ላይፕሲሽ ለተገን ጠያቂዎች ያወጣችው እቅድ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ላይፕሲሽ ለተገን ጠያቂዎች ያወጣችው እቅድ

በላያፕዚሽ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎች እስከዛሬ በነበረው አሰራር ከህብረተሰቡ ተገልለው በተወሰነ አካባቢ እንዲቆዩ ነው የሚደረገው ። ወደፊት ግን ከህብረተሰቡ ጋር ተሰባጥረው በከተማይቱ በሞላ በተለያዩ ቤቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ታስቧል ።

በላያፕዚሽ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎች እስከዛሬ በነበረው አሰራር ከህብረተሰቡ ተገልለው በተወሰነ አካባቢ እንዲቆዩ ነው የሚደረገው ። ወደፊት ግን ከህብረተሰቡ ጋር ተሰባጥረው በከተማይቱ በሞላ በተለያዩ ቤቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ታስቧል ። ይህ ሃሳብም የውጭ ዜጎች ከህብርተሰቡ ጋር ተዋህደው የሚኖሩበትን ሁኔታ በሚያጠኑ ባለሞያዎች ዘንድ ተወድሷል ። ይሁንና ህብረተሰቡ ሲቃወመው ነው የሰነበተው ። ተቃውሞውም በከፊል ዘረኝነት የሚንፀባረቅበት ነበር ። በዚህ ሐሳብ ላይ ብዙ ውይይቶችና ማሻሻያዎች ከተደረጉበት በኋላ የከተማይቱ ምክር ቤት ዛሬ ሐሳቡን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል ። አድርያን ክሪሽ ያቀረበውን ዘገባ ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።

ላይፕዚሽ ከጀርመን መዲና በርሊን በሰተደቡብ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኝ ከተማ ናት ። የከተማይቱ ከንቲባ ቶማስ ፋብያን ተገን ጠያቂዎች በላይፕዚሽ ህብረተሰቡ መካከል እንዲኖሩ ያቀረቡትን አዲስ ሃሳብ ለማስረዳት ከሁለት ወራት በላይ በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረዋል ። የከተማው አስተዳደር  በከተማይቱ ደቡብ ምስራቅ  በሚገኘው በሪቤክሽትራሰ ሰፈር ለ 115 ተገን ጠያቂዎች ቤት ለመከራየት አስቧል ። የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ስጋት አላቸው ።

«አብዛኛዎቹ የራይበቤክ ሽትራሰ ነዋሪዎች በዚህ ህንፃ ዙሪያ በእግር ይንሸራሸራሉ ።   አዛውንቶች ወጣት ወንዶች በበቡድን ተሰብስበው ቆመው  ሲያዩ መፍራታቸው አይቀርም »

« የትኛዋ እናት ናት ህፃን ልጇን ይዛ በማታ በፈቃደኝነት ወደ እኔ የድንገተኛ ህክምና ክሊኒክ የምትመጣው ? »

« በህንፃችን ውስጥ የሚገኙት የስነ ልቦና ችግሮችም ሆነ የጥርስ ሃኪሞቹ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ገልፀውልናል ። ቤቱን ለቀው ለመውጣት እያሰቡም ነው ። »

ነዋሪዎች እነዚህን መሰል ስጋታቸውን ሲገልፁ ከንቲባ ቶማስ ፋብያን ደግሞ ለ670 ተገን ጠያቂዎች አዳዲስ መኖሪያዎችን ማግኘት አለባቸው ። ርሳቸው ባፈለቁት በዚህ ሃሳብ ብዙ አበረታች አስተያየቶችን አግኝተዋል ። ሃሳቡን የተቃወሙዋቸውም ጥቂት አይደሉም ። ሆኖም ፋቢያን ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች ሃሳባቸውን መቀየራቸው እንደማይቀር ነው ተስፋ የሚያደርጉት ።

« ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ቦታዎች ስለ ውጭ ዜጎችና ስለ ስደተኞች ይነሱ የነበሩት በጣም ጥሩ ያልሆኑ አስተያየቶች ነክተውኛል ። አንዳንዶቹ አስተያየቶች በጣም የተጋነኑና ደስ የማያሰኙ ነበሩ ። በዚያው ልክ ደግሞ ብዙ የተለሳለሱና እኛንም በእጅጉ የሚያበረታቱም ነበሩ ። በኔ ግንዛቤ ይህ በግልፅ የብዙሃኑ አመለካከት ነው ።»

Der somalische Asylbewerber Sahardid Jama-Ahmed. Copyright: DW/Adrian Kriesch Juli, 2012, Leipzig

ዛሃርዲድ ጃማ አህመድ

በላይፕዚሽ ከተማ ለተገን ጠያቂዎቹ ወደፊት ስለታሰበው መኖሪያ በሚካሄደው ክርክር ውስጥ የመነጋገሪያ ርዕስ የሆኑት ሰዎች አልተካተቱም ። ከነዚህም አንዱ ሶማሊያዊው ዛሃርዲድ ጃማ አህመድ ነው ። ከዛሬ 10 ዓመት አንስቶ 200 ተገን ጠያቂዎች በሚገኙበት በቶርጋወር ሽትራሰ ነው የሚኖረው ። ወንደ ላጤዎች በበዛት የሚገኙበትን ይህን ባለ ድርብ አጥርና ያልታደሰ ስፍራ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ለሰው መኖሪያ አይሆንም ሲል  ሊዘጋው አቅዷል ። በዚህ መጠለያ የሚኖረው ዛርዲድ ጀርመንኛ አቀላጥፎ ይናገራል ።

« በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚፈፀምብኝን እድልዎ ለምጄዋለሁ ።ሆኖም ሰዎች ከተዋወቁኝ በኋላ ብዙዎቹ ሙሉ በሙሉ ይቀየራሉ ፤ አዎ ሁሌም እንደሚባለው ሰው ካላወቀህ በመጠኑም ቢሆን መጠንቀቁ አይቀርም ።»

የ40 ዓመቱ ዛርዲድ ለብቻው የሚኖርበት ቤት ማግኘት ይፈልጋል ። አሁን ባለበት አነስተኛ ክፍል ብዙ ዝንቦችና በረሮዎች አሉ ። ለዛርዲድ ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህዶ የመኖሩ እቅድ ትልቅ ችግር ነው ። ተገን ጠያቂዎች አንድ ቁርጥ ውሳኔ ስላላገኙ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲዋሃዱ የሚሰጣቸው አግልግሎት ዝቅተኛ ነው ። ለምሳሌ ዛርዲድ የአጥንት ህክምና ባለሞያ ነው ። ሆኖም እንዲሰራ አይፈቀድለትም ፤ በየሶስት ወሩ በሚራዘም ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ነው ያለው ።  አሁን በላይፕዚሽ የተጀመረው ጥረት ችግሮቹን በሙሉ ባያቃልልም ከ 100 ነዋሪዎች 6 ቱ ብቻ የውጭ ዜጋ በሆነባት በዚህች ከተማ ተገን ጠያቂዎች ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ ለማድረግ አንድ ጠቃሚ እርምጃ መሆኑ ይታመናል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic