ለእግር ኳስ ጨዋታ ዳኝነት የሥነ-ቴክኒክ አጋዥነት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 02.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ለእግር ኳስ ጨዋታ ዳኝነት የሥነ-ቴክኒክ አጋዥነት፣

ከመጪው ሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 4 ፣ 2002 ዓ ም፣ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄደው ለዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፣ ከዓለም ዙሪያ ማጣሪያውን ያለፉት 32 ቡድኖች በ 8 ምድብ ተደልድለው የሚወዳደሩበት ዕጣ፣

default

የፊታችን ዓርብ በልዩ ሥነ ሥርዓት ይወጣል። በዓለም ዋንጫ፣ በብሔራዊ ቡድኖችም ሆነ በክለቦች ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች በየጊዜው ከሚያጋጥሙ ዐበይት ችግሮች አንዱ፣ በአጫዋችነት በትክክል የዳኝነት ተግባር የማካሄዱ ጥያቄ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍም ሆነ ለማስወገድ የተለያዩ ሐሳቦች ቢቀርቡም እስካሁን ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። ለሰው ዐይን አስቸጋሪ የሚሆኑ አንዳንድ ቅጽበታዊ ክስተቶችን ወይም ሳንኮችን ሥነ-ቴክኒክ በሚገባ እንደሚፈታቸው ግን የሚያጠራጥር አይደለም። በዚህ ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን እንዴትነቱን ከማውሳታችን በፊት ፣ እስቲ ለአብነት ያህል የዳኞችን አንዳንድ አከራካሪ ውሳኔዎች እናስታውስ።

እ ጎ አ በ 1966 ዓ ም፣ ለንደን ዌምብሊ እስታዲየም በተደረገ የፍጻሜ ግጥሚያ ፣ የምዕራብ ጀርመን ቡድን ተሸንፎ፣ ኢንግላንድ የዓለም ዋንጫ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል። ይሁንና ያኔ ለድል ያበቃችው ግብ ከላይ የግቡን አግዳሚያ እንጨት መትታ ወደታች ኖራ ከተነሰነሰበት መሥመር ላይ እንደነጠረች ነበረ የመሥመር ዳኛው ግብ የመሆኗን ምልክት ሰጥተው ዋናው ዳኛ በማያሻር ውሳኔአቸው ያጸደቁት። ጀርመናውያን እስካዛሬ ድረስ ያች ግብ በአርግጥ ትክክለኛ ግብ አልነበረችም ነው የሚሉት። እ ጎ አ በ1986 ዓ ም፣ በዘመኑ እጅግ ዝነኛው የእግር ኳስ ተጫዋች ዲየጎ አርማንዶ ማራዶና በራስ የገጨ አስመስሎ በእጁ መትቶ ያስገባት ግብ መጽደቋ፣ በዓለም ዙሪያ የእግር ኳስ ተመልካቾችን ሁሉ እንዳስገረመ ታሪክ ሆኖ አልፏል። ራሱ ማራዶና፣ የኔ ሳይሆን የአግዚአብሔር እጅ ይሆናል ኳሷን ለግብ ያበቃት ማለቱም የሚታወስ ነው።

ከአውሮፓ ፣ ዘንድሮ፣ በመጨረሻዋ ሰዓት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመጓዝ ዕድል ከገጠማቸው የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል አንዱ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ነው። የመጨረሻውን የሞት ሽረት ግጥሚያ ያካሄደው ከአየር ላንድ ቡድን ጋር ሲሆን ለድል ያበቃችው ግብ የተገኘችው እውቁ የፊት አጥቂ ተጫዋች ቲየሪ ኦሪ ግብ አካባቢ እንደመስኖ ውሃ በአጁ እየመራ ባሻጋራት ኳስ መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ዳኛ ካላየ ወይም እንደመሰለው ከበየነ ምንም ማድረግ አይቻልም ፣ እስካሁን በሚሠራበት ደንብ መሠረት ፣ በኳስ ሜዳ ዳኛ የሚሰጠው ቅጽበታዊ ብይን ይጸናልና!ሐቁ ግን የተለየ መሆኑን ታዛቢ ብቻ ሳይሆን የራስ ወገንም ሊመሠክረው የሚችል ጉዳይ ነው። የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች Bixente Lizarazu ያለውን እናስታውስ።

«ያ፣ አሳፋሪ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ነበር። ቡድኑ፣ ቲየሪ ኦሪ ፤ በአጁ በገፋት ኳስ ነው፣ በተዓምር ከዚያ የደረሰው። በዚያ ጨዋታ ኩራት የሚያሳድር አንዳችም መሠረታዊ ምክንያት የለንም። »

Fußball Elfenbeinküste Diddier Drogba

ነሐሴ 30 ቀን 2001 ዓ ም፣ አቢጃ ውስጥ፣ ከአፍሪቃ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በተካሄደ የእግር ኳስ ጨዋታ፣ የኮትዲቯሩ ዲድዬ ድሮግባ፣ ኳስ ለመቆጣጠር፣ ከቡርኪና ፋሶው ኮኔ ካሪ ጋር ሲታገል፣

