ለታዳጊ አገሮች የማይበጀው የሁለት ወገን የነጻ ንግድ ስምምነት | ኤኮኖሚ | DW | 28.03.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ለታዳጊ አገሮች የማይበጀው የሁለት ወገን የነጻ ንግድ ስምምነት

በዓለም ንግድ ፍትሃዊነት ረገድ በድርጅቱ ዓባል ሃገራት መካከል የተካሄደው ድርድር የረባ ዕርምጃ ካለማሣየቱም በላይ በወቅቱ እንዲያውም ተሰናክሎ ነው የሚገኘው። የበለጸጉት መንግሥታት የእርሻ ድጎማቸውን በማቆም ወይም በሚገባው መጠን በመቀነስ ታዳጊ ሃገራት ለፉክክር ብቁ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ አይደሉም። ከአጠቃላዩ ስምምነት የተናጠሉን ውል መርጠዋል።

የልማት እጦት ገጽታ

የልማት እጦት ገጽታ

በመልማት ላይ የሚገኙት ሃገራት የነጻ ንግድን መርሆ ተከትለው ገበያቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲከፍቱ ከበለጸጉት መንግሥታት አኳያ የሚደረገው ግፊት እየጠነከረ ነው የሄደው። ሃብታም መንግሥታት ከዓለም ንግድ ድርድር መክሸፍ ወዲህ ገበዮችን በማስከፈት ፍላጎታቸው የሁለት ወገን፤ ማለት ባይላተራል የነጻ ንግድ ስምምነቶች ከተናጠል መንግሥታት ወይም አካባቢዎች ጋር ማካሄዱን አጠናክረዋል። ይህ ደግሞ ድሆቹን ሃገራት ይባስ ድሃ እንዳያደርግ ስጋት መፍጠሩ አልቀረም።

በዓለም ንግድ ድርጅት የድርድር ሂደት ሁነኛ መፍትሄ ሊገኝ አለመቻሉ በተለይ ዛሬ የዓለም የኤኮኖሚ ትስስር፤ ግሎባላይዜሺን እየተስፋፋ በሄደበት ዘመን የታዳጊዎቹን ሃገራት የገበያ ተሳትፎ የባሰ የሚያቆረቁዝ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። በወቅቱ በበለጸገው ዓለምና በታዳጊ ሃገራት መካከል መስፋፋት የያዘው አዲስ የነጻ ንግድ ስምምነት ደግሞ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ ካለው ግንዛቤ ውጭ ድሆቹን መንግሥታት ይበልጥ ድሃ የሚያደርግ ነው የሚሆነው።

ዓለምአቀፉ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም በቅርቡ በጉዳዩ አውጥቶት በነበረው ዘገባ እንዳመለከተው ታዳጊዎቹ ሃገራት ከሃብታሞቹ መንግሥታት ጋር እንዲፈርሙ በሚገደዱት የሁለት ወገን የንግድ ስምምነት የልማት ዕድላቸው ወደ ዜሮ እያቆለቆለ ነው። የወደፊት ተሥፋቸው ይመነምናል። በሁለት ወገኑ የነጻ ንግድ ስምምነት መሠረት ታዳጊዎቹ መንግሥታት ለምሳሌ የአውሮፓን ሕብረት ከመሳሰሉ አካባቢዎች ለሚመነጩ በድጎማ የሚመረቱ የእርሻ ምርቶች ገበዮቻቸውን መክፈት ይኖርባቸዋል። በአንጻሩ የተራገፈባችውን ምርት ያህል ወደ ውጭ ገበዮች አምርቶ የመላክ አቅም የላቸውም፤ የመፎካከር ብቃቱም እንዲሁ!

ገና ከዛሬው በበለጸጉት መንግሥታትና በታዳጊ ሃገራት መካከል የተደረጉት የሁለት ወገን ወይም የአካካቢ የነጻ ንግድ ስምምነቶች ከ 250 የሚበልጡ ሲሆን የኦክስፋም ዘገባ እንደጠቆመው በድርድር ደረጃ የሚገኙትም ብዙዎች ናቸው። በአማካይ በየሣምንቱ ሁለት የመዋዕለ-ነዋይ ውሎች እንደሚፈረሙ ነው የሚነገረው። ባይላተራሉ ስምምነት ዛሬ በዓለም ንግድ ላይ 30 በመቶ ድርሻ አለው። የውሉ መፈረም ፍጥነት እስትንፋስ የሚያሣጣ ነው ለማለት ይቻላል። ከግፊቱ ደግሞ የትኛውም ታዳጊ አገር፤ የፈለገውን ያህል የደኸየ ይሆን ያመለጠ የለም።

