ባለፉት መቶ ዓመታት በዩኤስ አሜሪካ ታሪክ፤ ከ 200 መቶ በላይ ሴቶች ለፕሬዚዳንትነቱ ስልጣን ተወዳድረዉ እንደነበርስ ያዉቃሉ?  በዕለቱ ዝግጅታችን በአሜሪካ የፕሬዚዳንት እጩ ሴት ተወዳዳሪ ሴቶችን ታሪክና የኢትዮጵያ ሴቶች በፖለቲካዉ፤ በማኅበራዊዉ፤ እንዲሁም በኪነ-ጥበቡ ያላቸዉን ተሳትፎ እናያለን።    

በዩኤስ አሜሪካ ባለፉት መቶ ዓመታት ባለዉ ታሪክ ብቻ ከ 200 መቶ በላይ ሴቶች የሀገሪቱን ፕሬዚዳንትነት መንበር ይዘዉ ዋይት ሃዉስ ለመግባት ተወዳድረዋል። አሜሪካዉያን ሴት ፕሬዚዳንት እንድትመረጥ የፈለጉ ይመስላሉ ይላሉ አሜሪካዊትዋ የታሪክ ተመራማሪ ኤለን ፊትዝፓትሪክ። ዩኤስ አሜሪካን በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት ስለእስካሁኖቹ ፕሬዚዳንቶች ሀሪቱ በርካታ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ሥነ-ፅሁፎች ቢኖርዋትም እስከዛሬ ፕሬዚዳንት ለመሆን ስለተወዳደሩት ሴቶች ግን ብዙም የተባለ የተነገረ ነገር የለም። 

«እስከዛሬ በርካታ ሴቶች ዋይት ሃዉስ ለመግባት ተወዳደሩ እንጂ አሸንፈዉ የፕሬዚደንት መንበሩን አልያዙም። ለዚህም ነዉ በተለይ ስለፕሬዚዳንትነት  ጉዳይ የሚጽፉት የታሪክ አዋቂዎች ለእንስት ፕሬዚዳንት እጩዎች ብዙም ትኩረት ያልሰጡት።»

በሌላ በኩል ይላሉ አሜሪካዊትዋ የታሪክ ተመራማሪ ኤለን ፊትዝፓትሪክ ሴት የታሪክ ፀሐፊዎች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ እንብዛም ትኩረት አልሰጡም። ምክንያቱ ደግሞ  ሴቶች ብዙም ሚና ስላልነበራቸዉ ነዉ።  

የዩኤስ አሜሪካ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት አሜሪካዊትዋ  ቪክቶርያ ዉድሁል በጎርጎረሳዊዉ 1872 ዓ,ም  በሀገሪቱ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ለመቅረብ የተወዳደሩ ሴት ናቸዉ። በዚህ ዘመን አንዲት ሴት እንዲህ ላለዉ ዉድድር የመቅረብ ፈቃድ የላትም ነበር። በፖለቲካዉም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዩች ሴቶች በአሁኑ ወቅት በሴትነታቸዉ ከሚያጋጥማቸዉ እንቅፋቶች ለየት ባለ ሁኔታ የዛሬ 144 ዓመት ለምርጫ ለመቅረብ  ያጋጠማቸዉ ችግር ምን ይመስል ነበር? የታሪክ ምሁርዋ ኤለን እንደሚሉት አሜሪካዊትዋ ሴት ተወዳዳሪ  ዉድሁል እጅግ ከፍተኛ ፈተናን በወቅቱ ተጋፍጠዋል።

« ዉድሁል በዚያን ጊዜ ዛሬ እጩ ተወዳዳሪ ሴቶች ሲገጥማቸዉ ከምናየዉ ችግር እጅግ በበለጠ ሁኔታ ዉስጥ ታግለዋል። በዚያን ጊዜ ሌሎች መምረጥ መቻላቸዉ እንጂ ፤ ለዉድድር የቀረቡ በምርጫዉ አይሳተፉም ነበር። »

በዩኤስ አሜሪካ የነበረዉ የርስ በርስ ጦርነት አብቅቶ የፖለቲካ ተሃድሶ በነበረበት ወቅት ነጻነትን በተመለከተ ከፍተኛ ክርክር እንደነበረ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት ተጨማሪ አንቀጽ 14 እና 15 በተመለከተ የአሜሪካ ምክር ቤት አፍሮ አሜሪካዉያን የምርጫ መካፈል መብትን  እንዲሁም ዜግነትን በተመለከተ ከፍተኛ ክርክር ተካሂዶም ነበር። 

ይህ ዉይይትና ክርክር በሚካሄድበት ወቅት ነበር ሴቶች በምርጫ ድምፅ መስጠት እንዲችሉ ፍቃድ የተሰጠዉ ። እንድያም ሆኖ ለፕሬዚዳንት ምርጫ በእጩነት ለመቅረብ የመጀመርያዋ ተወዳዳሪ ዉድሁልስ የሚያቀርቡት ሃሳብም ተቀባይነት አላገኘም። አብዛኞች ዉድሁል በእጩነት በመቅረባቸዉ እጅግ ሲገረሙ ሌሎች ሴት ሆነዉ ለፕሬዚደንትነት ምርጫ በእጩነት መቅረባቸዉን ጨርሶ አልተቀበሉትም ነበር።  ቪክቶርያ ዉድሁል ለምርጫ ከቀረቡ  ከ 100 ዓመት በኋላ ለፕሬዚዳንትነት በእጩነት የቀረቡት ማርግሪት ቼዝ ስሚዝ መሆናቸዉን የታሪክ ተመራማሪዋ ኤለን ፊትዝፓትሪክ ይናገራሉ።  በጎርጎረሳዊዉ 1964 ዓ,ም  ለምርጫ በእጩነት የቀረቡት ስሚዝ በአሜሪካዉ ምክር ቤት፤ በሕግ መወሰኛና በሕግ መምርያ በኩል ቢመረጡም ለመንበሩ የምረጡኝ ዘመቻ ማስኬጃ በቂ ገንዘብ ስላልነበራቸዉ ምርጫዉን ማሸነፍ እንዳልቻሉ ነዉ የተዘገበዉ። ዛሬ እኝህ ሴት ምን ሚና ይኖራቸዉ ይሆን ?

« ማርግሪት ቼዝ ስሚዝ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመርያዋ የፕሬዚዳንት እጩ በመሆን ታሪክ ጽፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ ስሚዝ በሀገሪቱ ጠንካራና ትልቅ ከሚባለዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ መታጨታቸዉ ነዉ። ስሚዝ በፖለቲካዉ ረገድ በሳል እዉቀት ያላቸዉ ሴናተር ነበሩ።  ስሚዝ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃና እዉቀት ያላቸዉ ከክሊንተን በፊት ለፕሬዚዳንትነት በእጩነት የቀረቡ ነበሩ። »

በኢትዮጵያ በፖለቲካዉ በማኅበራዊዉ እና በባህላዊዉ ረገድ ትልቁን ሰንሰለት በጣጥሰዉ ፤ እመቃዉንና ተጽኖዉን ሁሉ ገፈዉ የወጡ ሰፊና ጠንካራ ታሪክ ያላቸዉ እንስቶች እንዳሉ እሙን ነዉ።  አገራችን በመሠረቱ ቀደም ባለዉ ዘመን ለሴቶች መብት በመስጠት የሴት ንግሥት ያየች ሀገር ናት ያለን ታዋቂዉ ገጣሚና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ልሳኑ፤ እንድያም ሆኖ ከቤት የሚጀምረዉን ችግር በጣጥሰዉ የወጡ  ሴቶች ጥቂት አይደሉም ይላል።   

በዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫንና የሂላሪ ክሊንተንን ትግል የምትከታተለዉ ጋዜጠኛ ትዕግስት ተስፋዬ እንደምትለዉ በኢትዮጵያ የጣይቱ ታሪክ የሚጠቀስ ቢሆንም፤ በኪነ-ጥበቡ ዉስጥ በማሳለፊ እንደምሳሌነት የምንጠቅሳቸዉ ሌሎች ሴቶችም አሉ  ስትል በዝርዝር ተናግራለች።    

በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት የቅርስና ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ ተመራማሪና የታሪክ ምሁር አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ በአገራችን ታሪክ ከሴቶች ጎልተዉ የወጡ ብዙ የተፃፈላቸዉ እቴጌ ጣይቱ መሆናቸዉን ገልፆአል።

 

በጎርጎረሳዊዉ 1972 ዓ,ም በዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራቶችን ወክለዉ የቀረቡት የመጀመርያዋ ሴት እጩ ተወዳዳሪ ሻርሊ ቺዝሆልም ይባላሉ። ሻርሊ በኮንግረስ የተመረጡ የመጀመርያዋ አፍሮ አሜሪካዊትም ናቸዉ። ሻርሊ ጥቁር በመሆናቸዉ በሌላ በኩል ዴሞክራቶችን ወክለዉ የቀረቡ ቢሆንም በሁለቱም ዘርፍ ታግለዉ በርካቶችን ወደራሳቸዉ መሳብ አልቻሉም። ገጣሚና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ልሳኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስርዓቱ የፈጠረዉን ጭቆና በጣጥሰዉ የወጡ ሴቶች አሉ ሲል ይገልፃል።

 ዓለም በስደት ቀዉስ በተዘፈቀችበት በአሁኑ ጊዜ የጀርንዋ መርሂ መንግሥት አንጌላ ሜርክ በጦርነት ከሃገሩ የተሰደደ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን ያለምንም ማቅማማት በሃገራቸዉ በጀርመን መጠለያ በመስጠት ከፍተኛ ስብዕና ያሳዩ በዓለምን እዉቅናን ያገኙ የዘመናችን ታዋቂ ሴት ፖለቲከኛ መሆናቸዉ የሚዘነጋ አይደለም።  ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic