ልዕለ ጨረቃ ከ70 ዓመት በኋላ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 16.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ልዕለ ጨረቃ ከ70 ዓመት በኋላ

በመጠኗ እጅግ ግዙፍ የኾነች ጨረቃ ከ70 ዓመት ወዲህ ሰኞ ኅዳር 5 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. በመላው ዓለም ታይታለች። በተመሳሳይ ለምድር የቀረበች ጨረቃን ለመመልከት ከእንግዲህ 18 ዓመታትን መጠበቅ ያሻል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:03 ደቂቃ

ልዕለ ጨረቃ

እሁድ ኅዳር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ቦን፤ ጀርመን። ለወትሮው ድቅድቅ ጨለማ የሚውጠው የክረምት ወራት መዳረሻ እኩለ-ሌሊት በልዩ የጨረቃ ስርቅርቅታ ተውጧል። በጠራው ሰማይ ላይ ግዙፏ ጨረቃ እጅግ ደምቃ ትታያለች። በበነጋታው ሰኞ በመላው ዓለም ብዙዎች ከሰማዩ ጋር ቀጠሮ ይዘዋል። ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ስትናፈቅ የቆየችው ልዕለ ጨረቃ (supermoon) የምትወጣበት ማታ ነው፥ ሰኞ ማታ። ጨረቃ በዚህ ግዝፈቷ እና እጅግ ደማቅ ብርሃኗ ከታየች 70 ዓመታት ተቆጥሯል።

ከእንግዲህ ምናልባትም ለምድር እጅግ ቀርባ፤ በምሽቱ ፍንትው፣ ፏ! ብላ የም ትወጣበት ቀን አንድ ሕፃን ተወልዶ ለአቅመ-አዳም እስከሚደርስ የሚያስጠብቅ ይኾናል።  የሰኞ ኅዳር 5 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. የቦን ሰማይ ምሽት ቀጠሮ ያስያዘችው ጨረቃን በደመናው ጀቡኖ አለፈ። የደቡብ አፍሪቃ ሰማይ ግን በትዮጵያውያኑ የፊዚክስ ሊቃውንት ላይ አልጨከነም። በጠራው ሰማይ ልዕለ-ጨረቃን ሲያስቃኛቸው አምሽቷል፤ የሚያካፍሉን ይኖራል።  

የዕለተ-ሰኞ የጨረቃ ልዩ ገጽታን ለማማተር ከእንግዲህ 18 ዓመት መጠበቅ ያሻል። ከወትሮው በተለየ መልኩ ደምቃ እና ገዝፋ የታየችው ጨረቃ ለምድር 30,000 ኪሎ ሜትር ቀርባ እንደነበር ስነ-ፈለክ ሊቃውንት ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ጨረቃ በዚህ መልኩ ደምቃ የታየችው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1948 ዓ.ም. ነበር። በእርግጥ እጅግ የደመቀች እና የገዘፈች ጨረቃን፦ ማለትም (supermoon)በየ14 ወራቱ መመልከት ይቻላል። እንደ ሰኞ ዕለቱ ለምድር በጣም የቀረበች ደማቅ ጨረቃን ከእንግዲህ መመልከት የሚቻለው ግን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2034 ዓመት ይኾናል። ዶ/ር ጌታቸው መኮንን ጨረቃ እንዲህ ግዙፍ እና ደማቅ የምትሆንበትን ምክንያት በሞላላማ ምኅዋሯ እተሽከረከረች ለመሬት ስትቀርብ ኾኑን ያብራራሉ።

ዶ/ር ጌታቸው መኮንን በደቡብ አፍሪቃ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስና የፕሮግራሚንግ መምህር ናቸው። የዶክትሬት ጥናታቸውን ያከናወኑት ርእደ-ከዋክብት (asteroseismology) ላይ ነው። ጨረቃ የምትሽከረከርበት ምኅዋር ቅርጽ እንደ አሎሎ የተሟለለ ሲሆን አንደኛው ጫፍ ከሌላኛው ጫፍ ከምድር ጋር ያለው ርቀት እጅግ የተለያየ ነው። ጨረቃ ወደ መሬት በተጠጋች ቁጥርም በስበት ኃይሏ መሬት ላይ የተለያዩ ሞገዶች እንዲፈጠሩ ታደርጋለች። «ያ ማለት ግን» ይላሉ ዶ/ር ጌታቸው በተፈጥሮ ከሚከሰቱ አደጋዎች ጋር ግንኙነት የለውም።

የዩናይትድ ስቴትሱ ብሔራዊ የበረራ ሳይንስ እና የኅዋ አስተዳደርም (NASA)እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 ዓ.ም. ለኅትመት ያበቃው ጥናቱ ልዕለ-ጨረቃ በምድር ላይ ግዙፍ ተጽዕኖ እንደሌላት አትቷል። በተለይ ጃፓን ላይ የተከሰተው ኃያል ማዕበል እና መውጅ፣ እንዲሁም ርእደ-መሬት ከልዕለ-ጨረቃ ጋር ግንኙነት የለውም ብሏል። ስበቱ «የመሬት ቅርጽ ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል»ብለዋል።

