ለሴቶች መብት ታጋይዋ ሉብና አህመድ አል ሁሴን | ኢትዮጵያ | DW | 28.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ለሴቶች መብት ታጋይዋ ሉብና አህመድ አል ሁሴን

የሀገሪቱን የአለባበስ ህግ ችላ በማለት ሱሪ ለብሳለች በሚል ክስ የዝውውር ዕገዳ ያረፈባት ሱዳናዊትዋ ሉብና አህመድ አል ሁሴን ለሴቶች መብት ለመታገልና በቅርቡ የሚወጣውን መጽሀፍዋን ለማስተዋወቅ ዕገዳውን በመጣስ ሰሞኑን ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ገባች።

default

ለሴቶች መብት ታጋይዋ ሉብና አህመድ አል ሁሴን

ለተመድ ትሰራ የነበረችው ጋዜጠኛዋ ሉብና በተሰነዘረባት ክስ ባለፈው መስከረም መጀመሪያ ላይ በጅራፍ አርባ ጊዜ በአደባባይ እንድትገረፍ ቢበይንም፡ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ግዙፍ ተቃውሞ በመነሳቱ፡ ብይኑ የኋላ ኋላ ጋዜጠኛዋ አንድ መቶ ሀምሳ ዩሮ ወደምትከፍልበት መቀጫ መቀየሩ አይዘነጋም። ሆኖም፡ ሉብና ገንዘቡን ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆንዋ ታስራ ነበር። የሱዳን ጋዜጠኖች ህብረት ሉብና ሳታውቅ፡ በርስዋ ስም መቀጫውን ከከፈለ በኋላ ተፈታለች። ይሁንና፡ ሉብና ገንዘቡን በስሟ የከፈለው ቡድን ጉዳዩ ብዙ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዳያገኝ የፈለገ ከሱዳን መንግስት ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው መሆኑን ሉብና በማስረዳት ድርጊቱን ተቃውማለች። ሉብና በአንድ የካርቱም ምግብ ቤት ከሌሎች አስራ ሁለት ሴቶች ጋር ባንድነት የመታሰር ዕጣ የገጠማት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነበር። ምንም እንኳን በዚያን ጊዜ የተመድ ሰራተኛ ስለነበረች ከእስራት ነጻ ልትሆን ብትችልም፡ በዚሁ አቋሟ በመጠቀም ፈንታ፡ በህጉ አንጻር ለመታገል ስትል ስራዋን ለቃለች። የርስዋ መታሰርና መፈረድ በመቃወም ብዙዎች በመዲናይቱ ግዙፍ ተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸው አይዘነጋም። ሉብና በሱዳን የሻርያን ህግ ባቀፈው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ ተሀድሶ እንዲደረግ መተገልዋን ወደፊትም እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
« እኔ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ከሱዳን ውጭ ዘመቻየን እቀጥላለሁ። ጠበቃየንም ምክር እንዲሰጡኝ እና ከሴቶች ቡድኖች ጋር እንዲያገናኙኝ እጠይቃለሁ። ምክንያቱም በትግላችን ላይ የመላ ዓለም ርዳታ ያስፈልገናል። »
በአሁኑ ጊዜ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የምትገኘው ሉብና ሴቶች በአለባበሳቸው የተነሳ ክትትል እንዳያርፍባቸው ለጀመረችው ትግልዋ በሀገርዋ ያሉ ሙስሊም ሴቶች ሙሉ ሂጃብን እንዳይለብሱ ለመከልከል ጥረት ከጀመረችው ከፈረንሳይ ሞገስ አግኝታለች።
ለሱሪ መልበስ አርባ የጅራፍ ግርፋት የተሰኘው ሉብና በፈረንሳይኛ ቋንቋ የደረሰችው መጽሀፍዋ በሻሪያ ህግ አንጻር ያደረገችውን ትግልዋን የሚገልጽ ነው። በሱዳን የሻርያ ህግ እስከተዋወቀበት እአአ እስከ 1983 ዓም ድረስ ስለነበረው አስተዳደግዋ እና ስለጋዜጠኝነት ሙያዋ ዝርዝር መግለጫ የሚሰጠው ይኸው መጽሀፉ በእንግሊዝኛ፡ በዐረብኛ እና በኪስዋሂሊኛ ቋንቋች ተተርጉሞም ይወጣል። ለሉብና አቀባበል በፓሪስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፈረንሳዊው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቤርናርድ ኩሽነር ሉብና በትግልዋ ጽናትን ማሳየትዋን አድንቀው፡ የሉብና ትግል ለዐረብ፡ ብሎም፡ ለአፍሪቃ ሴቶች ትልቅ ትርጓሜ የያዘ ትግል መሆኑን አስረድተዋል። ሚንስትሩ በመቀጠልም ብዙ የሱዳን ሴቶች ሉብና ለደረሰባት ዓይነት ዕጣ መጋለጣቸውን አመልክተዋል።
« አርባ ሶስት ሚልዮን ሴቶች ባለፈው ዓመት 2008 በካርቱም አካባቢ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለዚሁ የጭቆና ተግባር በተላኩ ፖሊሶች መታሰራቸውን በአጽንዖት ላስታውቅ እፈልጋለሁ። ሉብና አህመድ አል ሁሴን ህጉን በመቃወም በዚህ እስራት አንጻር ለመታገል ቁርጥ ርምጃ ወስዳለች። »
በብዛት ሙስሊሞች በሚኖሩበት በሰሜናዊ ሱዳን በሚገኘው የሀገሪቱ መንግስት እና በአንጻሩ ለብዙ ዓመታት ትግል ባካሄደው በደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ጦር መካከል እአአ በ 2005 ዓም በኬንያ ናይቫሻ በተፈረመው የሰላም ውል መሰረት፡ የሻርያ ህግ በመዲናይቱ ካርቱም ለሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ላልሆኑት ዜጎች አያገለግልም። ይሁንና፡ ለጠቅላላ የሱዳን ሴቶች መብት ለመታገል ቆርጣ የተነሳችው ሉብና እንደምትለው፡ እነዚህም ሴቶች ለሻርያ ህግ ተጋልጠው መቀጫ ይደርስባቸዋል።

አርያም ተክሌ
RTR/DPA/DW