ታዲያ ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር ዘመነ-ግሎባላይዜሺን እየጠነከረ በሄደበት በአሁኑ ወቅት ስምምነቶቹ በድሆች ሃገራት ገበሬዎችና ሠራተኞች ትከሻ የሃብታም መንግሥታት የውጭ ንግድ አቅራቢዎችና ኩባንያዎችን ነው የሚጠቅሙት። ይህ በታጋዲው ዓለም ልማትና የተፈጥሮ ይዞታ ላይ ያለው ጉዳትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የዕውቀት ባለቤትነት ደምቦችን በመጠቀም ለምሳሌ የታዳጊው ዓለም ድሃ ሕዝብ ነፍስ-አዳኝ መድሃኒቶችን በቀላሉ እንዳያገኝ ያደርጋሉ።

አነስተኛ ገበሬዎች በማይቋቋሙት ሁኔታ የዘርና የሌላ እርሻ ምርቶችን ዋጋ መጨመርም ያለ ነገር ነው። ኦክስፋም እንደዘገበው ሁኔታው የታዳጊ ሃገራት ኩባንያዎች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ዕውቀቶችን የማግንታቸውን ሁኔታም የከበደ ያደርገዋል። መንግሥታቱም ቢሆን በዚህ አኳያ ሁኔታዎችን የማረቅ አቅም የላቸውም። አንዳንድ ታዳጊ አገሮች በቋጥኝና በጠጣር መሬት መካከል እንደቆሙ ነው የሚቆጠረው የኦክስፋም ዘገባ አርቃቂ ኤሚሊይ ጆንስ እንደሚናገሩት።

በርሳቸው አባባል ብዙዎቹ “የኤኮኖሚ ሽርክና ውል” ተብዬውን ስምምነት የሚፈርሙት በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ የነበራቸውን ልዩ የገበያ አስተያየት እንዳያጡ በመፍራት ነው። እነዚህ ሃገራት ከበለጸገው ዓለም በሚያስገቡት ምርት ላይ የጣሉትን ቀረጥ ዝቅ በማድረግ በአጸፋው የውጭ ንግድ አስተያየት ሲያገኙ ቆይተዋል። ሆኖም የተባለው ልዩ አስተያየት ብዙም ጠቅሟል ለማለት አይቻልም። ለምሳሌ የሰሜን አሜሪካ የነጻ ንግድ ስምምነት በአሕጽሮት NAFTA ባለፉት አሥር ዓመታት በሜክሢኮ ብቻ 1,3 ሚሊዮን ሕዝብ ሥራ-አጥ እንዲሆን ነው ያደረገው።

ወደ አሜሪካ ገበዮች የጨመረው የሜክሢኮ የውጭ ንግድ ዕድገትን አላስከተለም፤ እንዲያውም የሠራተኛው ደሞዝ መጠን ከአሥር ዓመታት በፊት ከነበረው ማቆልቆሉን የ 2004 መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይ የአግልግሎት ሰጪውን ዘርፍ ደምቦች የሚያለዝቡት ስምምነቶች የአገሬውን ኩባንያዎች የፉክክር አቅም የሚቀንሱና ከገበያ የሚያስወጡ፤ በአንጻሩም የታላላቅ ኩባንያዎችን ሞኖፖል የሚያጠናክሩ ሆነው ታይተዋል።

በሜክሢኮ የፊናንስ አገልግሎት ዘርፍም ቢሆን ሁኔታው የተለየ አይደለም። በነጻ ንግዱ ስምምነት ሂደት የአገሪቱ ባንኮች የሃብት ባለቤትነት በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 85 በመቶ በውጭ ዕጅ ሊገባ በቅቷል። በዚሁ ሳቢያ ለአገሬው ነጋዴዎች የሚሰጠው ብድር ከብሄራዊው አጠቃላይ ምርት አንጻር ከአሥር ወደ 0,3 በመቶ ማቆልቆሉም አልቀረም። ይህ ደግሞ በተለይ በገጠር የሚኖረውን ሕዝብ ክፉኛ ነው የጎዳው። በአጠቃላይ የሁለት ወገኑ የነጻ ንግድ ስምምነት ሂደት መስፋፋት ለታዳጊው ዓለም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነ እንዳይሄድ በጣሙን የሚያሰጋ ነው። የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር መልሶ መንሰራራትና ፍትሃዊ የጋራ ምላሽ መገኝቱ ይበልጥ አጣዳፊ ሆኖ ይቀጥላል።