1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥበብ ለሃገራዊ አንድነት

ሐሙስ፣ ሰኔ 28 2010

«ሚዲያዉም ወግኖ ነበር ሲሰራ የነበረዉ። ወገንተኛነቱ ሕዝባዊ እንጂ፤ ለፓርቲ መሆን የለበትም ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ። ይህ እዉነት አይደለም እንዴ? እዉነት እኮ ነዉ! ሚዲያዉ መርጦ፤ ለሚወደዉ ማድላት፤ ለማይወደዉ ደሞ ጥላቻችን አይደለም ማስተላለፍ ያለበት። እዉነት ላይ ነዉ ተመስርቶ መስራት ያለበት ነዉ ያሉት፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ» ደበበ እሸቱ

https://p.dw.com/p/30uT5
Die Rolle der Kunst in Politik und Gesellschaft
ምስል Getu Temesgen

የኪነ-ጥበብ ድርሻ ምንድን ነዉ?

አንጋፋዉ የመድረክ ፈርጥ አርቲስት ደበበ እሸቱ ኪነ-ጥበብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለዉን ጉልህ ሚና አስመልክቶ ከተናገረዉ የተወሰደ ነዉ። ወዳጆቹና የሞያ አጋሮቹ ጋሽ ደበበ ሲሉ የሚጠሩት አንጋፋዉ አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ ሰኔ 20 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸዉ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን ጋብዘዉ ሞያዊ ስለጠና እና ዉይይት ባደረጉበት መድረክ ላይ ተጋባዥ ነበር። ጥበብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለዉ  አስተዋጽዖ፤ አርቲስቶች በሞያቸዉ፤ ማኅበረሰቡ ዘንድ ያለዉን ጉድፍ የማሳየት ለእዉነት ለፍትህ ብሎም ለአንድነት ጠበቃ የመሆን ኃላፊነት እስከምን ድረስ ይሆን?

ባለፈዉ ሰኔ 20 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ጋር ዉይይት አድርገዋል። በዚህ ስልጠና አልያም ዉይይት ላይ ወደ 500 የሚሆኑ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች መሳተፋቸዉ ነዉ የተነገረዉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ትኩረት እንደሚሰጥና የልማቱ አካል አድርጎ እንደሚያየው በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቢሰማም፤ ጠቅላይ ሚንስትር  ዶ/ር  ዐብይ በእለቱ ጥናት አድርገዉ ሰፊ ነጥቦችን አንስተዉ ለኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ሃሳባቸዉን በይፋ ማካፈላቸዉ መምከራቸዉ፤ ለጥበብ ያላቸዉን ፍቅር አሳይተዋል፤ ኪነ-ጥበብ ዳግም በድፍረት ለማኅበረሰቡ እንድትቆም አድርገዋል ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎችም ተስማምተዋል። ጥሪዉ፤ ስልጠና ዉይይት ተባለ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለጥበብ ምንነት ነዉ ገለፃ ያደረጉልን ያለን የዚሁ መድረክ ተሳታፊ የነበረዉ፤ በፊልም ስራ በአርታይ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሞያዉ የሚታወቀዉ ሁሴን ከድር ነዉ። በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አዳራሹ ሲገቡ አጠገባችን ሁሉ መጥተዉ ሰላምታ አቅርበዉልናል ብሎአል።

«ዉይይት አይደለም ያደረግነዉ። ስለ ጥበብ ነዉ ሰፊ ገለጻ ያደረጉት፤ የጥበብ አላማ ምን እንደሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለጥበብ ያለዉን አስተሳሰብ በመጥቀስ ማብራርያ ሰጥተዋል። በመቀጠል ጠቢብ ማን ነዉ? በሚለዉ ነጥብ ላይ የራሳቸዉን ምልከታ አንስተዋል።  በመጨረሻ ላይ ወደ አምስት መቶዉ በላይ የሚሆነዉ የኪነ-ጥበብ ማኅበረሰብ፤ ለሃገሩ በጥበብ ረገድ ሊያበረክት የሚችለዉን አስተዋፅኦ፤ እንደዚሁ ገልፀዉልናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅርን፤ አንድነትን፤ ሠላምን ከመስበክ አንፃር፤ ሃገር ዉስጥ እስከዛሬ መሰራት የነበረበትን ያህል አልተሰራም የሚል እምነት አላቸዉ። ከዚህ በኋላ በተለይም ሕዝብ ለሕዝብ ኃሳብን በማንሳት፤ በቅድምያ በሃገር ዉስጥ ፍቅርን ሠላምን በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረፅ፤ «ቱር» ወይም የጥበብ ዝዉዉር እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከሃገር ዉጭ ሃገራት፤ ኤርትራ፤ ኬንያ፤ ጅቡቲ፤ ሶማሌ፤ ሱዳን፤ ጅቡቲ እያልን በየሃገሩ የሚዞር ቡድን መኖር እንዳለበት ነግረዉናል።»    

በመድረኩ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር የነበሩት የኪነ-ጥበብ ማኅበረሰቦች የሻይ ግብዣ ጉብኝት ሁሉ ነበራቸዉ። ሁሴይን ከድር እንደሚለዉ በምሳ ግብዣም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆመዉ ነዉ ያስተናገዱን፤

«ከአዳራሽ እንደወጣን የሻይ ግብዣ ከተደረገልን በኋላ፤ ቤተ-መንግሥትን ጎብኝተናል። ቤተ-መንግሥቱ  አፄ ምኒሊክ፤ አፄ ኃይለስላሴ፤ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ፤ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የኖሩበት ነዉ። ይህን ማየታችን በጣም የተለየ ስሜት ነበር የፈጠረብን። እነዚህን ካየን ከጨረስን በኃላ ወደ ምሳ ግብዣ ነበር የሄድነዉ። ምሳ ግብዣዉ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ እያንዳንዳችን ጠረቤዛ ላይ እየመጡ ነበር፤ ምግቡ ጣፈጣችሁ? ምን ይጨመር እያሉ ሰላም ሲሉንና ሲያስተናግዱን የነበረዉ። እና ሁኔታዉ እጅግ የሚያስገርም ከአንድ የአገር መሪ በታሪክም ያልሰማነዉ ልዩ የሆነ ነገር ነበር። ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መንግሥታት ከማኅበረሰቡ ያላቸዉን ርቀት አስመልክተን ብዙዎቻችን ወቀሳ እናቀርብ ነበር። እናም የጠቅላይ ሚኒንስትሩን ግብዣ እና ሁኔታ ሁሉ ፤ ይህ ነገር ይቀጥላል? ህልም ነዉ? ወይስ አርተፊሻል? የሚል ጥርጣሪ ዉስጥ ሁሉ ገብተናል። የሚዘልቅ ከሆነ ለማኅበረሰቡ ትልቅ ጠቀሜታ ያለዉ ሆኖ ነዉ ያገኘነዉ። ሃገራችን ሌሎች ሃገራት በደረሱበት የተሻለ ደረጃ ላይ ትደርስ ይሆን በሚል ሃሳብ እንድናዳብር አድርጎናል።»

Die Rolle der Kunst in Politik und Gesellschaft
ምስል Getu Temesgen

ሌላዉ በዚሁ ዝግጅት ላይ የታደመዉ አንጋፋዉ አርቲስት ደበበ እሸቱ ጥበብን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የተሰጠን ስልጠናም ሆነ ማብራርያ እጅግ ግሩም ነበር ብሎአል ። «በጣም ግሩም የሆነ ስልጠና ነዉ የሰጡን ማለት ይቻላል፤ እንደተባለዉ። ምክንያቱም የኪነ-ጥበብ ድርሻ ምንድን ነዉ? ኪነ-ጥበብ ምንድን ነዉ? ባለሞያዉስ ምንድን ነዉ?  ምን ማድረግ አለበት? ለኅብረተሰቡ ምን መቅረብ አለበት? ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች እስከዛሬ ቢሰሩም ቁጥራቸዉ ይሄን ያህል አይደለም፤ የበለጠ ልትሰሩ ይገባችኋል፤ ብለዉ ነዉ መመርያ የሰጡት። ስለዚህ የቀረ ነገር የለም በጥበብ ረገድ ሁሉንም ነገር ነግረዉናል። በጣም ብልህ ሰዉ ናቸዉ። ከኛ በተሻለ መንገድ ጥበቡ ማድረግ ያለበትንና ፤ ጥበበኛዉ ማድረግ ያለበትን፤ አንብበዉ አጥንተዉ፤ ነዉ ያቀረቡል። »

ጋሽ ደበበ የኪነ-ጥበቡ ማኅበረሰብ ከዚህ ስብሳባም ሆነ ስልጠና በኋላ ተነሳሽነት አግኝቶአል የሚል እምነት አለህ? 

«ወደዝያ የማንሄድ ከሆነ ሞያዉን መተዉ ነዉ ያለብን። አሁን በተካሄደዉ፤  ግንኙነት ግን ይሄንን እንድናደርግ ከህሊናችን ጋር መነጋገር እንዳለብን፤ መልሰን ደግሞ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ነዉ እኔ የተገነዘብኩት። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት በመካከላችሁ አለመግባባት ሊኖር ይችላል፤ ይሄ አለመግባባት ግን ዛሬ ከጀመርነዉ ፤ የሰላም የመቻቻል እና የአንድነት መርህ ላይ ተመስርታችሁ፤ በመካከላችሁ ያለዉን አለመግባባት አጥፍታችሁ ፤ ለሃገር እና ለወገን ቁሙ ነዉ ያሉት። በመካከላችን አለመግባባት ካለ፤ እንዳለም እርግጠኛ ነኝ ፤ ያ ችግር አለበት የምንለዉ  አካባቢ፤ ችግር የለብንም ከምንለዉ ሰዎች፤ ሁለታችን አንድ ላይ ሆኖ ፤ በግልጽ መወያየት እና መነጋገር ያስፈልጋል። ይቅር መባባል እና ያለፈዉን ትተን በአዲስ መንፈስ፤ በአዲስ አካሄድ ወደፊት መቀጠል ያለብን ይመስለኛል። ኅብረተሰቡን መቅደም መቻል አለብን። ያቃተን ያ ነዉ።

ገንዘብን ማስቀደም  ማስቀረት ይኖርብናል። በጥቅም መሳሳብን ማቆም አለብን። ግለሰቦችን እያመሰገንን፤ የጥበብ ሥራዎችን የግለሰቦች ማመስገኛ ማድረግ ማቆም አለብን። ይሄነዉ የተነገረን፤ ይሄ ነዉ የስማማነዉም፤ በዚህ መ ንገድ መቀጠል ካልቻልን ሞያዉን እየተዉነዉ መዉጣት ነዉ የሚያስፈልገዉ። ሁላችንም ይቅር ለመባባል ፈቃደኛ ለመሆን ጥንካሪዉን ማግኘት አለብን። ጥፋት የሰራንም ሰዎች ካለን ይቅር ለማለትና ይቅር ለመባል ፈቃደኝነታችንን ማሳየት አለብን። በአንድ  ወገን ያለዉን እየጨፋፍነን መቀመጥ አንችልም። ይህንን ነዉ ከስብሰባዉ የተረዳሁት እኔ።»      

ጋሽ ደበበ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያዉንም ቢሆን ጠቅሰዋል። ሚዲያዉ ጥበብን ካላካተተ፤ እንደሚጮህ ቆርቆሮ ያልህ ነዉ ሲሉ ነዉ የተናገሩት፤ ሚዲያዉንስ ምንድን ነዉ የምትመክረዉ?

«ሚዲያዉም እንደኛዉ ነዉ። ወግኖ ነዉ ሲሰራ የቆየዉ። ወገንተኛነቱ ሕዝባዊ መሆን አለበት እንጂ ለግለሰብ ለፓርቲ መሆን የለበትም ነዉ ያሉት። ይህ እዉነት አይደለም እንዴ? እዉነት እኮ ነዉ። ሚዲያዉ መርጦ፤ ለሚወደዉ ማድላት፤ ለማይወደዉ ደሞ ጥላቻችን አይደለም ማስተላለፍ ያለበት። እዉነት ላይ ነዉ ተመስርቶ መስራት ያለበት። ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሉት ጥበብ ያለበት ማንኛዉም ነገር ነዉ ይሁን ነዉ ያሉት። የኔም እምነት እንደዛ ነዉ። ጥበብን ያላጎናፀፈ፤ ጥበብን ያላቀፈ ነገር፤ ጣዕም አይኖረዉም»                 

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ጥበብ ለየትኛዉም ርዕዮተዓለም ማሸርገድ የለባትም፤ጥበብ ለማኅበረሰብ ልትቆም ይገባታል የሚል አቋም ነዉ ያላቸዉ ሲል ሁለገቡ ባለሞያ ሁሴይን ከድር ነግሮናል። በርግጥ የኪነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ በኋላ የተከሰተዉን ነገር ገና አላብላላዉም፤ ህልም ዉስጥ እንዳለ ነዉ የተሰማዉ፤ ያለን ሁሴይን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በጭምጭምታ መጽሐፍት ደርሰዋል እየተባለ ሲወራላቸዉ የነበረዉን ወሬም እዉነትነቱን አረጋግጠዋል ፤ ለጥቂቶችም መፃሕፍቶቻቸዉን በሽልማት መልክ መስጠታቸዉን ገልፆአል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