1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፀረ ሕገ ወጥ ፍልሰት እና የኒዠር ሚና

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12 2010

ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ሕገ ወጥ ፍልሰት በመታገሉ ረገድ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኒዠር ቁልፍ ሚና ይዛለች።  የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉም ከአውሮጳ ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው። ይህን የኒዠር ትብብር የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ በዚህ ሳምንት በርሊንን በጎበኙት ጊዜ አሞግሰዋል።

https://p.dw.com/p/33KKS
Niger Flüchtlingsdrehkreuz Agadez
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

« የአውሮጳ ህብረት በአፍሪቃ የግሉን ወረት በማሳደግ ሕገ ወጥ ፍልሰትን ለመታገል የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል። »

ጀርመን ለኒዠር የምታደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗንንም ሜርክል ለፕሬዚደንት ኢሱፉ አረጋግጠዋል።  ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ሕገ ወጥ ፍልሰት በመታገሉ ረገድ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኒዠር ቁልፍ ሚና ይዛለች።  የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉም ከአውሮጳ ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው። ይህን የኒዠር ትብብር ያሞገሰችው ጀርመን ለዚችው ሀገር  የምታደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በዚህ ሳምንት በርሊንን ለጎበኙት የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ ገልጸዋል። ይሁንና፣ ሌሎች የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራትም አፍሪቃውያን ስደተኞች ከመጀመሪያውም ስደት እንዳይገቡ በትውልድ አገሮቻቸው፣ በኒዠር እና በሳህል አካባቢ ሀገራት ውስጥ በትምህርቱ እና በልማት ዘርፎች ገንዘባቸውን እንዲያሳሰሩ አሳስበዋል።   
« ሕገ ወጥ ፍልሰትን ለማስቆም በምናደርገው ትግል ላይ ኒዠር ከኛ ጋር በተሳካ ሁኔታ ጥሩ ስራ እየሰራች በመሆኗ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ይሁንና፣  አውሮጳ እና  ጀርመን ሊረዱት የሚገባው ጉዳይ፣ ጥረታችን ሊሳካ የሚችለው ስደተኞቹ የሀገሮቻቸውን ኤኮኖሚ ማልማት፣  ለሚቀጥለው ትውልድ ጥሩ ትምህርት መስጠት የሚችሉበትን አጋጣሚ ስንፈጥርላቸው ነው። በዚህም የተነሳ ሕገ ወጡን ፍልሰት የመታገሉ እና   ችግሩ ለሚመለከታቸው ሀገራት ሕዝቦችም የልማት እድል የመፍጠሩ አሰራራ ጎን ለጎን መካሄድ ይኖርበታል። »
አውሮጳውያቱ እና ስደተኞቹ የሚነሱባቸው እና መሸጋገሪያ ያደረጓቸው አፍሪቃውያት ሀገራት በቫሌታ ማልታ ባካሄዱት ጉባዔ ላይ ይህንኑ ትብብር ለማጠናከር የደረሱትን  ስምምነት በተግባር  መተርጎም እንደሚጠበቅባቸው ሜርክል አክለው ተናግረዋል። 
ፕሬዚደንት ኢሱፉም በበኩላቸው የስደት መንስዔን ለመታገል ስደተኞቹ  በሚሱባቸውን እና በሚተላለፉባቸው ሀገራት ውስጥ ብዙ የስራ ቦታ መክፈት የሚያስችል የአውሮጳውያን ወረት ሊኖር ይገባል ብለዋል፣ የፍልሰት ችግር አውሮጳንም የሚነካ ነውና።
« ለሕገ ወጥ ፍልሰት ትክክለኛው መልስ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ሊገኝ ይችላል። ብዙ የስራ ቦታ መፍጠር  ይቻል ዘንድ የግሉ ዘርፍ  በተለያዩት የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ብዙ ወረት ማፍሰስ  ይገባዋል። »
እንደ ኒዠሩ ርዕሰ ብሔር አውሮጳ ወረት በማፍሰሱ ተግባር ላይ የምታደርገው ተሳትፎ ብዙ ዘርፎችን ቢሸፈን ሰፊ ውጤት ያስገኛል።
« በግብርናው ዘርፍ  ላይ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪውም ዘርፍ ላይ ያተኮረ ወረት ያስፈልጋል።  አፍሪቃ ኢንዱስትሪያዊነትን ማስፋፋት አለባት። አፍሪቃ የጥሬ አላባ ምንጭ ብቻ መሆኗን ማቆም ይኖርባታል። ጥሬ አላባውን ወደ ምርትነት በመቀየር በንግድ ወደተለያዩ አፍሪቃውያት እና ወደሌሎች ውጭ  ሀገራት መላክ መጀመር አለባት፣ ከዚህ በተጨማሪ በዚያው በአፍሪቃ ፣ በተለይ ደግሞ ፣ በሳህል አካባቢ ሀገራት ውስጥ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቬስትመንትን  ማንቀሳቀስ ይኖርባታል። »
ለሕገ ወጡ ፍልሰት ዋነኛ መተላለፊያ በሆነችው ሊቢያ የሚታየው የፖለቲካ ቀውስ የሚያበቃበትን መፍትሔ ማፈላለጉ ጠቃሚነቱ በመጀመሪያ ደረጃ ለ ሰሜን አፍሪቃዊቱ  ሀገር  ቢሆንም፣ በስደተተኞች ብዛት ችግር ላጋጠማቸው አውሮጳውያት ሀገራትም እንደሚበጅ  ፕሬዚደንት ኢሱፉ ገልጸዋል።
በሊቢያ  በኩል አድርገው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ  ለመሄድ ለሚፈልጉ ምዕራብ አፍሪቃውያን  በተለይ የኒዠር ከተማ አጋዴዝ  ዋነኛ መሸጋገሪያ  ሆና ታገለግላለች። ሰው አሸጋጋሪዎችም  በነዚህ የተሻለ እድል ፈላጊዎች ትከሻ ሕገ ወጡን ንግድ አስፋፍተዋል።  በነዚህ ሰው አሸጋጋሪዎች አማካኝነትም በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዚሁ አደገኛ  የበረኃ እና የሜድትሬንየን ባህር ጉዞ አውሮጳ ለመግባት ያላቸውን ትልቅ ህልም  እውን ለማድረግ ይሞክራሉ። ይሁንና፣ የኒዠር መንግሥት  ይህ ተግባር በሕግ እንደሚያስቀጣ  ካስታወቀ ወዲህ ፣ በከተማይቱ ሁኔታዎች መቀያየራቸውን  ነዋሪዎቹም ገልጸዋል።  
እንደ አጋዴዝ ነዋሪዎች፣ የኒዠር መንግሥት በአውሮጳ ህብረት ግፊት ይህን ሕግ ከሁለት ዓመት በፊት ካወጣ ወዲህ  ብዙ ሰው አሸጋጋሪዎች ታስረዋል፣  ስደተኞችን የሚያጋጉዙባቸው ትላልቅ  ተሽከርካሪዎቻቸውም ተወርሰዋል።  አንድ የቀድሞ ሰው አሸጋጋሪ ሕገ ወጥ ስራ እንዳልሰራ ነው ያስታወቀው።
« ምንም ሕገ ወጥ የሚባል ነገር አልነበረም። በዚች ከተማ ውስጥ ወጣቶች ለስደተኞቹ  አገልግሎት የሚሰጡ ትናንሽ መደብሮች፣ የምግብ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና የመሳሰሉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያካሂዱ ነበር። አሁን ግን  የአጋዴዝ ኤኮኖሚ ወድቋል። »
አንድ የአጋዴዝ ነዋሪ የአውሮጳ ህብረት በኒዠር ለምታደርገው ትብብር በምላሹ ከልማቱ ርዳታ በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ ወረት እንደሚያሰራ ቢሰሙም በተግባር ያዩት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
« ወደ ኒዠር የሄዱ የአውሮጳ ህብረት ባለስልጣናት በዚችው ሀገር ውስጥ 200 ሚልዮን ዮሮ  ለመወረት ተስማምተው ነበር። እንደሚታየው ግን፣ እስካሁን አንድም ሳንቲም አልመጣም። »
በሕጉ ምክንያት የአጋዴዝ ንግድ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ ነዋሪዎቹ ዕለታዊ ኑሯቸውን ለመምራት እንኳን ችግር እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ።
« ልጆቻችን መመገብ አለብን። አሁን ገቢ ስለሌለን ይህን ማድረግ አንችልም። እንዴት አድርገን ነው እንደበፊቱ  ልጆቻችንን ማሳደግ የምንችለው? » 
የአውሮጳ ህብረት  ለልማት ማረመጃ የሚሆን ወረት በማፍሰስ ፈንታ ለኒዠር ፀጥታ አካላት ብዙ ድጋፍ ያደርጋል። የጦር ኃይሉ ስደተኞችን የሚያሸጋግሩትን ሰዎች በየበረኃው በመከታተል ላይ ይገኛል። እስከ ሁለት ዓመት በፊት ድረስ  በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ያልፉባቸው የነበሩ የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን ማለፍ በአሁኑ ጊዜ አዳጋች በመሆኑ ስደተኞች አውሮጳ የመግባት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሌሎች አዳጋች መንገዶችን እንደሚመርጡ እና ይህም ለሞት እንደሚያጋልጣቸው የአጋዴዝ ነውሪ ገልጿል    
« አሁንም ብዙዎች ይሞታሉ። ፍሮንቴክስን ፣ ቡድን አምስት የተባለውን የሳህል ጦርን የመሳሰሉ  ፕሮዤዎች አሉ። ድሮ ስደተኞቹን የሚያጓጉዙት አሽከርካሪዎች መደበናውን መንገድ ነበር የሚጠቀሙት። የኒዘር መንግሥት ሰራተኞች ይመዝግቡ ነበር። አሁን ሕጉ ከወጣ በኋላ ግን አሽከርካሪዎቹ፣ ስደተኞቹ  ሌላ መንገድ ነው የሚወስዱት። ስለዚህ ምን ያህል ስደተኞች በመንገድ ላይ እንደሚሞቱ  አናውቅም። »
አርያም ተክሌ

Niger Agadez Sahara Flüchtlinge Schuhe
ምስል Reuters/Akintunde Akinleye
Libyen Internierungslager für Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Brabo
Deutschland Merkel trifft Mahamadou
ምስል picture-alliance/dpa/R. Hirschberger

እሸቴ በቀለ