1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

መንግስትና ቤተ ክርስቲያን በአዉሮፓ

ክርስቲያን ዴሞክራት የሚባሉት የተለያዩ የአዉሮፓ ሀገራት ፓርቲዎች አባላት ወደፊት ከሚፀድቀዉ የህብረቱ ህገ መንግስት ዉስጥ የሚካተተዉ አርማ ክርስትናንት የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት የሚለዉ ሃሳብ ዉድቅ መደረጉን ይተቻሉ።

የህገ መንግስቱ ዓርማ

የህገ መንግስቱ ዓርማ

ለአርማናት የተመረጠዉም ክርስትናንና የአይሁድ እምነትን የሚያንፀባርቅ ነበር። አዉሮፓችን የክርስትና ተፅዖኖ ያለባት ናት የሚሉት እነዚህ ወገኖች የአዉሮፓ የጋራ መተዳደሪያ ከእግዚአብሄር ጋ ግንኙነት ያለዉ እንዲሆን መደረግ አለበት ባይናቸዉ። ሆኖም በአብዛኛዎቹ የአዉሮፓ አባል ሀገራት ሃሳቡ ተቀባይነት አላገኘም።

ብራስልስ በሚገኘዉ የአዉሮፓ ፓርላማ መግቢያ አካባቢ የፓርላማ አባላቱን ስሜት ሊያረኩ ይችላሉ በሚል የማይገኝ ነገር የለም። የመፅሃፍ መሸጫ፤ ባንክ፤ የስፓርት ክለብ፤ እንዲሁም የልብስ ንፅህና መስጫ ስፍራዎችን መጥቀስ ይቻላል ከብዙ በጥቂቱ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የየትኛዉም እምነት መለያ ምልክት የሌለበት የፀሎት ቤት ከወደ ጥጉ ጎራ ሲሉ ያያሉ። በየሳምንቱ ሃሙስ ሃሙስ የፀሎት ልማድ ያለዉ የፓርላማ አባል ገብቶ እንደየእምነቱ ፀሎቱን ማድረስ ይችላል።

ምንም እንኳን ስታትስቲክስ ከ80 በመቶ በላይ የሆነዉ አዉሮፓዊ ከቤተክርስቲያን ወይም ከሃይማኖታዊ ማህበራት ጋ ትስስር እንዳላቸዉ ቢያሳይም፣ እግዚአብሄርን ለአዲሱ የአዉሮፓ ህብረት የግንኙነት ዉል ማለትም ለህገመንግስቱ በመሰረትነት አልተጠቀመበትም። መንግስትና ቤተክርስቲያንን ማለያየት የሚለዉ መመሪያም አከራካሪ ነዉ የሆነዉ። በአዉሮፓ ህብረት የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ተወካዩ ጆ ላይነን የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚቴዉ ሊቀ መንበር ናቸዉ። ህገ መንግስቱ ከአምላክ ጋ ግንኘት ይኑረዉ ወይስ አይኑረዉ በሚለዉ ክርክር ያለዉን እንዲህ ይገልፃሉ፤
«በመጨረሻ በፈረንሳይና በቤልጂግ ምክያንት ነዉ የፈረሰዉ። ሁለቱ ሀገራት በህገ መንግስታቸዉ መንግስትና ቤተ ክርስቲያንን እንዲለያዩ አይፈልጉም፤ ስለዚህ ሃሳቡን አልተቀበሉትም። ስለዚህ የአዉሮፓ ህብረትም ከእግዚአብሄር ጋ እንዲገናኝ ይሻሉ።»


ህገ መንግስቱን የሚያረቀዉ ኮሚቴ አባላት 75በመቶዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸዉ። ይሁዲና ሙስሊሞችም ቁጥራቸዉ ቢያንስም ስለተካተቱ የመገለል ስሜት አይሰማቸዉም ብለዉ ያምናሉ ሰፊዉን ቁጥር የያዙት ወገኖች። ጀርመን፤ ስፔን፤ ጣሊያንና ሌሎች ሀገራት በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ የእግዚአብሄር ስም ቢገባ ምንም ችግር የለም ብለዉ ነበር። በመጨረሻ ግን በጥቅሉ የአዉሮፓ ፓርላማ ይህን ሃሳብ ተቃወመ። ያም ሆኖ በአዉሮፓ ደረጃ ያለዉ ፖሊሲ አልቦ እግዚአብሄር ወይም እምነት አልባ አይደለም። የቤተክርስቲያንን መብት የሚያስጠብቁ ተሰሚነት ያላቸዉ ተሟጋቾች በብራስልስ ፅህፈት ቤት አላቸዉ።

ሃንስ ጌርት ፖይተሪንግ በፓርላማዉ የክርስቲያን ዲሞክራቶች ፕሬዝደንት በያዝነዉ የአዉሮፓዉያኑ ዓመት ማለቂያ ድረስ ይወጣል የሚባለዉ አዲሱ የአዉሮፓ ህብረት ህገ መንግስት ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ባያካትትም የሃይማኖትና የክርስትና እሴቶችን ማለትም መረዳዳትና ማህበራዊ ፍትህን ያንፀባርቃል ብለዉ ያምናሉ፤
«እነዚህ የእግዚአብሄር ስም እንዲጠራ ወይም የእምነት ምልክት እንዲጠቀስ ወይም የግሪኮች ፍልስፍናና የጥንት ሮማዉያን ህግ እንዲሰፍር የሚፈልጉ ወገኖች ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም። አሁን ግን በቀጥታ የክርስትና እሴቶች የክርስትና ሰብዓዊ አመለካከቶች በዚህ ህገ መንግስት አልተጠቀሱም።»


በእሳቸዉ አመለካከትም ምንም እንኳን ስመ እግዚአብሄር በቀጥታ ባይጠቀስም የእምነት እሴቱ በየዕለት ተዕለት ተግባራት ተካቶ ይታያል። ሲያብራሩትም በአዉሮፓ ለህይወት የሚሰጠዉ ግምት፤ ለአረጋዉያን የሚደረገዉ ክብካቤ፤ ዘረ መል ወይም ጂንን ለመለዋወጥ ለሚደረገዉ ሙከራ የሚታየዉ ጥርጣሬና ተቃዉሞ ሁሉ የእምነት እሴት ዉጤት መሆኑን ይገልጻሉ።


ጀርመን የአዉሮፓ ህብረትን የፕሬዝደንትነት መንበር በያዘችበት ወቅት በመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል አወያይነት ቀደም ሲል በተለያዩ አባል ሀገራት ተቀባይነትን አጥቶ የነበረዉ አዲሱ ህገ መንግስት ጉዳይ ዳግም አንሰራርቷል። በወቅቱም ፖላንድና ጣሊያን በተለየ መልኩ ነበር ህገ መንግስቱ ከአምላክ ጋ ግንኙነት እንዲኖረዉ የተሟገቱት። የጋራ ስምምነት ላይ ግን አልተደረሰም። ከዚያ ወዲህም የገፋ ዉይይት አልተደረገበትም። ቀደምቱን ታሪክ ለማዘከር በአዉሮፓ ዘመን ያስቆጠሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን እዚህም እዚያም ማየቱ የተለመደ ነዉ። ለአምልኮ የሚሄዱት ደግሞ ቁጥራቸዉ እዚህ ግባ አይባልም። በዚህም ምክንያት ይመስላል እነዚያ ለአምልኮ የተገነቡ ስፍራዎች ለሌላ አገልግሎት ሲዉሉ ይስተዋላል። ዛሬ የተለያየ እምነት በሚንፀባረቅባት አዉሮፓ ምንም እንኳን ክርስትናዉ ተፅዕኖ ያለዉ ቢመስልም ለህብረቱ በአርማ ደረጃ ለማስፈር የቀበዉን መከራከሪያ ያስተዋሉ አዉሮፓ ስንት እግዚአብሄር ያስፈልጋታል በሚል መተቸታቸዉ አልቀረም።