በወቅቱ ግን የጨረቃ ተጽዕኖ የታላቋ ብሪታንያ ንብረት የሆኑ አምስት ዓሣ አጥማጅ መርከቦች ወደ ባሕር ዳርቻዎች በኃይል እንዲገፉ ሰበብ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ መምህር የሆኑት ዶ/ር አማረ አበበ የጨረቃ ወደ ምድር መቅረብ መሬት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል ይላሉ።

ጨረቃ የራሷ የሆነ ብርሃን የማታመነጭ ፀሐያዊ አካል ናት። ለመሬት እንደ ሳተላይት ሆና ታገለግላለች። ከፀሐይ የምታገኘውን ብርሃን የምታንጸባርቀው ይህች የምድር ተጎራባች የጠፈር አካል ከምድር በአማካይ በ384,400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የምድርን ሩብ የምትኽለው የዚህች ጨረቃ የስበት መጠኗ 1.62 m/s2  ሜትር በሰከንድ ስኩዌር ሲሆን፤ ከሌሎች እንደ ምድር ካሉ አካላት ጋር ሲነፃጸር በጣም ዝቅተኛ የስበት ኃይል የሚባል ነው።

የምድር የስበት ኃይል በአንፃሩ 9.81 m/s2  ጨረቃ የተከሰተችው ስርዓተ-ፀሐይ እውን ከሆነ ከ95 ሚሊዮን ዓመታት በኋላ እንደሆነ ጠበብት ይናገራሉ። በአጠቃላይ የጨረቃ እድሜ እንደ ሳይንቲስቱ ገለጣ 4,5 ቢሊዮን ዓመት ይገመታል።

ሙሉ ጨረቃ በሚሆንበት ጊዜ በመሬት እና በጨረቃ መካከል የሚደረገው የስበት ኃይል የመሬት የላይኛው ክፍል (crust) ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ሆኖም ተጽዕኖውን በግልጽ አንመለከተውም። ረቂቅ ነው። 

በኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ በሒሳብ ትምህርት የአራተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ጃኔት ሞሴቴ የሰኞ ዕለት አይነት ግዙፍ ጨረቃ ትኖራለች ብላ ገምታ አታውቅም። እናም ግዙፏን ደማቅ ጨረቃ ስትመለክት የተሰማት እጅግ ልዩ ስሜት ነበር። «እጅግ ሲበዛ የሚደንቅ ነው። ልዕለ-ጨረቃ ሲባል እንዲህ አልጠበኩም ነበር። አንዳንድ ጊዜ በበጋ ወራት ፀሐይ ወደ አድማሷ በምታሽቆለቁልበት ወቅት ሙሉ ለሙሉ የማትጠፋበት ወቅት አለ። እናም ልዕለ-ጨረቃ ሲሉ እሷን ይመስለኝ ነበር» ብላለች። «እናም በኋላ ላይ ግን ይህቺን ግዙፍ ጨረቃ የመመልከት ጉጉቱ አደረብኝ። በአጉልቶ መመልከቺያ መነፅር ጨረቃ ዐይናችን ስር ያለች እስኪመስለን ድረስ ቀርባ ነው የተመለከትናት። በጣም የሚደንቅ ነው» ስትል አድናቆቷን ገልጣለች።

ፊዚክስ እና ኬሚስትሪ በማጥናት ዘንድሮ ተመራቂ የኾነው ሌላኛው ተማሪ ዲሬጼ ሪንቃስኦኔም ከእነ ዶክተር ጌታቸው ጋር ኾኖ ጨረቃን በአጉልቶ መመልከቻ መነፅር የመመልከት ዕድል አግኝቶ ነበር። «ችግሩ ጨረቃ ብቅ ስትል ወዲያው መመልከት አለመቻላችን ነው» ያለው ዲሬጼ  ጨረቃ በወጣችበት ወቅት ደቡብ አፍሪቃ ማፊኬንግ ውስጥም ደመናማ እንደነበር ገልጧል። «አመሻሹ 12 እና 12 ሰአት ተኩል ላይ ግን ጨረቃ እጅግ ደምቃ እና ገዝፋ መመልከት ችለናል። እጅግ ሲበዛ አስደናቂ ነበር። ሁላችንም በመደመም ነው የተመለከትናት»

ከእዚህ ቀደም ጥቁር ጨረቃ፣ ቀይ ጨረቃ ተመልክቻለሁ ያለው ዲሬጼ «ግን እንደዚህ አይነት እጅግ ግዙፍ እና ደማቅ ጨረቃ ተመልክቼ አላውቅም» ሲል አድናቆቱን ገልጧል። በተለይ ፀሐይ ወደ አድማሷ ስታሽቆለቁል በወቅቱ ደመናማ ቢሆንም ደንገዝገዝ ማለት ሲጀምር ግን እይታው ለብዙዎች አስደማሚ ነበር ብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic