1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለግዢ የቀረበው ዋጋ ከመነሻ ተመን ያነሰ ነው

ዓርብ፣ ጥር 12 2009

ከአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ብአዴን ጋር ትስስር ያለው ጥረት ኮርፖሬት በመንግሥት ሥር የነበሩ ሁለት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ወደ ራሱ ለማዛወር መቃረቡ ተነግሯል፡፡ ጥረት ለግዢ ያቀረበው ዋጋ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ከተቀመጠው መነሻ ያነሰ ቢሆንም ፋብሪካዎቹ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ ወደ ጥረት እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡

https://p.dw.com/p/2VwgB
Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherin
ምስል Jeroen van Loon

Ruling party company to take over 2 state factories (FINAL) - MP3-Stereo

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሆኑት የባህር ዳር እና ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለጥረት እንዲሸጡ ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የቀረበለትን ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ነው፡፡ 

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒሥቴር ጽሕፈት ቤት የወሰደው ጥረት ሁለቱን ፋብሪካዎች ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ  ቀድሞ ከተቀመጠው ተመን በታች ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጥረት የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለመግዛት 315 ሚሊዮን ብር ዋጋ ማቅረቡን ሀገር ዉስጥ የሚታተም አንድ ሳምንታዊ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ደግሞ 450 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡

በጥረት በኩል የቀረበው ዋጋ በወቅቱ የገበያ ሁኔታ ላይ ተንተርሶ ከወጣው ተመን በታች መሆኑን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒሥቴር የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ይቀበላሉ፡፡ መንግሥት ሁለቱን ፋብሪካዎች ወደ ግል ለማዛወር በተደጋጋሚ ለጨረታ ቢያቀርባቸውም ገዢ እንደታጣ የሚያስታውሱት አቶ ወንዳፍራሽ በዚህም ምክንያት በድርድር ለመሸጥ ሂደቱ እንደተጀመረ ያስረዳሉ፡፡ 

“እናንተ ያቀረባችሁት ዋጋ [ያነሰ] ብለው ፎርቹኖች የሚጠቅሱን ምንድነው ከዚህ በፊት ጠቋሚ ዋጋ የምንለው አለ፡፡ ከዚህ በፊት ጨረታ ላይ ያወጣነውን [ዋጋ] ተከትለው ነው ከዚህ በፊት ቀርቦ ከነበረው ያነሰ ነው የሚሉት፡፡ ከዚያ አንጻር ከታየ ያነሰ ነው፡፡ ነገር ግን ድርድር ላይ ተደራዳሪዎቹ ናቸው ዋጋ የሚያቀርቡት፡፡ ድርድር ላይ ዋጋ አንተምንም፡፡ በነገራችን ላይ ወደ ድርድርም ስንሄድ ማስታወቂያ አውጥተን ነው፡፡ ሁሉም ፍላጎት ያለው ለመግዛት እንዲደራደር ማለት ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ የተሻለውን መርጠን እንደራደራለን፡፡ የተሻለ ዋጋ ያቀረበውን፣ የተሻለ የሥራ ዕቅድ ካቀረበው ጋር እንደራደራለን፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ አሰራራችን” ይላሉ መሥሪያ ቤታቸውን የመረጠውን አካሄድ ሲያብራሩ፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba Origin Africa 2015 Textile Messe Ausstellung
ምስል DW/Y. Egiziabher

ጥረት ሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቱ ቀደም ሲል ላወጣው ተመን ቀረብ ያለ ዋጋ ስላቀረበ እና የሥራ ዕቅዱም የተሻለ ስለሆነ መመረጡን አቶ ወንዳፍራሽ ተናግረዋል፡፡ ጥረት የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ከሆነው የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጋር ትስስር ያለው ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ካሳ እና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ በረከት ስምዖን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡ የድርጅቱ ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜ በሰጡት መግለጫ ጥረት የተቋቋመው የአሁኑ ብአዴን የቀድሞው ኢህዴን በትጥቅ ትግሉ ወቅት በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ባሰባሰበው ንብረት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

ከ20 ዓመት በፊት የተመሠረተው ጥረት በአሁኑ ወቅት 17 በሥራ ላይ ያሉ ድርጅቶችን እንደሚያንቀሳቅስ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከጥረት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የተላጀ ልብስ ስፌት ፋብሪካ ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው ከኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በተከራያቸው ማሽኖች እንደሆነ ሠራተኞች ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡ በ1981 ዓ.ም የተመሠረተው ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ለገበያ ከሚያቀርባቸው የአንሶላ፣ ፎጣ እና የትራስ ልብሶች ሌላ የሽመና እና የፈትል ማሽኖች አሉት፡፡ ጣሊያን ለኢትዮጵያ በከፈለችው የደም ካሣ በ1953 ዓ.ም የተቋቋመው የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቃ ፋብሪካ ዋነኛ ምርቱ አንሶላ ነው፡፡ 

ሁለቱ የመንግሥት ፋብሪካዎች ለጥረት እንዲዛወሩ ቢወሰንም ለፋብሪካዎቹ ሥራ አመራሮችም ሆነ ሠራተኞች በይፋ የተገለጸ ነገር እስካሁን አለመኖሩን ለዶይቸ ቨለ አስተያየታቸውን የሰጡ ተናግረዋል፡፡ የሁለቱም ፋብሪካዎች ሥራ አስኪያጆች እስከትናንት ድረስ ጀርመን ፍራንክፈርት እየተካሄደ በሚገኝ የሳምንት አውደ ርዕይ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ብርሃኔ እስካሁን ስለ ፋብሪካው መሸጥ በይፋ የደረሳቸው ነገር እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡   

“ምንም የለም፡፡ ላለፉት አስር ኣመታት ሁሌም ጨረታ ይወጣል፡፡ ጋዜጣ ሲወጣ ሰው ደብዳቤ ይዞ ሊጎበኝ ሲመጣ ማስጎብኘት ነው እንጂ ለእኛ አሁን አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሁሌ ስለሚወራ ይሸጣል፣ ተሸጧል አዲስ ነገር አይደለም” ይላሉ አቶ ያሬድ፡፡  

ሁለቱ ፋብሪካዎች ለጥረት እንዲሸጡ ቢወሰንም የማዛወር ሂደቱ ገና እንደሚቀር አቶ ወንዳፍራሽ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም መጀመሪያ ክፍያውን መፈጸም ይኖርበታል። መሥሪያ ቤታቸው ለጥረት ኃላፊዎች ይህንኑ ባለፈው ሳምንት ማሳወቁንና ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ከጥረት በኩል መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