ለአሜሪካን የስለላ ተቋም የሚሰልልዉ ያሁ | ዓለም | DW | 14.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ለአሜሪካን የስለላ ተቋም የሚሰልልዉ ያሁ

ግዙፉ የኢንተርኔት ግንኙነት መረብ ያሁ ባለፈዉ ዓመት በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ የኢሜይል ተጠቃሚ ደንበኞቹን በምሥጢር ሲሰልል እንደነበር መረጃዎች እየወጡ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00

የኢንተርኔት ስለላ

ድርጅቱ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015 ዓ,ም ከዩናይትድ ስቴት የስለላ ተቋም በተሰጠዉ መመሪያ መሠረት በየጊዜዉ የደንበኞቹን የኢሜይል ልዉዉጥ በስዉር ፎቶ ያነሳል የሚሉ ዘገባዎች ወጥተዋል። ይህን የጠቆመዉ የቀድሞዉ የድርጅቱ ባልደረባ እንደሚለዉ ያሁ ትዕዛዙን ከአሜሪካዉ ብሔራዊ የስለላ ተቋም NSA ወይም የፌደራል የምርመራ ቢሮ ማለትም FBI ነዉ የተቀበለዉ።

ይህን ትዕዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ያሁ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ደንበኞቹ የሚለዋወጡትን የኢሜይል ልዉዉጥ ፎቶ የሚያነሳ ወይም በሙያዊ ቃሉ ስካን የሚያደርግ ለየት ያለ ሶፍትዌር ያሆ በፕሮግራሙ ማካተቱን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል። ይህም ይላል ዘገባዉ በዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት ሳይሆን በድርጅቱ ብቻ የሚደረግ የዜጎችን መረጃ በትክክለኛዉ ሰዓት የማጮለግ እና የመሰለል ርምጃ መሆኑ ተረጋግጧል። እንደ ዘገባዉ እስካሁን ባለስልጣናቱ ፖስታዎችን እና የመልዕክት መለዋወጫ ዉስጥ የተጠራቀሙ መረጃዎችን ነበር የሚከታተሉት። ለዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የሚሠራ እንዲህ ያለዉ የስለላ ፕሮግራም ሲፈጠር ግን አዲስ፤ የተለየ እና ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ።  ያሁ ይህ በቀረበለት ጥያቄ እና በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መሠረት የተደረገ ነዉ ይላል።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ግልፅነትን አሳየሁበት ባለዉ ዓመታዊ ዘገባዉ ግን ያሁ ለአሜሪካን የስለላ ተቋም መሥራቱን ይፋ አላደረገም ነበር። በወቅቱ የተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ተቋማት ኢሜይላቸዉ ሳይሰለል እንዳልቀረ ስጋታቸዉን ገልጸዋል። በተጠቀሰዉ ጊዜም ከ39 ሺህ የሚበልጡ ችግሩ እንዳጋጠማቸዉ ተመዝግቧል።  

«እንደ እዉነቱ ከሆነ መረጃዎችን በተመለከተ የዩናይትድ ስቴትስ ተቋማት አሳልፈዉ እንደሚሰጡ ስኖዉደን ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ በይፋ ታዉቋል። የያሁም ተመሳሳይ ነዉ። ጉግል እና ሌሎች የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች ይህን ያስተባብላሉ። እዉነት መሆን ያለመሆኑ ነገር ግን አከራካሪ ነዉ። » ይላል የኢንተርኔት የመረጃ ልዉዉጥ ተሟጋች እና ጋዜጠኛዉ ማርኩስ ቤክዳል።

እንዲህ ያሉ መረጃዎችን በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ይፋ ያደረገዉ ኤድዋርድ ስኖዉደን የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ተቋማት ከኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግሯል። ድርጅቶቹ ግን ይህን ያስተባብላሉ። እነሱ የሚሉትም የሚፈለጉ መረጃዎችን የሚሰጡት ሕግን መሠረት በማድረግ የሚጠየቁትን ብቻ ነዉ። ማይክሮ ሶፍት፣ ጉግል እና ትዊተር በበኩላቸዉ እንዲህ ዓይነቱን የስለላ ተቋማት ጥያቄ እንደማያስተናግዱ በመግለፅ ራሳቸዉን ከዚህ ያርቃሉ።