የእግር ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስና የመሳሰሉ ጨዋታዎች ዳኞች ሥራ፣ ፍጹም የሚያስቀና አይደለም። ለምን ቢሉ፣ የተጫዋቾችንና የኳስን ፍጥነት ፣ በአጠቃላይ የውድድር እንቅሥቃሴን ምንጊዜም በዐይን ብሌን ብቻ ተመልክቶ ትክክለኛ ብይን መስጠት ያዳግታልና። ስለሆነም ፣ ፈጣን የሥነ-ቴክኒክ ድጋፍ እንደሚበጅ ግንዛቤ እያገኘ መምጣቱ የሚታበል አልሆነም። ለምሳሌ ያህል በቅጽበት አንድን ድርጊት መልሶ የሚያሳይ ቪዲዮ ፣ ዳኞች፣ በእርጋታ እንዲያመዛዝኑና ውሳኔአቸውን እንዲከልሱ ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ እስቴትስ ፣ በገና ጨዋታ፣ ቴኒስም ሆነ የአሜሪካ እግር ኳስ ውድድር፣ ከበድ ያሉ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ጊዜያት አልፎ- አልፎ አከራካሪ ውጤትን ለማስተካከልም ሆነ ለማጽናት ፣ በቪዲዮ የተቀረጸውን መልሶ መመልከት የሚቻልበት ሁኔታ ይሠራበታል። በተለይ በዐበይት የሜዳ ቴኒስ ውድድሮች፣ ኳሱ የነጠረችው ከመሥመር ውጭ መሆን አለመሆኗን፣ ዳኞች በተጫዋቾች ተጠየቁም አልተጠየቁ ፣ የሚጠራጠሩ ተመልካቾች ግልፅ እንዲሆንላቸው በማሰብ ይመስላል፣ በምስል እንዲታይ ይደረጋል። ኳሷ የምታርፍበትን ትክክለኛውን ነጥብ ለማሳየት የምትለጋዋን የፈጣንዋን ኳስ እንቅሥቃሴ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርጹ 6 ያህል ካሜራዎች ያግዛሉ። እናም፣ ዳኛው፣ ኳሷ፣ ከመሥመር ውጭ መሆን አለመሆኗን በተረጋገጠ ሁኔታ መወሰን ይቻላል ማለት ነው። ይህም ይግባኝ የማይልበት የመጨረሻ ውሳኔ ነው የሚሆነው።

እግር ኳስን በተመለከተ ፣ እውቁ የአስፖርት ጫማ ሠሪና ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ «አዲዳስ»ና ሌሎችም ኩባንያዎች ያለችበትን ፣ የምታርፍበትን የሜዳ ነጥብ በትክክል የምታሳይ በውስጧ ኢምንት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ የምትሸከም ኳስ መሥራት በይፋ ካሳወቁ 2 ዓመት አልፏል። በእነርሱ አቅድ መሠረት፣ በግብ ማስቆጠሪያ መስመሮች ዙሪያ ፣ በትኅተ-ምድር የኤሌክትሪክ ሽቦ ተዘርግቶ፣ ኳሷ፣ ከመሥመር በማለፍ ግብ ከሆነች፣ ዋና አጫዎች ዳኛ በሚያሥሩት ልዩ የእጅ ሰዓት አማካኝነት ማረጋገጫ ምልክት ይሰጣቸዋል። የእንግሊዝ የአንደኛ ምድብ የአግር ኳስ ክለቦች ማኅበር ደግሞ፣ ከቪዲዮና «አዲዳስ» ካቀረባት «ብልጥ ኳስ» ከተሰችው፣ በውስጥዋ ረቂቅ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ከሚገኝባት ልዩ የእግር ኳስ ሌላ፣ በአማራጭነት ልክ እንደ ሜዳ ቴኒስ ኳስ፣ የእግር ኳስም የሚያርፍበትንም ሆነ የሚነጥርበትን ቦታ የሚያመላክተውን ዘዴ መፈተሹ ታውቋል።

በዘመናዊ ሥነ ቴክኒክ በመታገዝ፣ ለአካራካሪ የእስፖርት ውድድር ውጤት፣ ፍጹም ትክክለኛ የሆነውን ብይን መስጠት ይቻላል። ግን ፣ ሥነ-ቴክኒክ የጋለ የእስፖርት ውድድርን ስሜትና ቅጽበታዊው ሰብአዊ ብይን፣ በተመካቾች ዘንድ የሚያሳድረውን

ስሜት ያርቅ ይሆናል። ሥነ-ቴክኒክ የሚረዳው፣ በስህተትም ሆነ በሌላ ምክንያት የተላለፈ ውሳኔን ለማስተካከል ብቻ ነው።

ተክሌ የኋላ፣ ሸዋዬ ለገሠ