«እንዲህ ያለ ጥያቄ ቀርቦልን አያዉቅም፤ ቢቀርብልን እንኳን ምላሽ አንሰጥም ነበር።» ይላሉ የጉግል ቃል አቀባይ። አፕል በበኩሉ የራሱን ተጠቃሚዎች የሚሰልልበት ሶፍትዌር እንዲፈጥር እንዳልተጠየቀ ለዋሽንግተን ፖስት ገልጿል።  ማይክሮሶፍት ደግሞ «ይህን መሰል ጥያቄ ቢቀርብልኝ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እወስደዉ ነበር።» ነዉ የሚለዉ። አፕል ባለፈዉ የካቲት ወር በሚያመርታቸዉ የእጅ ስልኮች ማለትም ስማርት ፎኖች ላይ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችል ፕሮግራም እንዲያክልበት ከአሜሪካን መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ ለፍርድ ቤት አቤት ብሏል። ማርኩስ ቤክዳል ግን ይህም ሆኖ አሁን ያሆ ላይ የሚሰማዉ ጥርጣሬ ሁሉንም የዩናይትድ ስቴትስ ኩባንያዎች ይነካል ባይ ነዉ። ጋዜጠኛዉ ቤክዳል፤ ጀርመን ዉስጥ የመረጃ ስለላ ስልት ስለመኖሩ ሲናገር፤

«በመሠረቱ ክትትሎች ይኖራሉ፤  ፌደራል የስለላ አገልግሎት የሚጠቀምበት SINA –Box ማለትም የመረጃዎችን ደህንነት የሚጠብቅ ስልት አለ።» ይላል።

SINA –Box  የተሰኘዉ ሃርድ ዌር እና ሶፍት ዌር ነዉ፤ ይህም  ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸዉን መረጃዎች ግንኙነት እንዲጠብቅ ሆኖ የተዘጋጀ ነዉ። ለምሳሌም በኩባንያዎች እና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል ያለዉን የመረጃ ልዉዉጥ ደህንነት ይጠብቃል።  ጋዜጠኛዉ እንደሚለዉ ግን በዉስጡ ምን እንዳለ ተጠቃሚዎቹ በፍፁም አያዉቁም። እንደ እሱ ገለጻም አዲሱ የፌደራል ስለላ አገልግሎቱ ሕግ፤ ወደፊት በኢንተርኔት የሚደረጉ ግንኙነቶች ክትትል እንዲደረግባቸዉ ይፈቅዳል፤ የመረጃ ልዉዉጦችም እስከ ስድስት ወራት ሳይጠፉ እንዲከማቹ ያደርጋል። በመረጃ ደህንነት በኩል አሁን የጀርመን የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢያዎቹ ሜይል ቦክስ ዶት ኦርግ እና ፖስቴኦ ዶት ዲኢ፤ ከአሜሪካኖቹ ተፎካካሪዎቻቸዉ የተሻሉ እንደሆኑም ይገልጻል። እነዚህኞቹ መልዕክቶች ከላኪዉ ወደ ተፈላጊዉ ተቀባይ ብቻ እንደተቆለፉ እንዲደርሱ የሚያደርጉ ጠንካራ ስልት ማለትም ኢንክሪፕሽን አላቸዉ። ለጀርመን የመረጃ ጥበቃ ሕግም የተገዙ ናቸዉ። እንዲያም ሆኖ ግን በፈረንሳይ ወይም ብሪታንያ የስለላ ተቋማት ከመሰለል አያድኑም። ብቸኛዉ በባለስልጣኖች ሳይሰለሉ ኢሜይልን መለዋወጥ የሚያስችለዉ መንገድ ኢንስክሪፕሽን ወይም ከላኪ ወደተቀባይ የተቆለፉ መልዕክቶችን ማድረስ የሚያስችል ስልት ያለዉ ብቻ መሆኑንም በአፅንኦት ይገልጻል።

 ሳብሪና ፓብስት/ ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic